የኛ “ትራንስፎርሜሽን ፕላን” ኢትዮጵያን ከዘረኝነት ማጽዳት ነው
(Ginbot7.org) — አንድን ነገር ደጋግሞ እየሠራ የተለየ ውጤት የሚጠብቅ አዕምሮው በትክክል የማይሠራ ሰው ብቻ ነው ይባላል። ወያኔ አዕምሮዓቸው በትክክል መሥራት በማይችል ሰዎች የተሞላ ድርጅት መሆኑ ድርጊቱ ይመሰክራል። ባለፉት አምሳ ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ ሲደረግ የቆየው በባዶ ቁጥሮች በተነፋ እቅድ የመኩራራትን “ስልት” ዛሬ እነ ግርማ ብሩ እንደ አዲስ ጥበብ ያስተዋውቁን ይዘዋል። የወያኔ የሰሞኑ ማደንቆሪያ “አዲሱ” የአምስት ዓመት እቅድ “ትራንስፎርሜሽን ፕላን” በመባል ፈረንጅና ስም እንዲኖረው ከመደረጉ በስተቀር በይዘትም ሆነ በቅርጽ ከድሮዎቹ የባሰ እንጂ የተሻለ ነገር የለበትም።
የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እቅድ ታሪክ መለስ ብሎ ለተመለከተ በተመሳሳይነታቸው መገረሙ አይቀርም። ሁሉም ወረቀት ላይ የሚጮኹ ናቸው። ሁሉም የየጊዜው ባለሥልጣኖች ጉራቸውን ነዝተውባቸዋል። ይሁንም እንጂ አንዳቸውም እናሳካለን ያሉትን ግማሹን እንኳን ተግባራዊ አላደረጉም። በተለይም ባለፉት ሠላሳ አመታት እቅዶቹ ብቻ ሳይሆን አቃጆቹም አልተቀየሩም። ለምሳሌ ግርማ ብሩ፣ መኮንን ማንያዘዋል እና ሱፍያን አህመድ የደርግ ማዕከላዊ ፕላን ባለሥልጣናት በነበሩበት ጊዜ በአየር ላይ የተንሳፈፉ እቅዶችን እየነደፉ ስለፈጣን ልማት አይቀሬነት “በደርግኛ” ሲተነትኑ ነበር። ዛሬ ያው የሰለጠኑበትን የውሸት እቅድ “አጠናክረው” “በወያኔኛ” መተንተን ተያይዘውታል። እነዚሁ ሰዎች የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ውስጥ ስለመሆኑ ቢያንስ በሶስት የተለያዩ ጊዜያት ተናግረዋል። የመጀመሪያው የደርግን የአስር ዓመት እቅድ ሲያስተዋውቁ የተናገሩት ሲሆን፤ በዘመነ ወያኔ ደግሞ ይኸ ሁለተኛ ጊዜዓቸው ነው። ዘወትር ተግባራዊነቱ የማይታይ “የመዋቅራዊ ለውጥ እቅድ” አጋፋሪዎች ሆነው መቅረታቸው ህሊናቸውን አይኮሰኩሰውም። “እናመጣለን ብላችሁት የነበረው እድገት የታል?” ብሎ የጠየቃቸው ስለሌለ ውሸትን ከመለማመድ አልፈው ከአጥንትና ሥጋቸው ጋር አዋህደውታል። ይብዛም ይነስ ያላቸውን የአካዳሚና የአስተዳደር እውቀት እየቀለበ ለሚጋልባቸው አምባገነን ሁሉ መጠቀሚያ አድርገውታል። እናም አሁን ለበለጠ ውሸት ተበረታተው ቀርበዋል። ከእነዚህ ሰዎች የተሻለ የአድርባይነት ህያው ተምሳሌት ከየት ይገኛል?
አሁን የታወጀው “የትራንስፎርሜሽን እቅድ” በዘፈቀደ ከተሞሉ ቁጥሮች በስተቀር መሬት ባለ ሃቅ ላይ ላለመመሥረቱ በርካታ ጥያቄዎችን በማንሳት ማረጋገጥ ይቻላል። “ምን ተደርጎ ነው ኢኮኖሚው በአንድ ጊዜ እንዲህ የሚመነደገው?” የሚለው ጥያቄ መሠረታዊ ነው። ማንም እንደሚረዳው የአገር ኢኮኖሚ በአንድ ምሽት በቅሎ የሚያድር እንጉዳይ አይደለም። ለእንጉዳይም ቢሆን ደመናና ካፊያ ያስፈልገዋል። አሁን እየተነገረን ያለው እድገት ምንጩ እምን ላይ ነው? ይህ ጥያቄ በተደጋጋሚ ተነስቶ መልስ ባለማግኘቱ ወደ ሌሎች ጥያቄዎች እናልፋለን። ወያኔዎች እንዲህ በቀላሉ መመንደግ እንደሚቻል እያወቁ ምነው እስከዛሬ ተንቀረፈፉ? ለምንድነው ባለፈው አምስት ዓመት የታቀደውን ግማሽ ያህል እንኳን ሰብል ያልተሰበሰበው? ከ16. 7 ሚሊዮን ቶን ወደ 38.21 ሚሊዮን ቶን እናሳድጋለን ተብሎ ታቅዶ 18.08 ሚሊዮን ቶን ላይ ሲቆም ማን ተጠየቀ? ለምንድነው የኢንዱስትሪው ድርሻ 16.5 ከመቶ ይሆናል ተብሎ ታቅዶ ድሮ ከነበረበት 13.6 ከመቶ ወደ 13 ከመቶ ያሽቆለቆለው? ባለፉት አምስት ዓመታት ያልሰራው እቅድ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት እንደሚሠራ በምን ተገመተ? ጥያቄዎቻችን ብዙ ናቸው። የአፋር ክልል አምስት ሚሊዮን ተማሪዎችን አስመዘገበ እያለ ከሚቀደድ የዋሾዎች ቡድን እርባና ያለው ምላሽ ይገኛል ተብሎ ስለማይጠበቅ ጥያቄዎቻችንን እዚሁ ላይ ማብቃቱን መርጠናል።
አንድ ሃቅ ግን አጽንዖት ሊሰጠው ይገባል። ይህም “የአምስት ዓመቱ የትራንስፎርሜሽን ፕላን” የውሸት ክምር መሆኑ ነው። ከውሸትነቱ በተጨማሪ ግን ይህ እቅድ ከዚህ በፊት ከነበሩት ሁሉ የበለጠ ለኢትዮጵያ አደገኛ ነው። ይህንን በመጠኑም ቢሆን ዘርዘር አድርጎ ማየት ይበጃል።
ወያኔ በዘር የተከፈለች ሁለት ኢትዮጵያዎችን ፈጥሯል። አንደኛዋ ኢትዮጵያ የወያኔዎችና የምስለኔዎቻቸው ነች። ይህች አገር ሃብታምና በከፍተኛ ፍጥነት እያደገች ያለች ናት። የዚች አገር ዜጎች ቁጥር ከጥቂት መቶ ሺዎች አይበልጥም። ሌላኛዋ ኢትዮጵያ 80 ሚሊዮን ያህል እንሆናለን ተብሎ የምንገመተውን የያዘችው ምስኪኗ እማማ ኢትዮጵያ ናት።
ሃብታሟ ኢትዮጵያ በዓመት 3.3 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር እርዳታ ስለምታገኝ በዓመት 15 በመቶ ማደግ ያንሳታል። እርግጥ ነው እርዳታ የሚመጣው በድሃዋ ኢትዮጵያ ስም ነው። ይሁን እንጂ የሃብታሟ ኢትዮጵያ “ምርጥ” ዜጎች አንዱ በተቋራጭነት፣ ሌላው በእቃ አቅራቢነት፤ አንዱ በደላላነት፣ ሌላው በአስፈፃሚነት ቢሊዮኖቹን ዶላሮች ይከፋፈሉታል። የውጭ እርዳታ እና “በምርጥ ዜጎች” መካከል ያለው የሃብት ክፍፍል እንዲቀጥል መንገዶች መሠራት፤ ግድቦች መገንባት አለባቸው – አለበለዚያማ ምን በምን ሰበብ ሊወሰድ ኖሯል?
በከተሞች አዳዲስ ፎቆችና ቪላዎች መገንባታቸውም እሙን ነው። ሆኖም አሁንም እነዚህ ፎቆችና ቪላዎች የእነማን ናቸው ብሎ መጠየቅ ያሻል። መልሱም ቀላል ነው – ንብረትነታቸው የሃብታሟ ኢትዮጵያ ዜጎች ነው። በድሆች መንደር ውስጥ የዱባይ ህንፃ መንትያዎች ቢገነቡ የመበላለጣችን እንጂ የመልማታችንን መጠን አያመለክቱም።
የሃብታሟ ኢትዮጵያ ዜጎች ሃብት በአገር ውስጥ ብቻ አይደለም ያለው። እነዚሁ ሰዎች በአውሮፓ፣ በአሜሪካ እና በአረብ አገሮች የሚንቀሳቀሱና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን እያከማቹ ነው። አዜብ መስፍን፣ ስብሃት ነጋ፣ ሳሞራ የኑስ፣ ገዛኢ አበራ፣ አርከበ እቁባይ፣ አባይ ፀሃዬ፣ አባዱላ ገመዳ፣ ኩማ ደመቅሳ እና መሰሎች በውጭ አገራት ያከማቹት ሃብት በመቶ ሚሊዮኖች የአሜሪካ ዶላሮች የሚገመት ነው።
የአብዛኞቻችን ኢትዮጵያ ግን እያደር እየከሳችና እየገረጣች ነው። የአብዛኞቻችን ኢትዮጵያ በድህነት፣ በበሽታ፣ በማይምነት፣ በፍትህ እጦት ዓለምን ትመራለች። ዜጎቿ አገር ለቀው እንዳይወጡ በር ተዘግቶባቸው የሚገኙ እስረኞችና ግዞተኞች ናቸው። ይህች ኢትዮጵያ በቅራኔዎች ተወጥራ ልትፈነዳ ደርሳለች። የሁለተኛዋ ኢትዮጵያ ዜጎች መሬት በአንደኛ ኢትዮጵያ ዜጎች እየተነጠቁ ገበሬዎች ለቀን ሠራተኝነት እንኳን የወያኔ አባልነት ፎርም በመሙላት ተገዢነታቸውን እንዲያረጋግጡ የሚገደዱባት አገር ናት።
ታድያ የሶፍያን አህመድና ግርማ ብሩ “የትራንስፎርሜሽን ፕላን” የየትኛዋ ኢትዮጵያ እቅድ ነው? ሃብታሟ ኢትዮጵያ “ትራንስፎርም” ከሆነች ቆይቷል፤ ደግሞ 15 ከመቶ ያንሳታል። የኛዋ ኢትዮጵያ ግን ስለምን እየተነገረ እንደሆነም አይገባትም። እሷ በሰቆቃ፣ በእልህና በቁጭት ተሞልታ ለውጥን በማማጥ ላይ ያለች ናት። ስለ “ኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን” ለመቀለድ ጊዜም ፍላጎትም አቅምም የላትም።
“የአምስት ዓመት የትራንስፎርሜሽን ፕላን” ነፋስ ላይ የቆመ በመሆኑ ከግርግር በስተቀር መሬት ላይ የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም። ሆኖም ከሌሎች ተመሳሳይ እቅዶች ይኸኛው የከፋ የሚያደርገው በሌሎች አገሮች እርዳታ በትንሹ እንኳን ቢሳካ ጥቂት ዘረኞችን ጠቅሞ አብዛኛዎቻችንን የሚጎዳ መሆኑ ነው። ይህ ደግሞ ለማናችንም አይበጅም።
ኢትዮጵያ በሁለት ተከፍላ መቆየት አትችልም። “ትራንስፎርም” መደረግ ያለበት እውነታ ይህ ነው:: የኛ ትራንስፎርሜሽን ፕላን ዘረኝነትን በማጥፋት ኢትዮጵያን የሁሉም ዜጎቿ የእኩል አገር ማድረግ ነው። ይህ ደግሞ ይቻላል፤ እናደርገዋለንምም!!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!