አቅሙን ያወቀ ማህበረሰብ ፖለቲካዊ ተጽእኖዎችን ለማድረግ ሊንቀሳቀስ ይችላል!!!

የአለም ባንክ በቅርቡ ባደረገው ጥናት፣ ውጭ አገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው በየአመቱ የሚልኩት ገንዘብ 3.2 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ገልጿል። ይህ ቁጥር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከሚያወጣው ቁጥር ጋር እጅግ ይራራቃል። ብሔራዊ ባንክ በየአመቱ ከውጭ ኢትዮጵያውያን ተላከ እያለ የሚያወጣው ገንዘብ አንድ ቢሊዮን ዶላር እንኳ ደርሶ አያውቅም።

3.2 ቢሊዮን ዶላር ማለት የአገሪቱ አጠቃላይ ምርት አንድ አስረኛ ነው። ይህ መጠን ከምእራባውያን ከሚሰጠው እርዳታ ጋር ሲደመር፤ ከአገሪቱ የአጠቃላይ ምርት ከሃያ በመቶ በላይ ይሆናል።

በወያኔ ቁጥጥር ስር ያለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይህንን ቁጥር እጅግ አሳንሶ የሚናገርበት ምክንያት አጠያያቂ ነው። ባንኩ ወይ ደካማ የሆነ የመረጃ አሰባሰብ ዘዴ ስለሚጠቀም ነው፤ አልያም አንድ የፖለቲካ ተንታኝ ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለጹት እውነተኛውን መጠን በሌላ ፖለቲካዊ ምክንያቶች ለመግለጽ አይፈልግም።

በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለረዥም አመታት ለዘረኛውና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ የእግር እሾህ ሆነው መቆየታቸው ይታወቃል። ብዙ የተቃዋሚ ቡድኖችም፣ በተለይ ከ97ቱ ምርጫ በኋላ፣ ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ የሚልኩ ሰዎች በባንኮች በኩል በመላክ ለወያኔ የውጭ ምንዛሬ ከማቅረብ፣ ሌላ መንገድ እንዲፈልጉ ሲያበረታቱ ቆይተዋል። የዝግጅት ክፍላችንን ያናገሩት የፖለቲካ ተንታኝ እንደሚሉት፣ ይህንን ያህል ገንዘብ እየላክ ነው ብሎ በውጭ ለሚኖረው ኢትዮጵያዊ መናገር፣ ስደተኛው ማህብረሰብ አቅሙን እንዲያውቅ ያደርገዋል። አቅሙን ያወቀ ማህበረሰብ ደግሞ ፖለቲካዊ ተጽእኖዎችን ለማድረግ ሊንቀሳቀስ ይችላል።

ብሔራዊ ባንክ እውነተኛውን ቁጥር መግለጽ የማይፈልግበት ሌላም ምክንያት ሊኖረው ይችላል። የኢኮኖሚ እድገት ማምጣቱን ለማሳየት ቁጥር ከመፈብረክ ጀምሮ የማይቃጣው ነገር ለሌለው አገዛዝ፤ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የሚልኩት ገንዘብ በአገሪቱ አጠቃላይ ምርት ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ አለው ብሎ መናገር አሳፋሪ ነው። እንግዲህ የቁጥር ጫወታ የወያኔን ህልውና ከማስጠበቅ አኳያ ያለውን ከፍተኛ ስራ ላወቅን፤ ይህ ቢሆን አያስገርመንም።

የአለም ባንክ ባካሄደው ጥናት ከደረሰባቸው ግኝቶች ውስጥ ሌላው፣ 14 በመቶ የሚሆኑት ለአቅመ አዳም የደረሱ ኢትዮጵያውያን፥ በአማካይ በአመት 600 ዶላር የሚሆን ገንዘብ ውጭ አገር ከሚገኙ ዘመዶቻቸው ይደርሳቸዋል የሚል ነው። ይህ የሚያሳየን ገንዘቡ የተከማቸው በተወሰነ የማህበረሰቡ ክፍል ዘንድ መሆኑን ነው።

አገሪቱ ውስጥ ያለው ሃብትም እንደዚሁ ነው፤ በጥቂቶች ዘንድ የተከማቸ ነው።

ብዙውን ጊዜ ኢትዮጵያውያን በነፍስ ወከፍ በቀን ይህን እና ያን ያህል ዶላር ገቢ ያገኛሉ የሚሉ ቁጥሮችን እናነባለን። አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን በቀን በአንድ እና በሁለት ዶላር መካከል ገቢ እንዳላቸው የብዙ ተቋማት ግምት ነው። የአገሪቱ አጠቃላይ ምርት በህዝብ ብዛት ሲካፈል የሚገኘው የነፍስ ወከፍ ገቢ ተብዬም በአመት ከሶስት መቶ ዶላር በላይ ነው።

ይህ መጠን በአለም ላይ እጅግ ዝቅተኛ ከሆኑት ተርታ የሚመደብ እና ለአገራችን ድህነትም እንደ ማስረጃ የሚጠቀስ ቢሆንም፤ አብዛኞቻችንም በየቦታው የሚጠቀሱትን እነዚህን ቁጥሮች እንደዋዛ እያነሳን ብንደግምም፤ እውነታው ግን አብዛኞቹ ኢትዮጵያዊ ያን የተባለውን መጠን እንኳ አለማግኘታቸው ነው።

ወያኔ ሰራሹ የዋጋ ንረት ህዝቡን ከጉስቁልና ወደባሰ ሁኔታ የከተተባቸው ያለፉት አምስት አመታት ይቅሩና፤ ከዛ በፊት እንኳ ቆሎ በልተው እና በቡና እና በውሃ አወራርደው የሚውሉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር እጅጉን ትልቅ ነበር። በወር ሰላሳ ብር ደሞዝ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ብዙ ናቸው።

ከአገሪቱ ህዝብ 85 በመቶ የሚሆነውን የሚሸፍነው እና ከሄክታር ባነሰች መሬት ላይ የሚያርሰው ገበሬ በአመት አንዴ ወደ ገበያ ከሚወስደው እህል በአማካይ ከአምስት ሺህ ብር በላይ ያገኛል ቢባል ዘበት ነው። ቢያገኝ እንኳ ያን ገቢ የሚካፈለው ከቤተሰቡ ጋር ነውና፤ በቀን አንድ ዶላር የነፍስ ወከፍ ገቢ ሳይሆን የቤተሰብ ገቢ ቢሆን ምናልባት የተሻለ ያስኬዳል።

ከቁጥር ጫወታው ባሻገር፣ የአገራችን ህዝብ አሰቃቂ በሆነ ድህነት ውስጥ እንደሚኖር ግልጽ ነው። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩት እና በየአመቱ የእርዳታ ጥገኞች የሆኑት ዜጎች፤ ከረሃብ የተነሳ በየትምህርት ቤቶች እራሳቸውን እየሳቱ የሚወድቁት ህጻናት ተማሪዎች፤ ወደ ዘረፋ የዞሩት ተስፋ የቆረጡ ወጣቶች፤ እና ሌሎች በድህነት አረንቋ የሚማቅቁ ኢትዮጵያውያን ይህንን ይመስክሩ።

እንግዲህ በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በእጃቸው ያለውን መሳሪያ ተገንዝበዋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። እነሱ ዘመዶቻቸውን ለመርዳት የሚልኩት ገንዘብ ለወያኔ አገዛዝ ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሬ በመስጠት እያጠናከረው ይገኛል። በመሆኑም፥ በመንግስት እና በሌላም ህጋዊ መስመሮች ገንዘብ በመላክ የዘረኛውን አገዛዝ እጅ ከማጠናከር፤ ሌላ መንገዶችን እንዲፈልጉ ሲያበረታቱ የቆዩ ቡድኖችን ጥሪ ሊቀበሉ ይገባቸዋል። ይህ ለአገራችን እና ለህዝባችን ማድረግ ከሚገባን ሁሉ ታናሹ ነውና።