ብአዴን እስከመቼ በምርጥ ባርያነት ይፈነጥዛል?
ባርነት ክፉ ነገር ነው። ለጌታ በመስገድ ብዛት በተገኘ ሙገሳ መፈንጠዝ ደግሞ ከባርነትም የባሰ ነው። ባርያ ዛሬ ነፃ ባይሆንም ወደፊት ነፃ የመውጣት ህልም አለው። በጉልበተኛ ፈንጋይ ነፃነቱን ቢያጣም የህሊና ነፃነቱን ያላስደፈረ ባርያ ለሙሉ ነፃነት መታገሉ የማይቀር ነው። የባርያው ከአሳዳሪው ጋር እኩል የመሆን ህልም ትግሉ ሲሰምር እውን ይሆናል። በባርያነቱ እየፈነጠዘ ያለ ባርያ ግን ነፃ ሰው የመሆን ህልሙንም ጭምር አጥቷል። እንዲህ ዓይነቱ ባርያ በአካልም፤ በመንፈስም ባሪያ ነው። ነፃ ሰው የመሆን እድል የለውም።
አፄ ኃይለሥላሴ፣ በመጀሪያዎቹ አስርታት ዘመነ ንግሥናቸው “የባርነት አስወጋጅ ቢሮ” የሚባል ተቋም ነበራቸው። ይህ ቢሮ ገንዘብ ለጌቶቻቸው እየከፈለ ባሮችን ነፃ ያወጣ ነበር። ታድያ አንዳንድ “ታማኝ” ባሮች እቢሮው ድረስ እየሄዱ ለጌቶቻቸው ገንዘብ ካስገኙ በኋላ ባርነታቸውን ይቀጥሉ እንደነበር ሰነዶች ያስረዳሉ። ነፃ የሚወጡበትን ገንዘብ ለጌታቸው በመስጠት ተጨማሪ ገቢ አስገኝተዋልና ባሮቹ በጌቶቻቸው ይወደሱ እንደነበር መገመት ይቻላል።
እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ ዛሬ የብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) የሚገኝበት ሁኔታ ይህንን ይመስላል። ብአዴን፣ የህወሃት ምርጥ ባርያ መሆኑ ሳያንሰው በባርነቱ የሚፈነጥዝ ድርጅት ነው። ብአዴን የጌታውን፣ የህወሃትን ማለትም የመለስን ሙገሳን ለማግኘት የሚሆነውን መታዘብ ህሊናን ያቆስላል።
ሰሞኑን የብአዴን ፈንጠዚያ ወቅት ነው። ጌታው ህወሃት – በአምሳለ መለስ ዜናዊ – ባህርዳር ድረስ ሂዶ አሞግሶታል። “ጎበዝና ታማኝ ባርያ” መሆኑ ነግሮታል። ሠላሳ ሻማ ተለኩሶለት ተፍነቅንቋል። “በ1985 ተወልጄ በ2003 እንዴት ሠላሳ ዓመት ሊሞላኝ ቻለ?” ብሎ መጠየቅ አይቻለውም፤ አይገባውምም። ባርያ የሰጡትን ይቀበላል። በ30 ፋንታ 10 ዓመት ነው ቢሉትም ይቀበላል። “የኢህዴን ታሪክ ለኔ ምኔ ነው?” ብሎ አይመራመርም። መጠየቅ እና መመራመር ለባሮች የተሰጠ ነገር አይደለም። አስፈላጊው ነገር ታማኝ ባርነትን እያረጋገጡ ማብላትና መብላት፣ ማጠጣትና መጠጣት፣ ማስጨፈርና መጨፈር እና ማዘረፍና መዝረፍ ነው። የአሳዳሪው መልካም ፈቃድ ከሌለ እነዚህ ሁሉ እንደማይኖሩ ያውቃልና፤ ብአዴን “እድሉን” እየተጠቀመበት ነው።
በዚህ መሃል የአማራ ህዝብ ይታዘባል፤ ይዘግባል። “ተያንዳንዱ ቤት ስንት ስንት ተዋጣ፤ ተመንግሥትስ ካዝና ስንት ወጣ?” እያለ ገበሬው ይጠይቃል። የብአዴንን ጌቶችና አጃቢዎቻቸውን ለመጠበቅ ከትግራይ ለመጡ ዘቦችና ፊርማቶሪዎች 16 ሚሊዮን ብር ወጪ ሆኗል መባሉ፤ ለከተሞች ማሸብረቂያ አምፖሎችና ጨርቆች 5 ሚሊዮን ብር መውጣቱ፤ ለሚበላና ለሚጠጣ 30 ሚሊዮን መመደቡ፤ እንዲያው ለድግስ ብቻ ወደ 60 ሚሊዮን ብር መውጣቱ እብዙ ድሆች አማሮች ጆሮ ደርሷል። ለድግስ የወጣው ገንዘብ የአማራ ክልል ተማሪዎችን በሞላ የዓመት ደብተርና እርሳስ ይሸፍን እንደነበር በየቤቱ ይጉረመረማል። ብአዴንን ግን ይህ አያሳስበውም። ብአዴን ጌታው ያዘዘውን በመፈጸም የሚደሰት ጥርቅም ነው። “አጉርሰኝ” ሲለው ያጎርሳል፤ “ጉረስ” ሲለው በደስታና በችኮላ ይጎርሳል።
የአማራ ህዝብ ብአዴንን የመሰለ አሳፋሪ ድርጅት በታሪኩ ገጥሞት አያውቅም። በባዕድ ወረራ ጊዜ ለጣልያን ያደሩ ባንዶች እንኳን ከዛሬዎቹ ብአዴኖች የተሻለ ክብር ነበራቸው። ከዛሬዎቹም በተሻለ በጌቶቻቸው ጣሊያኖች ይሰሙ ነበር። ብአዴን ግን ራሱን ከባንዳነትም አውርዶ ባርነት ደረጃ ላይ የጣለ ከመሆንም አልፎ በባርነቱ የሚደሰት ድርጅት ነው።
ብአዴንን በተመለከተ ግልጽ ያልሆነ ጉዳይ ቢኖር አንድ ነገር ብቻ ነው። “እሱም እስከ መቼ ነው ጌታው በባርያነቱ እንዲፈነጥዝ የሚፈቅድለት?” የሚለው ጥያቄ ነው። ሁኔታዎች እንደሚያመላክቱት በወያኔ ዓይን የብአዴን ዋጋ እያሽቆለቆለ ነው። ሁሉም የይስሙላ ስልጣን ቢሆኑም አስቀድሞ ከአፈጉባዬነት ቀጥሎ ደግሞ ከመለስ ምክትልነት መባረሩ ብአዴን ለወያኔ የማይጠቅም ያረጀ ባርያ እየሆነ የመሆኑ ማሳያዎች ናቸው። ከእንግዲህ ወያኔ ይህን አሮጌ ባርያ የሚያሞካሽበት ምክንያት የለውም። የአሁኑ ቡረቃም የስንብት ይመስላል።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ብአዴንን ከአባላቱ ለይቶ ማየት ይሻል። ድርጅቱ ከባንዳም የወረደ ነፃ የመውጣት ተስፋ የሌለው ባርያ ነው። ሆኖም ግን ኅሊና ያላችሁ አባላት ካላችሁ በፍጥነት ራሳችሁን ከዚህ ድርጅት የምታላቅቁበትን አሊያም እውስጡ ሆናችሁ ድርጅቱን የምትገድሉበትን መንገድ መሻት የራሳችሁ ኃላፊነት ነው። እንኳን የብአዴን የወያኔም እድሜ አጭር እንደሆነ እንነግራችኋለን። ልቦና ያላችሁ ወደ ውስጣችሁ ተመልከቱ እንላለን።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!