ዘረኛው አምባገነን መለስ ዜናዊ የስኳር ምርትን በግል ለመቆጣጠር መወሰኑ ፖለቲካዊ እንድምታዎች አሉት ተባለ
ዘረኛው አምባገነን መለስ ዜናዊ የስኳር ልማት ኤጀንሲን በደርግ ዘመን እንደነበረው በኮርፖሬሽን መዋቅር ተደራጅቶ በሱ የግል ቁጥጥር ስር እንዲቀመጥ ትእዛዝ ማስተላለፉን ለአገዛዙ ቅርበት ያለው የሪፖርተር ጋዜጣ ባለፈው እሁድ ዘግቦ ነበር።
አዲስ የሚቋቋመው ኮርፖሬሽን ፊንጫ፣ ወንጂ ሸዋና መተሃራ፤ እንዲሁም በግናባታ ላይ የሚገኘውን የተንዳሆ የስኳር ፋብሪካ በስሩ ከመያዝ በተጨማሪ፤ አገዛዙ በሚቀጥሉት አምስት አመታት እገነባቸዋለሁ የሚላቸውን ሶስት ፋብሪካዎች በስሩ የሚይዝ ይሆናል።
በአሁኑ ሰዓት የስኳር ምርትን በበላይነት የሚያስተዳድረው እና ምርቱን ከፋብሪካዎች እየወሰደ ለገበያ የሚያቀርበው የኢትዮጵያ ስኳር ልማት ኤጀንሲ፤ የስኳርን ዋጋ ሆነ ብሎ ከሚገባው በላይ በማናር ለአገዛዙ ከፍተኛ ትርፍ ሲሰበስብ እንደቆየ ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል። ስኳር አገር ውስጥ ከሚያስገኘው ገቢ በተጨማሪ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ እንደሆነም ይታወቃል።
መለስ ዜናዊ ከስኳር በተጨማሪ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን በግል ቁጥጥሩ ስር እንዲሆን ትእዛዝ ማስተላለፉንም የሪፖርተር ዘገባ አሳይቷል። ጋዜጣውን ያናገረ አንድ የወያኔ ባለስልጣን፥ “የስኳርና የኢነርጂ ዘርፎች በቀጣዩ አምስት ዓመታት ግዙፍ ግንባታ የሚካሄድባቸው በመሆናቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርበት ጉዳዩን መከታተል በመፈለጋቸው ነው” ማለቱንም ለማወቅ ተችሏል።
ይሁን እንጂ በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጡን የፖለቲካ ተንታኞች፥ የመለስ ዜናዊ ውሳኔ በቅርቡ ካስተለላፋቸው የፖለቲካ ውሳኔዎች አኳያ ሊታይ የሚገባው ነው ይላሉ። እንደነሱ ገለጻ፥ አምባገነኑ ስልጣንን ሁሉ በእጁ የሚያስገቡ ውሳኔዎችን ከማንኛውም ጊዜ በላይ አጠናክሮ እያስተላለፈ ያለበት ጊዜ እንደመሆኑ እነዚህ ውሳኔዎችም ከዛ ተለይተው ሊታዩ አይገባም። ስኳር እና ኢነርጂ ቁልፍ ኢንዱስትሪዎች ቢሆኑ እንኳ መለስ ዜናዊ ሌሎችን በመመደብ ፈንታ በራሱ ቁጥጥር ስር ማድረጉ ከጊዜ ወደጊዜ የሚያምናቸው ሰዎች እያጠሩት እና ከራሱ በስተቀር በቂ የሆነ ሰው የለም የሚለው እምነቱ እየተጠናከረ መሄዱን ያሳያል ሲሉ አስረድተዋል።