በምርጫ ታዛቢው ሪፓርት መደሰታችን በኅብረቱና መንግሥታቱ ፓሊሲ ላይ ያለንን ቅሬታ አይለውጥም!!!

የአውሮፓ ኅብረት የኢትዮጵያ ምርጫ 2002 ታዛቢዎች የተልዕኮው ማጠቃለያ ሪፖርት አቅርቧል። ቡድኑ የ2002ቱ የህዝብ ተወካዮችና የክልል ምክር ቤቶች ምርጫ “ለምርጫ የተቀመጡ ዓለም ዓቀፋዊ ግዴታዎችን ያላሟላ ነበር” ሲል ደምድሟል።

የታዛቢ ቡድኑ በሪፓርቱ ምርጫው “አስፈላጊ በሆነው የሂደቱ ክፍል ውስጥ ግልጽነትና ለሁሉም ተቃዋሚዎች የተመቻቸ የመጫወቻ ሜዳ ማዘጋጀት ያለመቻል ጉድለት ነበረው። የበለጠ ተገቢ እና ወካይ የምርጫ ሂደት ለማረጋገጥ የሚያስችል የምርጫ ሂደትን ለማረጋገጥ የሚያስችል በቂ የሆነ ጥረት አልተደረገም” ሲል ተችቷል።

ከዚህም በተጨማሪ

  • መራጩ ህዝብ የገጠመውን የመረጃ አፈና፤
  • የምርጫ ቦርድ የተፎካካሪ ፓርቲዎችን አመኔታ ማጣት፤
  • ገዢው ፓርቲ የመንግሥትን ንብረት ለምርጫ ቅስቀሳ መጠቀሙ፤
  • በመንግሥትና በፓርቲ መካከል ድንበር አለመከለሉ፤ እና
  • በድምጽ ቆጠራና በድምጽ ማስታወቅ ወቅት በርካታ ጉድለቶች መታየታቸው በሪፓርቱ ላይ ተተንትኗል።

በማጠቃለያም ቡድኑ ለወደፊቱ ቢደረጉ ይበጃሉ ያላቸውን የማሻሻያ ነጥቦችን አቅርቧል። ካቀረባቸው የማሻሻያ አስተያየቶች ውስጥ:-

  1. የተቃዋሚዎችን ተሳትፎና ብቃት ለማሳደግ እና የፓለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት አንድ በስደት ላይ የሚገኙ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ እንዲመለሱ እና የታሰሩት እንዲፈቱ፤
  2. በገዢ ፓርቲና በመንግሥት መካከል ግልጽ የሆነ ልዩነት እንዲኖር፤
  3. የመራጮችና የተመራጮች ምዝገባ ግልጽነት እንዲኖረው እና ምዝገባው በኮምፒዩተር የታገዘ እንዲሆን፤ እና
  4. ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመኔታ ያለው ተቋም እንዲሆን የሚሉ ይገኙበታል።

የአውሮፓ ኅብረት የምርጫ ታዛቢዎች ቡድን ተልዕኮዉን በብቃት ስላከናወነ ሊመሰገን ይገባል። ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ለልዑካኑ ቡድን መሪ ሚስተር ቲጅስ በርማን እና ባልደረቦቻቸው ያለውን አክብሮት ይገልፃል።

ይሁን እንጂ የአውሮፓ ኅብረትና የአውሮፓ መንግሥታት በዚህ ሪፓርት ምክንያት የሚወስዱት ተጨባጭ እርምጃ ይኖራል ብለን አንገምትም። ስለሆነም ሪፓርቱ በኅብረቱና በመንግሥታቱ የኢትዮጵያ ፓሊሲ ላይ ያለንን ቅሬታ የሚለውጥ አይደለም።

የ1997 ምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ ሚስስ አና ጎሜዝ ተመሳሳይ ሪፓርት አቅርበው እንደነበር ይታወሳል። የአውሮፓ ኅብረትና መንግሥታቱ በዚያ ሪፓርት መነሻ ተጨባጭ እርምጃዎችን ወስደው ቢሆን ኖሮ የዘንድሮው አሳዛኝ ድራማ ባልተከሰተም ነበር ብለን እናምናለን።

በጫንቃችን ላይ የተንሰራፋውን ዘረኛና አምባገነን ሥርዓት ማስወገድ የኛ ኃላፊነት ስለመሆኑ የዘነጋንበት ወቅት የለም። ሆኖም ግን የአውሮፓ ኅብረት፣ የአውሮፓ መንግሥታት እና ሌሎችም ዲሞክራሲያዊ አገሮች በሥልጣን ላይ ያለው ሥርዓት ህገ-ወጥ መሆኑን እያወቁ የፋይናንስ፣ የወታደራዊና የመረጃ ድጋፍ እያደረጉለት ትግላችንን አዳክመውብናል። ዲሞክራሲያዊ አገሮች እሴቶቻቸውን በውጭ ጉዳይ ፓሊሲዎቻቸው በተለይም በኢትዮጵያ ፓሊሲዎቻቸው ማየት እንሻለን።

ከዘረኛና አምባገነን ሥርዓት ጋር መወገን የአጭር ጊዜ ጠቀሜታ ያለው ቢመስልም ጉዳቱ እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ የአውሮፓ ኅብረትና መንግሥታቱ እንዲያጤኑ አበክረን እናሳስባለን። የአካባቢ ሰላም የሚጠበቀው፤ እውነተኛ የኢኮኖሚ ልማት የሚኖረው፤ ፍትህ የሚሰፍነው የህዝብ ውክልና ያለው መንግሥት ሲኖር መሆኑን ኅብረቱና መንግሥታቱ እንዲያጤኑ እናሳስባለን።

እነሱ በመረጡት መንግሥት መመራት እንደሚሹ ሁሉ የኢትዮጵያ ህዝብም በመረጠው መንግሥት መመራት የሚሻ መሆኑን ልብ እንዲሉ ደግመን ደጋግመን እናሳስባለን።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!