የውጭ ምንዛሪ ለውጡ እውነተኛ ምክንያቶች እና መውሰድ የሚኖርብን እርምጃዎች

(Ginbot 7) — ወያኔ በድንገት የብርን የምንዛሬ ምጣኔ በ20 በመቶ እንዲቀንስ አድርጎ ቀድሞ በ13.62 የኢትዮጵያ ብር ይመነዘር የነበረው አንድ የአሜሪካ ዶላር በብር 16.35 እንዲመነዘር አዟል። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ እንደ ወታደራዊ ተቋም በትዕዛዝ የሚመራ በመሆኑ ለምንዛሪው ምክንያት መጠየቅ ያለበት መለስ ዜናዊ እንጂ የባንኩ ገዢ ወይም “ቦርድ” የተባለው ስብስብ አይደለም። የባንኩ ገዢም ሆነ ቦርዱ አስፈፃሚዎች እንጂ ወሳኞች አይደሉም። የገንዘብንም የበጀትንም ፓሊሲዎች የሚቀርፀው ወይም እንደተመቸው የሚጫወትባቸው መለስ ዜናዊ እንደሆነ አገር ያወቀው ጉዳይ ነው። እናም መለስ ዜናዊ ይኸን ድንገተኛ የምንዛሬ ለውጥ ያደገረባቸውን እውነተኛ ምክንያቶችን ማወቅ ይጠቅማል።

ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ባደረገው መጠነኛ ምርምር እና ስለወያኔ ባህርይ ካለው እውቀት በመነሳት የውጭ ምንዛሪው ለውጥ እውነተኛ ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሷል።

  1. ፈጣን ዘረፋ – ይህ ከፍተኛ የምንዛሪ ለውጥ ድንገተኛ የሆነው ለተራው ኢትዮጵያዊ እንጂ ለወያኔ ባለሥልጣኖች እንዳልሆነ እኛ በተጨባጭ የደረስንበት ጉዳይ ነው። የምንዛሪው ለውጥ ከመደረጉ ጥቂት ቀናት በፊት ጀምሮ ወያኔ “አሜሪካ ገንዘብዋን ልትቀይር ነው” የሚል ውዥንብር በማስወራት የዋሁ ነጋዴ የያዘውን የውጭ ገንዘብ እንዲቀይር ገፋፋው። የወያኔ ባለሥልጣኖችና ተላላኪዎቻቸው ደግሞ በጎን በስፋት ወደ ገበያ የቀረበውን የውጭ አገር ገንዘብ ሸመቱ። ግዢው ሲጠናቀቅ ትዕዛዙ ተላለፈና በአንድ ጊዜ ሃብታቸው በ20 ከመቶ እንዲያድግ ተደረገ። እንዲህ አይነት መሰሪ ተግባር በዘራፊነታቸው በታወቁ መንግሥታት ዘንድ እንኳን አስፀያፊ ተግባር ነው፤ ለወያኔ ግን ብልህነት ነው።
  2. “ተወዳዳሪነትን ማሳደግ” – ወያኔ ለም መሬት የመሸጥ ፉክክር ውስጥ ገብቷል። ቻይና መንግሥቷ እራሱ ነጋዴ ሆኖ መሬት እየሸመተ ነው። ህንድና ሌሎች አገራት ደግሞ የመሬት ግዢውን እንዲያጧጡፉ የየሃገራቸው ቱጃሮችን እያበረታቱ ነው። አፍቅሮተ-ንዋይ የማስተዋያ አዕምሮዓቸውን የሰለበባቸው የአፍሪቃ አገሮች ገዢዎች “ከእኔ ግዙኝ፤ ከእኔ ግዙኝ” በሚል ፉክክር ውስጥ ገብተዋል። ወያኔ ለባዕዳን ለም መሬትን በሄክታር በአስር ዶላር እየሸጠ ቢሆንም ከዚህም በታች በማውረድ “ተወዳዳሪነቱን” ከፍ ለማድረግ ታጥቆ ተነስቷል። የቡናና የጫት የወጪ ንግድ እና የማዳበሪያና የመድሃኒት የገቢ ንግዶች በምንዛሪ ለውጥ ምክንያት እጅግም እንደማይለወጡ የታወቀ ጉዳይ ነው። ለወያኔ በብር መርከስ ምክንያት የሚፋፋ ንግድ ያለው የመሬት ሽያጭ ብቻ ነው። እናም ወያኔ የብር ምንዛሪ በመቀነስ የኢትዮጵያን ለም መሬት በሳንቲሞች በመቸርቸር ለባህዳን አስረክቦ እማንወጣው ማጥ ውስጥ ሊያስገባን አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ነው።
  3. ከድሃው ወደ ሃብታም የሚጎርፈው የሃብት ፍሰትን ማሳለጥ – አሁን የተደረገው የምንዛሬ ለውጥ ብዙም ጊዜም ሳይወስድ የአገር ውስጥ ዋጋዎችን ማስጨመሩ አይቀርም። በዚህም ምክንያት ለጥቂት ጊዜዓት ጋብ ብሎ የነበረው የዋጋ ግሽበት ይቀሰቀሳል። የዋጋ ግሽበት ደግሞ የወያኔ ጥብቅ ወዳጅ ነው። የዋጋ ግሽበት ድሃው የሚያጠራቅመውን ገንዘብ ስውር በሆነ መንገድ እወያኔ ኪስ ውስጥ ይከትለታል። በዋጋ ግሽበት ምክንያት ሃብቱን በኢትዮጵያ ብር ያስቀመጠ ይከስራል፤ የኢትዮጵያ ብርን የተበደረ ደግሞ ይከብራል። በዛሬዋ ኢትዮጵያችን ውስጥ ሃብት በብር – ለዚያው በትናንሽ ብሮች – የሚያስቀምጠው ድሃው ነጋዴና የመንግሥት ሠራተኛው ነው፤ በሚሊዮኖች የሚበደረው ደግሞ “ልማታዊ ባለሃብት” እየተባለ የሚቆላመጠው ወያኔ፣ የወያኔ ወዳጅ አልያም የወያኔ ወገንተኛ ነው። እናም የሰሞኑ የምንዛሪ ለውጥ ሃብትን ከድሃው ሀገርተኛ ወደ ወያኔው ሃብታም ሲያሸጋግር የነበረው የዋጋ ንረት እንዲቀሰቀስ ታስቦ የተደረገ ነው።
  4. የትላልቅ ቁጥሮች ፍቅር – ወያኔ ትላልቅ ቁጥሮችን ይወዳል፤ ለህልውናው ያስፈልጉታልም። በውሸት የተሞሉ የቁጥር ቁልሎች የእርዳታው ምንጭ ናቸው። የብርን አንፃራዊ ዋጋ በ20 ከመቶ በመቀነስ የ15 በመቶ ዓመታዊ እድገት ህልሙን የማሳካት እቅድ አለው። ከዚህ አንፃር ሲታይ ይህ የምንዛሪ ለውጥ “የአምስት ዓመት የትራንስፎርሜሽን እቅዱ” አካል ነው። ዋጋዎች ሲጨምሩ ቁጥሮችም ይጨምራሉ። ወረቀት ላይ እስከታየ ድረስ እድሃው ማዕድ ላይ እድገቱ ባይታይም ዓለም ባንክን እምብዛም አይጨንቀውም።

እኛ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

ወያኔ በኢትዮጵያዊያንና በኢትዮጵያ ላይ እንዲጨፍር እስከፈቀድንለት ድረስ እንዲህ የረቀቁ የዘረፋ ዓይነቶችን በመፈልሰፍ ማስደመሙን ይቀጥልበታል። የወያኔን የዘረፋ ጥበብን እየተከታተሉ ማጋለጥ ተገቢ ቢሆንም ዋነኛ ሥራችን መሆን ያለበት ግን በሁለገብ ትግል ወያኔን ፊት ለፊት ገጥሞ ማዳከም ብሎም ማስወገድ ነው።

ግንቦት 7 ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ እንደገለፀው ሁሉ በውጭ አገራት የሚገኘው ኢትዮጵያዊ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ባለመሆን ብቻ እንኳን ወያኔን ማስጨነቅ ይችላል። የወያኔ ማባበያዎችን ተቀብለው ሃብታቸውን ወደ ኢትዮጵያ ያሻገሩ ወገኖች ዛሬ አባብለው በወሰዷቸው ሰዎች ተንኮል የንብረታቸው 20 በመቶ ማሙቷል። ይህ የምንዛሪ ለውጥ የመጨረሻው እንዳማይሆን ከወዲሁ ማስጠንቀቅ እንወዳለን። ወያኔ ጥቅም እስካገኘበት ድረስ ደግሞ ብርን ማዳከሙን ይቀጥልበታል። ወያኔ ለራሱ ካልሆነ በስተቀር ለማንም ደንታ የለውም። ይህን ከልብ ከተረዳን ደግሞ ዘላቂ መፍትሄዎች ላይ ማትኮር ይኖርብናል።

በግንቦት 7 እምነት ዘላቂው መፍትሄ በተባበረ ክንድ ወያኔን ማስወገድ ነው። ለዚህ ወሳኝ ትግል ሁላችንም በጋራ እንነሳ!!!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!