የወያኔው አገዛዝ የአምስቱ አመት የኢኮኖሚ ልማት ትራንፎርሜሽን እቅድ የህልም እንጀራ ነው ሲሉ ታዋቂ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች አጣጣሉት

በቅርብ ቀን ይፋ የሆነው የአምባገነኑና ዘረኛው መለስ ዜናዊ የአምስት ዓመታት የልማት ግብ ርቆ የተሰቀለ ዳቦ ወይንም የህልም እንጀራ ነው እየተባለ መተቸቱን የገለጸው የቪ ኦ ኤ ው አማርኛ ክፍል በአምስት አመቱ የልማት መርኃ ግብር ዙሪያ በሀርፐር ዩኒቨርስቲ የኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑትን ዶ/ር ጌታቸው በጋሻውንና በአለም ባንክ ከ30 አመታት በላይ በከፍተኛ አማካሪነት የሰሩትና በኢትዮጵያ ድህነትን ለማጥፋት የሚቻልበትን መንገድ የሚያመላክት መጸሃፍ በቅርቡ ለንባብ ያበቁትን ዶ/ር አክሎግ ቢራራን አነጋግሯል።

ቀደም ብሎ አምባገነኑ መለስ «አስር ከመቶ እናድጋለን ስንል እንደ እብድ ታይተን ነበር እኛ ግን ከዚያም በላይ አሳክተናል ፤ ከዚህ በላይ ከሰራን ደግሞ የበለጠ ውጤታማ እንሆናለን፤ ልምዱና አቅሙ አለን » ማለቱን አስመልክቶ አስተያየታቸውን የተጠየቁት ኢኮኖሚስቶቹ በሰጡት መልስ የስካሁኑ የኢትዮጱያ የእድገት አሃዝ በርካቶችን እያወዛገቡ ይገኛሉ ካሉ በኋላ የማንኛውም ሃገር በሰባትም ይባል በ11 ነጥብ እድገት አሳይቻለሁ ሲል ይህ አባባል ሁሌም ከሀዝብ ኑሮ መሻሻል ጋር ሊታይ ይገባዋል ብለዋል። በመቀጠልም እድገት በጥቂት የኢኮኖሚ ዘርፎች ሊመዘገብ ይቺላል ነገር ግን የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ መሰረት ምንድነው የሚለው ጥያቄ በጣም መሰረታዊና አንገብጋቢ የሆነ ጥያቄ ነው ካሉ በኋላ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ደግሞ በግብርና ላይ የተመሰረተ ነው፤ ስለግብርና ስናወራ ደግሞ ትንንሽ የሆኑ አምራቾችን ይመለከታል። ስለሆነም ስለ እድገት ስናወራ እነኝህ ወገኖች ኑሮአቸው ተሻሽሏል ወይስ እንደዚያው ነው፣ ማነቆዎች አሉባቸው ወይንስ የሉባቸውም የኑሮ ውድነት ከፍ ብሏል ወይንስ ዝቅ ብሏል? የሚሉትን ልንመዝን ይገባናል ብለዋል። ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ አብዛኛው ህዝብና ገበሬ ኑሮ እንደተመዘገበው እድገት ተሻሽሏል ለማለት አመላካች የሆኑ መረጃዎች የሉም፤ በምንም አይነት ልንክደው የማንቺለው ነገር ከ6 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ስር በሰደደ የውጪ ርዳት ድጋፍ እንዳሉ ተደጋግሞ ተነግሯል፤ ባለፈው ዓመት ኦክስ ፋም ባቀረበው ሪፖርት ደግሞ ከ13 ሚሊዮን የማያንስ ህዝብ ረሃብተኛ ነው ተብሏል። በመሆኑም እንቆቅልሹ ለግብርናው ዘርፍ እድገት አሳይቷል ሲባል መጋቢ የሆነው አስተዋጾ የሚያደርገው ክፍል ይሄው አርሶአደር በመሆኑ መሰረታዊ የማዋቅር ለውጥ ተደርጓል የሚለው ነገር ፉርሽ ይሆናል ማለት ነው ብለዋል።

የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎቹ በሌላም በኩል የአምስት ዓመቱ የትራንስፎርሜሽን እቅድ በአምስት ዓመት ኢትዮጵያን ከተረጂነት ለማላቀቅ ፍጹም አይቻልም፤ ተአምራዊ የሚባሉ ግኝቶች ካልተፈጠሩ በስተቀር የሚባለውን ለማመን ያዳግታል። ፈጽሞ ከውነታ የራቀ፤ በሃገሪቱ ያሉትን ነባራዊ ሁኔታዎች ያላገናዘበ፤ በዓለም ደረጃ ራሱ በጣም እያደጉ ናቸው የሚባሉ እንደ ቻይናና ህንድ ያሉ ሃገራትን ብንወስድ እነመለስ ዜናዊ አስመዘገብን የሚሉት 11 .5 % እድገት እንዴት ሊሆን እንደቻለ፤ በተለይም ዓለማቺን አሁን ካለቺበት የኢኮኖሚ ድቀት አንጻር ኢትዮጵያ በተጠቀሰው እድገት መጠን አደገች ሲባል መለኮታዊነትን የያዙ ይመስላል እንጂ ሊያሳምን የሚችል ነገር የለውም ብለዋል። በመጨረሻም ከመንግስት የሚቀርቡት ዴታዎች (መረጃዎች) በፍጹም ተአማኒነት ያሎአቸው አይደሉም፤ ኢትዮጵያ ከዓለማችን በድህነት ሁለተኛ በህዝብ ብዛቷ ደግሞ ከአፍሪካ ሶስተኛ ሆና እያለች በምን አይነ ተአምር ይህ የታሰበ እቅድ እንደሚሳካ አይገባንም በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የግንቦት ሰባት የፍትህ የነጻነትና የዴሞክራሲ ንቅናቄ ሳምንታዊ ረሰ አንቀጾቹን ጨምሮ በተለያዩ ፕሮግራሞቹ ይህ የወያኔ ሪፖርትም ሆነ እቅድ ምንም መሰረት የሌለውና መራባዊያንን ለማማለል የታቀደ እንጉርጉሮ እንደሆነ በተደጋጋሚ መግለጹ ይታወቃል።