አስረኛው ታላቁ ሩጫ አሁንም የህዝብ ብሶት መግለጫ ሆኖ አለፈ
የህዝብ ድምጽ እንደ ጦር የሚያስፈራው ዘረኛው አምባገነን መለስ ዜናዊ፣ በአስረኛው የታላቁ ሩጫ ዝግጅት ላይ እንዳለፉት አመታት ሁሉ የህዝብ ተቃውሞ ለመስማት መገደዱን የግንቦት 7 ድምጽ ዘጋቢ ከአዲስ አበባ ባስተላለፈው መረጃ አሳውቋል።
የታላቁ ሩጫ አስተባባሪዎች የዘንድሮው ሩጫ መግቢያ ቲኬት ገና ሳይተዋወቅ ተሸጦ አልቋል ብለው ማወጃቸው በብዙዎች ዘንድ አነጋጋሪ ሆኖ መሰንበቱን እና ዝግጅቱ በወያኔ አገዛዝ ቁጥጥር ስር ሳይወድቅ እንዳልቀረ ጥርጣሬ መፍጠሩን መዘገባችን ይታወሳል። በርካቶች አገዛዙ በሩጫው ላይ የሚገለጹትን ተቃውሞዎች ከወዲሁ ለማፈን ሲል ካድሬዎቹ ቲኬቶቹን ለደጋፊዎች እና ለፓርቲ አባላት እንዲያከፋፍሉ በጅምላ ሳይጠቀልለው አልቀረም ሲሉ ግምታቸውን ግልጸው ነበር።
በተጨማሪም፥ የሩጫው መስመር በቤተመንግስቱ እና በሌሎች የመንግስት ተቋማት ህንጻዎች በኩል እንዳያልፍ ለውጥ እንደተደረገበት ይታወቃል።
ይሁን እንጂ፥ እሁድ እለት በተካሄደው ዝግጅት ላይ በርካታ ወጣቶች ብሶታቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል። በሩጫው ሂደት ከተሰሙት መዝሙሮች እና መፈክሮች ውስጥም የሚከተሉት ይገኙበታል፡-
- “እንዴት ይረሳል? እንዴት ይረሳል? ረሳሽው ወይ፣ 97ን?”
- “ኢትዮጵያችን ሃብታም፤ እኛ ኪሳችን ባዶ፤ ቤታችን ባዶ። ባለስልጣን ሃብታም፤ በሙስና፣ በሌብነት፣ በዘረፋ…”
- “ተከብረሽ የኖርሽው ባባቶቻችን ደም፣ ባባቶቻችን ደም፤ እናት ኢትዮጵያ የደፈረሽ ይውደም፤ ወያኔ ይውደም።”
- “የመለስ ስልጣን ገደብ ይኑረው”
- “በመሳለጫ፣ በቤተመንግስት እንዳትንጫጫ”
- “ታላቁ ሩጫ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ብሶት መግለጫ”
እና የመሳሰሉት።
ከዚህም በተጨማሪ፥ ወጣቶቹ የቅንጅትን የሁለት ጣት እና የመድረክን የአምስት ጣት ምልክቶች ሲያሳዩ ተስተውለዋል። በአንድ ወቅትም ጣቶቻቸውን ወደ አራት ኪሎ እየጠቆሙ፣ “ያዝ ያዝ ያዝ” እያሉ ዘምረዋል። ዘረኛው አምባገነን የህዝብ ድጋፍ እንደሌለው ስለሚያውቅ ዜጎች አመለካከቶቻቸውን ሊገልጹ የሚችሉባቸውን መንገዶች ሁሉ ማፈኑ ይታወቃል።