ፍትህ የተነፈጉ ኢትዮጵያውያን በወያኔ ሹመኞች ላይ ጥቃት መፈጸም መጀመራቸውን ዘገባዎች አመለከቱ

የሱሉልታ ከተማ ነዋሪዎች ባለፈው ሳምንት በከተማቸው የወያኔ ሹመኛ ላይ የጥቃት እርምጃ ወስደዋል ሲል የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ድርጅት – ኢሳት – ዘግቧል።

የኢሳት ዘገባ እንዳመለከተው፥ መሬታቸው በህገ-ወጥ መንገድ የተቀማባቸው ነዋሪዎች የከተማዋ ከንቲባ ከስልጣን መውረዱን ሲሰሙ፣ በሱና በተባባሪው ላይ ድብደባ ፈጽመዋል። ከባለስልጣኑ መሬት የወሰዱ ባለሃብቶችም በተመሳሳይ ሁኔታ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ታውቋል። የከተማው ፖሊስ ጥቃቱን ተከትሎ የተነሳውን ረብሻ ለመቆጣጠር ባለመቻሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ወደ አካባቢው መሄዳቸውንም የኢሳት ዘገባ ገልጿል።

በወያኔ አገዛዝ ሹመኞች ላይ በሱሉልታ የተፈጸመው ጥቃት ከመሬት ጉዳይ ጋር የተያያዘ ይሁን እንጂ፤ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚገኙ ዜጎች መብታቸውን የማስከበሩን ጉዳይ ወደገዛ እጃቸው መውሰዳቸውን መረጃዎች እያመላከቱ ነው። ከዚህ በፊት ለዝግጅት ክፍላችን የደረሰ መረጃ እንደሚጠቁመው፤ ጉኢሽ የተባለው የአላማጣ ከተማ ከንቲባ በተመሳሳይ ሁኔታ በነዋሪዎች ድብደባ ደርሶበታል። በህዝቡ ላይ የሚያደርሰውን ግፍ ካላቆመ ተጨማሪ ቅጣት እንደሚደርስበት ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት መለቀቁንም የደረሰን መረጃ ጠቁሟል።