በኖርዎይ ኦስሎ ሂዩማን ራይትስ ዋች ስለ ኢትዮጵያ ባወጣው ሪፖርት ላይ ውይይት ተካሄደ
ባለፈው ሰኞ ኖቨምበር ስምንት ቀን 2010 ዓም በኖርዎይ ኦስሎ ከተማ የኖርዎይ ዓለም አቀፍ ህግና ፖሊሲ ኢንስቲትዩት ያዘጋጀውና Development without Freedom How Aid Underwrites Repression in Ethiopia በሚል ርእስ ሂዩማን ራይትስ ዋች በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት ላይ ያተኮረ ወርክሾፕ ተካሄደ። በስብሰባው በርካታ ኢትዮጵያዊያን፤ ተጋባዥ እንግዶች፤ የኖርዎይ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት እንዲሁም የተለያዩ ርዳታ ሰጪ ድርጂት ወኪሎች የተገኙ መሆኑን የግንቦት 7 ድምጽ ዘጋቢ ከስፍራው ባስተላለፈው ዘገባ አሳውቋል።
በእለቱ ሂዩማን ራይትስ ዋች ያወጣውን ሪፖርት ለውይይት ያቀረቡት በድርጅቱ ከፍተኛ ተመራማሪና የአፍሪቃ ቀንድ ቡድን መሪ ሌዝሊ ሌፍኮ ሲሆኑ፤ በውይይቱ የኖርዎይ መንግስት ስቴት ሴክሬታሪ ኢንግሪድ ፊስካ፣ በቅርቡ የሂዩማን ራይስት ዋች የዓመቱ ምርጥ ተሸላሚ የሆነው ኢትዮጵያዊው ዮሴፍ ሙሉጌታ፤ የኖርዎይ ዓለም አቀፍ ህግና ፖሊሲ ኢንስቲትዩት ኤክስፐርት ፕሮፌሰር ሼትልና ሌሎችም በርካታ ተሳታፊዎች ተገኝተው ነበር።
ሌዝሊ ሌፍኮ ሪፖርቱን አስመልክቶ ባቀረቡት አጭር ማብራሪያ በኢትዮጵያ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታና ኢትዮጵያውያን ያሉበትን እጅግ አስከፊ ገጽታ፤ የወያኔው አገዛዝ በምን አይነት መልክና ሁኔታ ለልማት ርዳታ እየተባለ ከውጭ ሃገራት መንግስታት የሚጎርፍለትን ገንዘብ ለፖለቲካ ፍጆታ እንደሚያውል በተጨባጭ ማስረጃዎች በማስደገፍ ተሳታፊዎችን ባረካ መልኩ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ሌፍኮ ከኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ ጀምሮ እስከ ዝቅተኛ የወረዳ ገጠር ቀበሌዎች መዘዋወራቸውን ጠቅሰው የራሳቸውን ተሞክሮና መረጃ በመመርኮዝ ዘረኛውና አምባገነኑ የወያኔ አገዛዝ በኢትዮጵያዊያን ላይ እያደረሰ ያለውን በደል በዝርዝር አስረድተዋል። በማብራሪያቸው መጨረሻም ምእራባዊያን ለጋሽ ሃገራት ለአገዛዙ የሚለግሱት ገንዘብ ለፖለቲካ ፍጆታ መዋሉንና በኢትዮጵያ የሰባዊ መብቶች ጥሰት እጂግ በሚገርም ሁኔታ እየተባባሰ መሄዱ እየታወቀ በተቃራኒው የለጋሽ ሃገራት ርዳታ ደግሞ በእጥፍ መጨመሩን አስረድተዋል። ሌፍኮ ይህ ምን አንድምታ እንዳለውና ምንስ መልእክት እያስተላለፉ እንደሆነ ጥያቄውን መመለስ ያለባቸው ራሳቸው ለጋሽ ሃገራቱ ናቸው በማለት አጠቃለዋል።
በቀረበው ሪፖርት ላይ ሰፊ ውይይት፣ ክርክርና በተለይም በእለቱ ስብሰባው ላይ ከተሳተፉ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን እልህና ቁጭት በተሞላበት መልኩ በኢትዮጵያ እየታየ ስላለው አስከፊና አሳዛኝ ሁኔታ ተጨማሪና ማጠናከሪያ መረጃዎች ተሰጥተዋል። ኢትዮጵያዊያኑ ኖርዎይን ጨምሮ ምእራባዊያን ሃገራት የልማት ርዳታ እያሉ የሚልኩትን ገንዘብ የወያኔው አገዛዝ የጥይት መግዣና ወገኖቻችንን ማስጨረሻ እያደረገው እንደሆነ ሊያውቁና አስቸኩአይ የሆነ ርምጃም ይወስዱ ዘንድ ጠይቀዋል።