የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከአገዛዙ የፍራፍሬ ድርጅት ብርትኳን እንዲገዙ እየተገደዱ ነው

“ኢት ፍሩት” የተባለው እና በወያኔ ቁጥጥር ስር የሚገኘው የመንግስት የፍራፍሬ ድርጅት፤ ሙዝ ብቻ ለመግዛት የሚፈልጉን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ብርትኳንም እንዲገዙ እያስገደደ መሆኑን ከመዲናይቱ የደረሰን ዘገባ አመልክቷል።

የግንቦት 7 ድምጽ ዘጋቢ አጠናቅሮ በላከው ዘገባ እንደሚያሳየው፥ የሙዝ ዋጋ ከብርትኳን ጋር ሲወዳደር ርካሽ በመሆኑ፣ አብዛኛው ነዋሪ ሙዝ ብቻ ሲገዛ በመስተዋሉ፤ ድርጅቱ ብርትኳን ለማይገዙ ተጠቃሚዎች ሙዝ አልሸጥም ብሎ ከልክሏል። ሙዝ በኪሎ ከ6-7 ብር ሲሆን፤ የብርትኳን ዋጋ የዛን እጥፍ እንደሆነ ታውቋል። ብርትኳን የተወደደበት ምክንያትም በአብዛኛው በአገዛዙ ቁጥጥር ስር ባሉ የመንግስት እርሻዎች ስለሚመረት ነው ተብሏል።

የግንቦት 7 ድምጽ ባለፈው አመት ባቀረበው ዘገባ፣ አንድ የኢትዮጵያ መከላከያ አውሮፕላን ብርትኳን ጭኖ በደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ ወደሚገኝ የፍራፍሬ ነጋዴ መውሰዱን መዘገባችን ይታወሳል። የፍራፍሬ ነጋዴው በማይታወቅ ምክንያት ብርትኳኑን ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆኑ፣ የአውሮፕላኑ አብራሪዎች በዋና ከተማዋ በጁባ መሃል ላይ ፍራፍሬውን አራግፈው ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸውን በወቅቱ የአይን እማኞች ለዝግጅት ክፍላችን ገልጸዋል። ፍራፍሬው የመጣው ከመንግስት እርሻ ሲሆን፤ ከሽያጩ በስተጀርባም የአገዛዙ ባለስልጣናት እንደነበሩበት ዘገባው ጠቅሶ ነበር።