የብር ዋጋ መውደቁን ተከትሎ የተፈጠረው የዋጋ ግሽበት ሸማቾችን ማስደንገጡ ታወቀ

በወያኔ ቁጥጥር ስር የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባላፈው ሳምንት በአንድ ዶላር ዋጋ ላይ የ20% ጭማሪ በማድረግ ወደ 16 ብር ከ35 ሳንቲም ማሳደጉ ይታወሳል።

ይህንን ተከትሎ የተፈጠረው የዋጋ ግሽበት ሸማቾችን ማስደንገጡን የደረሰን ዘገባ አመልክቷል። የግንቦት 7 ድምጽ ዘጋቢ በአዲስ አበባ በመርካቶ አካባቢ ተዘዋውሮ እንደተመለከተው፥ የስሚንቶ ዋጋ በ10 ብር የጨመረ ሲሆን፣ ለህንፃ ግንባታ የሚውል ብረት ዋጋም በኪሎ ግራም ሁለት ብር ጨምሯል። አዲስ ነገር ኦንላይን የተባለው የዜና ድረ-ገጽም በተለያዩ ቁሳቁሶች ላይ የዋጋ ጭማሪ መደረጉን ዘግቧል።

የአዲስ አበባ ምንጮቻችን እንደገለጹት፥ የዋጋ ግሽበቱ በሸማቾች ላይ መደናገጥን እና አለመረጋጋትን ፈጥሯል። ብዙዎችም ተጨማሪ ግሽበት እንዳይፈጠር በመስጋት በብዛት ሲሸምቱ ተስተውለዋል።