በዳላስ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የዘረኛው አገዛዝ ተወካዮች ያዘጋጁትን ስብሰባ አስተጓጎሉ

የሎስ አንጀለሱ የወያኔ ቆንስላ ሹመኛ ታዬ አስቀስላሴ በዳላስ ላሉ ኢትዮጵያውያን ስለ እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ተብዬው ገለጻ ለመስጠት የተገኘበት ስብሰባ በአካባቢው ባሉ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ተቃውሞ ተስተጓጉሏል።

ሰዎች እሱን ሊሰሙ የተሰበሰቡ የመሰለው ታዬ በፈገግታ ሲፈካ፣ ንግግሩን ሳይጀምር የቀደመው አንድ ኢትዮጵያዊ ተሰብሳቢዎቹ በድህረ-ምርጫ 97 ለወደቁት ሰማእታት የህሊና ጸሎት በማድረግ ስብሰባውን እንዲጀምሩ ጠይቋል። ቀጥሎም በስብሰባው አዳራሽ ከተገኙት ውስጥ አብዛኞቹ አስቀድመው የተጠራሩ አገር-ወዳድ ኢትዮጵያውያን በመሆናቸው፣ ጥሪውን በመቀበል ተነስተው ቆመዋል።

በወቅቱ ከመድረኩ አካባቢ የሚመጡ ድምጾች፥ “የምን ሰማእታት?” እያሉ ይጠይቁ ነበር፤ ከተሰብሳቢዎቹ አንዱም “ለሁሉም ሰማእታት፣ ደርግ ለገደላቸውም ይሁን ለሁሉም” ብሎ ለማብራራት ቢሞክርም፤ በጉዳዩ ያልተደሰቱ ጥቂት የዘረኛው አገዛዝ ደጋፊዎች አተካራ ፈጥረዋል። መድረክ ላይ ቆሞ እድል እንዲሰጠው ሲማጸን የነበረው ታዬ፤ በተሳታፊዎቹ ከቁብ ባለመቆጠሩ ቀጥሎ የተነሳውን ረብሻ ለማስቆም አልቻለም።

ታዬ አስቀስላሴ የወያኔ ላንቲካ ወይም የምልክት ሹመኛ ነው ያሉን አንድ የዝግጅት ክፍላችን ምንጭ፤ በሎስ አንጀለስ በሚገኘው ቆንስላ፣ እውነተኛው ባለስልጣን ከሱ በስተጀርባ የተቀመጠው ተክሉ ሃብተወልድ ነው ብለዋል። እኒሁ ምንጭ፥ ግለሰቡ ዘረኛውን አገዛዝ በመወከል ራሱን የሚያዋርድበት ምክንያት ጥቅም እንደሆነ በመግለጽ፤ በ1997 ምርጫ ማግስት ተቃዋሚዎች ስልጣን የሚረከቡ መስሎት ለአንድ የሰሜን አሜሪካ የቅንጅት ድጋፍ ቡድኖች አመራር አባል ስልክ ደውሎ “እንዴት ልርዳችሁ?” ብሎ መጠየቁን ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ግለሰብ እንደሰሙ ጠቅሰዋል።