አገራችን ገድሏት የማያውቅ አንድ ነገር ቢኖር የሚጋደልላት ጀግና ነው
“ብሬቭ ሃርት” ወይም ቆራጥ ልብ የተባለው ፊልም ከሰባት ዘመናት በፊት የኖረውን የስኮትላንዳዊውን አርበኛ ዊሊያም ዋሌስ ታሪክ ይተርካል። ዊሊያም ዋሌስ በወቅቱ እስኮትላንድን ከብሪታንያ የቀኝ ግዛት አገዛዝ ነጻ ለማውጣት ይደረጉ በነበሩት ጦርነቶች ላይ ከፈጸማቸው ገድሎች የተነሳ፤ ጀግና ቢሞት እንኳ ስሙ ለዘላለም ይኖራልና፣ እስከዛሬ ድረስ በአገሩ እንደ አርበኛ እና ብሔራዊ ጀግና የሚታሰብ ሰው ነው።
ቆራጥ ልብ በተባለው ፊልም ላይ፣ የእንግሊዝ ንጉስ እስኮትላንድን ወሮ የአገሪቱ ንጉስ ብሎ እራሱን ሾሟል። ከዛ ቀጥሎ በሰፈነው ኢ-ፍትሃዊ አገዛዝ ምክንያት ዊሊያም አባት እና ወንድሙን አጥቶ ነበር። ወደ ውጭ አገር ሄዶ አጎቱ ዘንድ ያደገው ዊሊያም ከአመታት በኋላ ሲመለስ፤ አሁንም የአገሩ ህዝብ በእንግሊዙ ንጉስ፣ በኤድዋርድ ሎንግሻንክ ጨካኝ አገዛዝ ስር ይማቅቅ ነበር። የንጉሱ ሹሞች የጭሰኞቹን ልጃገረድ ልጆች እየቀሙ ክብራቸውን መድፈር በህግ እስኪፈቀድላቸው ድረስ የእስኮትላንድን ህዝብ ያሰቃዩ ነበር።
ዊሊያም ዋሌስ ወደ አገሩ ተመልሶ ያየውን ነገር አልወደደውም። ይሁን እንጂ በቻላቸው መጠን ሁሉ የእንግሊዝን የጭቆና አገዛዝ ሲዋጉ የቆዩ የመንደሩ ሰዎች ተጠግተው የአባቱን አርበኝነት በማስታወስ እንዲቀላቀላቸው ሲጠይቁት ፈቃደኛ አልነበረም። ዊሊያም የልጅነት ዘመን ፍቅሩን አግኝቶ እሷን አግብቶ በሰላም እያረሰ ለመኖር ብቻ እንደሚፈልግ ነግሮ ሸኛቸው።
የንግሱ ሾሞች ፍቅሩን ቀምተው ሳይደፍሩበት በፊትም፣ በሚስጥር ጫካ ውስጥ በተደረገ ዝግጅት አገባት። አግብቶ እንዳላገባ ሰውም ከሚስቱ ጋር በሚስጥር እየተገናኘ በፍቅር መዋኘቱን ቀጠለው። የምስኪኑ ዊሊያም ደስታ ግን ብዙም አልቆየለት። የቀድሞው ፈሪ፣ የኋላው ጀግና ዊሊያም ዋሌስ ኢ-ፍትሃዊነት በነገሰበት ምድር “እኔ አንገቴን አቀርቅሬ እና ዝም ብዬ እያረስኩ መኖር እና ቤተሰብ ማፍራት ነው የምፈልገው” ብሎ ነገር እንደሌለ ሊማር ነበር።
የእንግሊዝ ወታደሮች ሚስቱን ሊደፍሩ ሲታገሏት የደረሰው ዊሊያም፤ እያንዳንዳቸውን እያነሳ በቡጢ እያፈረጠ ጥሎ እሷን ፈረስ ላይ አስቀምጦ ጋልባ እንድትሸሽ ለማድረግ ሞከረ። እሷም ሞከረች። እሱ ወደኋላ ቀርቶ ወታደሮቹን ተዋጋ። ያመለጠች መስሎት ሄዳለች ብሎ ወደሚያምንበት ቦታ በፈረስ ጀርባ ላይ ሆኖ ገሰገሰ። ፍቅሩ ግን አልነበረችም። ኢ-ፍትሃዊነት ቀደማት።
የዊሊያም ዋሌስ የልጅነት ፍቅር እና የወጣትነት ሚስት አንድ ግንድ ላይ ተጠፍራ ታስራለች። የቅኝ አገዛዙ ሹም ከፊት ለፊቷ እየተጎባደደ ፍርሃት ስቅዞ ለያዛቸው የመንደሩ እስኮትላንዳውያን ንግግር ያደርጋል። “በንጉሱ ወታደሮች ላይ ጥቃት የሚያደርስ በንጉሱ ላይ እንደተነሳ ይቆጠራል!” ብሎ ዘወር ይልና የወጣቷን ቆንጆ አንገት በቢላዋ ሸረከተው።
ድንቄም በሰላም መኖር፤ በሰላም ማረስ፤ በሰላም ቤተሰብ ማፍራት። የዋሁ ዊሊያም ይኸኔ የት ይሆን?
የፍቅሩን መሰረቅ የሰማው ዊሊያም እየገሰገሰ ወደመንደር ተመልሷል። የቅኝ አገዛዙ ወታደሮች እመቃብሯን እንደ ወጥመድ በመጠቀም ይዘው እንደሚያስሩት በማመን አካባቢውን ከበዋል።
የሚወደውን ሁሉ ያጣውና ከዚህ ኋላ የሚኖርለት ምንም ምድራዊ ነገር እንደሌለው የተረዳው ሰው ግን እሳት ለብሶ እና እሳት ጎርሶ ከመንገዱ የቆመውን ሁሉ እየበላ ለማለፍ መጣ እንጂ እጅ ለመስጠት አልመጣም። የቅኝ ግዛቱን ወታደሮች ቄራ እንደገቡ እንስሳት የጎማመዳቸው ዊሊያም፤ የፍቅሩን ገዳይም ከግንድ አስደግፎ አንገቱን ቀላው።
ከዛን ቀን ጀምሮ ዊሊያም ፈሪው ዊሊያም ከመሆን ወደ ጀግናው ዊሊያም ተሸጋገረ። ፋስና ገጀራ ተሸክመው ሊጋፈጡት በወጡት ሃያሉ የእንግሊዝ ጦር ፊት በፍርሃት በመቅለጥ፣ መሞት አንፈልግም፣ ወደቤታችን እንመለስ በሚሉ እስኮትላንዳውያን ፊት ለፊት ቆሞ እራሱን ያገኘው ዊሊያም፤ “እሺ ሂዱ” ይላቸው ነበር። “ሂዱ፣ ግቡ ወደየቤቶቻችሁ። ሞት እንደሆን አይቀርላችሁም። ጥያቄው ምን ስትሰሩ ሞታችሁ ነው። ዛሬ ቆማችሁ ብትዋጉ፣ አዎን፣ እኔ አልዋሻችሁም፤ ትሞቱ ይሆናል። ቢሆንም ግን የምትሞቱት ነፃ ሰዎች ሆናችሁ ነው። እቤታችሁ ገብታችሁ እነሱ እስኪመጡላችሁ ወይም እንዲሁ እስክትሞቱ የምትጠብቁ ከሆነ ግን ባሮች እንደሆናችሁ ትሞታላችሁ።”
ዊሊያም ዋሌስ እስከለተ ሞቱ ድረስ ለፍትህ ቆመ። ዊሊያም ዋሌስ ሞተ። ብዙዎች ሚሊዮኖችም ሞቱ። የሱ ስም ግን ከዘመናት በኋላም በአገሩ ህዝብ ልብ ውስጥ ይኖራል፤ ይጠራል። ጀግና ዘላለማዊ ነውና።
ከዊሊያም ዋሌስ ገድል ጋር የሚመሳሰል ታሪክ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ተቆጥረው አያልቁም። አገራችን አንድ ገድሏት የማያውቅ ነገር ቢኖር የሚጋደልላት ጀግና ነው። ይሁን እንጂ የዊሊያምን ታሪክ ለመናገር የመረጥንበት ምክንያት አለን። ብዙ ጊዜ በአገራችን ስለ ጀግና ሲወራ ስለ ቀድሞ ፍርሃቱ አይወራም።
በአለማችን ታሪክ ታላቅ ገድል የፈጸሙ እና ስማቸው ዘላለማዊ የሆኑ ብዙ ጀግኖች፤ ለውጥ ወደማምጣት እርምጃቸው ከመግባታቸው በፊት፣ እርምጃውን እንዲወስዱ የተገደዱ ናቸው። “እኔ ጭቅጭቅ እና ጦርነት አልፈልግም፤ በሰላም መኖር፣ በሰላም ማረስ፣ በሰላም መነገድ፣ በሰላም ቤተሰብ ማፍራት፣ በሰላም ማስተማር እንጂ ሌላ ምንም አልፈልግም። አትንኩኝ። አትድረሱብኝ። አባካችሁ ተውኝ እኔ የናንተ ፖለቲካ አይጥመኝም።” እና የመሳሰሉትን የሚሉ ናቸው። ከዛ ሰላማቸው፣ እርሻቸው፣ ንግዳቸው፣ ትምህርት ቤታቸው፣ ስራቸው፣ ቤተሰባቸው ሲወሰዱባቸው፤ “ከፋኝ” ብለው ይነሳሉ። ከተነሱ በኋላም የሚመልሳቸው የለም።
ፍርሃት ተፈጥሯዊ የሆነ የሰው ልጅ ባህሪ አካል ነው። በተወሰነ ደረጃም አስፈላጊ ነው። ክፋቱ ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ ሰውየውን አላሰራ ሲል ነው። የዛሬ ጀግና ሁሉ የአንድ ወቅት ፈሪ ነበር። ስለፈራህ በራስህ ተስፋ ልትቆርጥ አይገባም። በውስጥህ እሳተ ገሞራ አለ።
ታዲያ የተገፋህ እለት፣ እሳተ ገሞራህ ፈንቅሎ እንደሚወጣ እናውቃለን። ያንን ማወቁም ልባችንን ያሞቀዋል። ነገር ግን እስክትገፋ የምትጠብቅ ከሆነ፣ እንደ ዊሊያም ዋሌስ የልጅነት ፍቅርህን ማጣት ማለት ሊሆን ይችላል። እናትህን፣ አባትህን፣ ክብርህን፣ አገርህን።