አንድ መቶ የአለም አገራትን የኑሮ ሁኔታ ያነፃፀረ አዲስ ሪፖርት ኢትዮጵያን 94ኛ ደረጃ ላይ አስቀመጠ
ታዋቂው የአሜሪካ ጋዜጣ ኒውስዊክ “ዛሬ ብትወለድ፥ የትኛው አገር በጤና፣ በደህንነት፣ በብልጽግና፣ እና በእድገት የተሞላ ኑሮ እንዲኖርህ ከፍተኛውን እድል ይሰጥሃል?” የሚለውን ጥያቄ ይዞ በመነሳት መቶ አገሮችን አነፃጽሮ ደረጃን ያወጣ ሲሆን ከነዚህ መቶ አገሮች ውስጥም ኢትዮጵያን 94ኛ ደረጃ ላይ ያስቀመጣት መሆኑን ለማወቅ ተቺሏል።
ኒውስዊክ ትምህርትን፣ ጤናን፣ የኑሮ ጥራት ደረጃን፣ የኢኮኖሚ ተወዳዳሪነትን፣ እና የፖለቲካ ሁኔታን እንደማነፃጸሪያ ነጥቦች የተጠቀመ ሲሆን ለምሳሌ የኑሮ ጥራት ደረጃን ለመመዘን ከተጠቀመባቸው ቁልፎች ውስጥ አንዱ “በቀን ከሁለት ዶላር በታች” የሚያገኙ ዜጎች ቁጥር ሲሆን፤ ከዛ አኳያ ኢትዮጵያ ውስጥ 77.57% የሚሆነው ህዝብ ያንን ገቢ እንደሚያገኝ አስቀምጧል። ይህ የኒውስዊክ ሪፖርት አገራቱን ለማነፃጸር የተጠቀመው መረጃ እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር 2008 እና 2009ን የሚሸፍን መሆኑ ታውቋል።
በእንግሊዝ አገር የሚገኘው ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ከተበባሩት መንግስታት ጋር በመተባበር ከአንድ ወር በፊት ባወጣው ሪፖርት ላይ “መልታይ ዳይሜንሽናል ፑቨርቲ ኢንዴክስ” የተባለ ዘርፈ ብዙ የድህነት መመዘኛ በመጠቀም የአለም አገራትን አወድድሮ፤ ኢትዮጵያ ከአፍሪካዊቷ ኒጀር ቀጥላ ሁለተኛዋ የአለም ደሃ አገር እንደሆነች እና 90% የሚሆኑት ዜጎቿም በድህነት እንደሚማቅቁ መግለጹን መዘገባችን ይታወሳል።