የትግራይ ተወላጆች የሆኑ የገዢው ቡድን አባላት የአፋር ክልል ባለስልጣናትን እንዳሻቸው ያሳስራሉ የሚል ክስ ቀረበ
“ኦል አፋር“ የተባለው የዜና ድረ-ገጽ፣ የአፋር ክልል የንግድ፣ ኢንዱስትሪ እና ኢንቬስትመንት ቢሮ ሃላፊ አቶ ያዮ ማሂ በፌዴራል ፖሊስ ደሴ ከተማ ላይ መታሰራቸውን ዘግቦ ነበር።
ድረ-ገጹ፥ ባለስልጣኑ ትራንስፖርቴሽንን በሚመለከት በአፋር እና በአማራ ክልል መካከል የተፈጠረን አለመግባባት ለመፍታት ወደ ደሴ እንዳቀኑ እና ባቲ ወረዳ አካባቢ ሰፍሮ በሚገኘው የፌዴራል ፖሊስ ባልታወቀ ምክንያት መታሰሩን ገልጿል። የፌዴራል ፖሊስ የአፋር ክልል ባለስልጣናትን ሲያስር የመጀመሪያው እንዳልሆነ እና አቶ አደም አብዱ ሁሴን የተባለ ግለሰብ አዲስ አበባ ላይ ሙስና ውስጥ ገብተሃል በሚል በፌዴራል ፖሊስ መታሰሩን ገልጿል።
ይሁን እንጂ ለዝግጅት ክፍላችን መረጃ የላኩ ግለሰብ የወያኔ አገዛዝ እውነት በአፋር የሚካሄድን ሙስና ለማስቆም ቢፈልግ በክልሉ ያሉ ባለስልጣናት በሙሉ ሊታሰሩ ይገባል ያሉ ሲሆን፤ ግለሰቦቹ የሚታሰሩበት ምክንያት የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የወያኔ ባለስልጣናትን ጥቅም የሚነኩ ውሳኔዎች ባለማወቅ ሲያስተላልፉ ነው ብለዋል። የአፋር ታርጋ የያዙ መኪናዎች በአማራ ክልል ውስጥ እንዳይንቀሳቀሱ ተከልክሎ ነበር ያሉት ግለሰብ፤ አቶ ያዮ ማሄም በተራቸው የአማራ ክልልን ታርጋ የያዙ መኪናዎች ወደ አፋር ክልል ገብተው አገልግሎት እንዳይሰጡ እንደ ጊዜያዊ እርምጃ መወሰናቸውን ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ የአማራ ክልል ታርጋ ይዘው በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ አብዛኞቹ ተሽከርካሪዎች የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የመከላከያ ባለስልጣናት ንብረቶች እንደሆኑ እና አቶ ያዮም በአማራ ክልል ላይ እርምጃ የወሰዱ መስሏቸው ሳያውቁ ጉልበተኛ ባለስልጣናትን እንዳስቆጡ ገልጸዋል። ፌዴራል ፖሊስ አቶ ያዮን ያሰረው በነዚህ ባለስልጣናት ቀጥተኛ ትእዛዝ ነው ሲሉም ከሰዋል። በሙስና ምክንያት ታሰሩ የተባሉት ግለሰብም ለአገዛዙ ቅርበት ያለውን የንግድ ሰው ጥቅም የሚነካ ውሳኔ በማስተላለፋቸው ነው ሲሉ የመረጃ ምንጩ ይናገራሉ።