በዜጎች አፈና የሚሳተፉ የወያኔ ባለስልጣናት ወደ አውሮፓ አገራት ከመግባት እንዲታገዱ የጀርመኑ ግሪን ፓርቲ ጥሪ አቀረበ
የጀርመን አገሩ ግሪን ፓርቲ ባወጣው የአቋም መግለጫ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲን ለማስፈን የሚደርገውን ጥረት ለመደገፍ መወሰኑ ተዘግቧል።
ፓርቲው በመግለጫው፥ ዘረኛው አምባገነን መለስ ዜናዊ የዛሬ ሃያ አመት ስልጣን ሲቆጣጠር ዴሞክራሲን አሰፍናለሁ ብሎ ቃል መግባቱ ሃሰት ሆኖ እንደተገኘ አስታውሶ፤ በኢትዮጵያ የሚፈጸመውን ግፍ እና አፈና ዘርዝሯል። ባለፈው አመት ግንቦት 15 ቀን የተካሄደው የምርጫ ተውኔት በነፃ እና ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ አለመካሄዱን እና በተቃዋሚ ቡድኖች ላይ ጥቃት ሲካሄድ መቆየቱን መስክሯል። የወ/ት ብርትኳን ሚደቅሳን ለሁለት አመታት እስር ላይ መቆየት፤ የወ/ሮ አማረች ገላኔን እና የአቶ አረጋዊ ገብረዮሃንስን ግድያም እንደ ምሳሌ ጠቅሷል።
ዘረኛው እና አምባገነናዊው አገዛዝ በአገር ቤት ገለልተኛ መገናኛ ብዙሃንን ማስወገዱ ሳያንሰው፤ ከውጭ አገር የሚተላለፉ የኤሌክትሮኒክ መገናኛ ብዙሃንንም ማፈኑን ፓርቲው አውግዟል።
አለማቀፉ ማህበረሰብ በዚህ ጉዳይ ላይ ሲያሳይ የቆየው መቆጠብ ተቀባይነት እንደሌለው በመጥቀስ፤ ከዚህ በኋላ ዝምታው ሊያበቃ ይገባዋል ብሏል።
ግሪን ፓርቲ ይህንን አላማ ከግብ ከማድረስ አኳያ በርካታ የተግባር ውሳኔዎችን የደረደረ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ በሚካሄደው የሰብአዊ መብት ጥሰት እና አፈና ተሳታፊ የሆኑት ግለሰቦች ወደ አውሮፓ ህብረት እንዳይገቡ እና ገንዘባቸውም እንዲታገድ የህብረቱን አባል አገራት እንደሚጠይቅ ገልጿል። የወያኔ አገዛዝ በኢትዮጵያ ውስጥ በሚፈጸሙት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ላይ ምርመራ እንዲያካሄድ የጀርመን መንግስት ጫና እንዲያደርግም እጠይቃለሁ ብሏል።
የዝግጅት ክፍላችን በዚህ ጉዳይ ላይ ያነገራቸው አንድ የፖለቲካ ተንታኝ፥ ምንም እንኳ እንደዚህ ንቁ የሆኑ አንዳንድ የምእራባዉያን አገራት ቡድኖች እና ግለሰቦች ቢኖሩም፤ ነፃነታችንን ልናስከብር የምንችለው ግን እኛው እራሳቻን መሆናችንን ለደቂቃ እንኳ መርሳት እና መዘናጋት የለብንም ብለዋል።