በኢትዮጵያ የረሃብ መንስኤ ድርቅ ሳይሆን አምባገነናዊ መሪዎች ናቸው ተባለ
በኢትዮጵያ የሚከሰተው ተደጋጋሚ ረሃብ መንስኤ የዝናብ እጥረት ሳይሆን መሪዎች ናቸው ሲሉ ዊሊያም ኢስተርሊ የተባሉ ታዋቂ ኢኮኖሚስት ተናግረዋል።
ሚስተር ኢስተርሊ “ዘ ዋል ስትሪት ጆርናል” ለተባለው ታዋቂ የአሜሪካ ጋዜጣ በፃፉት ጽሁፍ፥ “የአምባገነናዊ መሪዎቻቸውን ያህል ድርቅ ኢትዮጵያውያንን አልጎዳም” ብለዋል። ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ሁኔታ ከደርግ ጊዜ አምብዛም አልተለወጠም ያሉት ኢኮኖሚስት፤ ምእራባውያን በረሃብ የተጎዱ ኢትዮጵያውያንን የሚረዱ እየመሰላቸው የረሃቡ መንስኤ የሆኑትን አገዛዞች በእርዳታቸው እያጠናከሩ እንደሆነ አስረድተዋል።
ጨምረውም፥ ምእራባውያን ከ1997ቱ ምርጫ በኋላ እርዳታቸውን በቀጥታ ለፌዴራሉ መንግስት ከመስጠት ይልቅ ወደ ወረዳዎች ቢያዞሩም አገዛዙ ያንንም የመንግስት መዋቅር የሚቆጣጠር በመሆኑ ይህ ለውጥ ምንም ተጽእኖ አላሰደረበትም ብለዋል። በኢትዮጵያ ላለው የግፍ አስተዳደር ጀርባ እየሰጡ ዝም ብሎ እርዳታ መስጠት ምንም ጥቅም አያስገኝም በማለት ኢኮኖሚስቱ ጽሁፋቸውን ደምድመዋል።