ፔትሮናስ ኩባንያ በኦጋዴን የነበረውን የነዳጅ አሰሳ መብት መሸጡ የወያኔን ውድቀት ያሳያል ሲል ኦብነግ ተናገረ
የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) ፔትሮናስ የተባለው ማሌዢያዊ ኩባንያ የኦጋዴን የነዳጅ አሰሳ መብቱን መሸጡ፣ ወያኔ በአካባቢው ያለውን ግጭት መፍታት እንዳልቻለ አመልካች ነው ሲል አውግዟል።
ፔትሮናስ ኩባንያ ለበርካታ አመታት በኦጋዴን አካባቢ የነዳጅ ፍለጋ ስራ እንዳከናወነ የታወቀ ሲሆን፤ ከበርካታ ወራት በፊት ስራውን አቋርጦ መውጣቱ ሲዘገብ የወያኔ ባለስልጣናት ፈጽመው መካዳቸው ይታወሳል። በወቅቱ ጉዳዩን የዘገቡ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን፥ ፔትሮናስ አካባቢውን ለቆ የወጣው ኦብነግ ባካባቢው ባካሄደው ተደጋጋሚ ጥቃት እና በተለይም የሂላላ የጋስ አሰሳ መስክን በመቆጣጠሩ እንደሆነ መጠቆማቸው ይታወሳል።
በዚህ ሳምንት “ሳውዝ ዌስት ኢነርጂ” የተባለ ኩባንያ ፔትሮናስ በኦጋዴን ያለውን የነዳጅ አሰሳ መብት ሙሉ በሙሉ ለመግዛት መስማማቱን በርካታ የዜና አውታሮች ዘግበዋል። “ሳውዝ ዌስት ኢነርጂ” የተባለው ኩባንያ የተመዘገበው በሆንግ ኮንግ ቢሆንም፤ ቴዎድሮስ አሸናፊ የተባለ እና በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት አሜሪካዊ የሆነ ግለሰብ የአብዛኛው ድርሻ ባለቤት እንደሆነ ለማወቅ ችለናል።
ይህንን ዜና ተከትሎ መግለጫ ያወጣው ኦብነግ፥ ወያኔ ኦጋዴንን ሙሉ ለሙሉ እንደተቆጣጠረ ለማረጋገጥ ባለመቻሉ እንደ ፔትሮናስ ያሉ የውጭ አገር ኩባንያዎች አካባቢውን ለቀው ለመውጣት ተገደዋል ብሏል። የፔትሮናስን መብት የገዛው “ሳውዝ ዌስት ኢነርጂ” የወያኔ የእጅ አዙር ኩባንያ እንደሆነ የሚጠቁመው የኦብነግ መግለጫ፤ አገዛዙ የኦጋዴንን ህዝብ የጨፈጨፈው ለዚህ ኩባንያ መንገድ ለማመቻቸት እንደሆነና የኦጋዴን ህዝብም ኩባንያውን ከወያኔ ለይቶ እንደማያየው ገልጿል።