ዘረኛውና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ የውጭ እርዳታን ለአፈና ማዋሉ መወገዙ እንደቀጠለ ነው

“ሂውማን ራይትስ ዋች” የተባለው አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ሰራተኛ የሆኑት ሚስ ሌስሊ ሌፍኮው ሰሞኑን ባወጧቸው ጽሁፎች የአውሮፓ እና የካናዳ መንግስታት አፋኝ የሆነውን የወያኔ አገዛዝ እየረዱ ነው ብለዋል።

“ሂውማን ራይትስ ዋች” በቅርቡ ባወጣው ሰፊ ሪፖርት፣ ምእራባውያን መንግስታት ለወያኔ በአመት ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ እየሰጡ እንደሆነና፤ ያም እርዳታ ለዘረኛውና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ የጭቆና ስራ እየዋለ እንደሆነ መግለጹን መዘገባችን ይታወሳል።

ሌስሊ ሌፍኮው ዩሮፕ ቮይስ ለተባለው ድረ-ገጽ በጻፉት ጽሁፍ፥ የአውሮፓ አገራት ለወያኔ ከሚሰጠው እርዳታ አንድ ሶስተኛውን እንደሚሸፍኑ እና የአውሮፓ ኮሚሽን ብቻውን በየአመቱ 400 ሚሊዮን ዩሮ ለአገዛዙ እንደሚሰጥ ገልጸዋል። ይህ እርዳታ ደግሞ የድሆችን ህይወት በማሻሻል ስም የሚመጣ ቢሆንም፤ እውነታው ግን ለገዢው ቡድን ድጋፍ ለማሰባሰብ እና የተቃዋሚ አባላት እና ደጋፊዎችን ለመቅጣት ስራ ላይ እየዋለ ነው ሲሉ አስረድተዋል።

ሲቲዚንስ ስፔሻል ለተባለ የካናዳ አገር የመረጃ አውታር በላኩት ጽሁፍ ደግሞ፥ የምእራባውያን መንግስታት ለጋሽ ድርጅቶች አለ የተባለውን ችግር በጽሞና በመመልከት ፈንታ በማስተባበል ላይ የበለጠ ጉልበት ማፍሰሳቸው አስደንጋጭ ነው ብለዋል። የወያኔ አገዛዝ እርዳታን ለፖለቲካ አፈና መጠቀሙ ሰሞኑን እንደገና አለማቀፍ ትኩረት የሳበ ሲሆን፤ የብሪታንያው ቴሌግራፍ ጋዜጣ ሰሞኑን ባወጣው ጽሁፍ የአገሪቱ መንግስት እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አፋኝ መንግስታት የሚሰጠውን እርዳታ እንደገና እንዲያስብበት ጥሪ አቅርቧል።