የትግራይ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ታሰሩ
ተሰናባቹ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት በሐምሌ ወር መጨረሻ ጉባዔው ባደረገው ግምገማ፣ የክልሉን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ አቶ ኃይለ አብርሃን ከሥልጣናቸው ካነሳቸው በኋላ እንዲከሰሱ ወሰነ፡፡ በአሁኑ ወቅት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ከተለያዩ ምንጮች ለማወቅ ተችሏል፡፡
ምክር ቤቱ አደረገ በተባለው ጥልቀት ያለው ግምገማ፣ ላለፉት በርካታ ዓመታት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሆነው የቆዩት አቶ ኃይለ፣ የዳኞችን ነፃነት በመጋፋት፣ የፍትሕ ሥርዓቱን ባለማስከበራቸውና የተለያዩ የሕግ ጥሰቶችን መፈጸማቸው በግምገማው ላይ ተወስቷል፡፡
ፕሬዚዳንቱ በሙያ ብቃታቸው የታወቁና የሥነ ምግባር ችግር ያልነበረባቸውን ዳኞች ከተቋሙ እንዲፈልሱ በማድረግና ብቃት የሌላቸውንና የሥነ ምግባር ችግር ያለባቸውን ግለሰቦች በመሾም ኃላፊነታቸውን ላልተፈለገ ዓላማ መጠቀማቸው በግምገማው ላይ ተነስቷል፡፡
አቶ ኃይለ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውስጥ ሙስናና ብልሹ አሠራረ ሲፈጽሙ እንደነበር በማስመልከት በቀረቡ ሐሳቦች ላይ በምክር ቤቱ ጉባዔ ሰፊ ጊዜ ተሰጥቶባቸው ውይይት እንደተካሄደባቸው ምንጮች ገልጸዋል፡፡
የምክር ቤቱ ጉባዔ ፕሬዚዳንቱ ከኃላፊነታቸው ተነስተው ፈጽመውታል የተባለው ሙስናና ብልሹ አሠራር በአስቸኳይ ተጣርቶ ለሕግ እንዲቀርቡ በሙሉ ድምፅ መወሰኑ ታውቋል፡፡ ምንጮች እንደጠቆሙት፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ ኃይለ አብርሃ ከሥልጣናቸው ተነስተው በአሁኑ ወቅት በቁጥጥር ሥር ይገኛሉ፡፡ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች እንደሚሉት፣ በአሁኑ ጊዜ አስፈላጊ የሆኑ ማስረጃዎች ተሰባስበው ጉዳዩ ለፍርድ ሒደት በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ፣ ምርጫ 2002ን ተከትሎ በትግራይ ክልል የተለያዩ ከተሞች ግምገማዎች ተጀምረዋል፡፡ በተለይም በአድዋ ከተማ የተካሔደው ሕዝባዊ ኮንፈረንስና ግምገማ በርካታ የከተማው ሥራ አስፈጻሚ አባላት ከኃላፊነታቸው ያስነሳ ሲሆን፣ ኃላፊዎቹ ፈጽመዋቸዋል የተባሉ ሙስናዎችና ብልሹ አሠራሮች ተጣርተው ለሕግ እንዲቀርቡ መወሰኑን ከሥፍራው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
በከተማው ማዘጋጃ ቤት ተቀጥረው ሲሠሩ የቆዩ ከአሥር በላይ መሐንዲሶችም በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ከአካባቢው ምንጮች ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡
ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የከተማው ሠራተኞችና ነዋሪዎች እንደገለጹት፣ ግምገማው የተካሔደው የአድዋ ከተማ ከንቲባ አቶ ዓርአያ መርዕድ የአድዋው ንግስተ ሳባ ትምህርተ ቤት የቀድሞ ተማሪዎች በአሜሪካ ባካሄዱት የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ላይ ለመገኘት ወደዚያ አቅንተው ስለነበሩ፣ እሳቸው ባልነበሩበት ወቅት ነው፡፡
በግምገማው ወቅት የከተማው አስተዳደር ማዘጋጃ ቤት ኃላፊዎችና መሐንዲሶች በጋራ ስፋቱ በውል ያልታወቀ፣ በተለይም ለኮንዶሚኒየም ግንባታ ሳይቀር የተከለለ የመንግሥት መሬት ለግለሰቦች መስጠታቸው ተነስቷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እነዚህ ኃላፊዎች በከተማው ውስጥ በነዋሪነት በማይታወቅ ግለሰብ ስም እስከ 150 ሺሕ ኩንታል ሲሚንቶ ከመሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ በማውጣት ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸውም ተነግሯል፡፡
የግምገማው ተሳታፊዎች እንደገለጹት፣ ኃላፊዎቹ የትምህርት ማስረጃ የሌላቸው ግለሰቦችን ሕጋዊ ባልሆነና ዕውቅና ባልተሰጠው ማስረጃ እንዲቀጠሩና ዘመድ አዝማዶቻቸውን ካላግባብ የተለያዩ ጽሕፈት ቤቶች ኃላፊዎች እንዲሆኑ አድርገዋል፡፡ እንዲሁም ቀደም ሲል የከተማው አስተዳዳር ይጠቀምበት የነበረን የኪራይ ሕንጻ እንዲለቅ በማድረግ፣ የይዘትና የመጠን ልዩነት የሌለውን ሕንጻ ቀድሞ ከሚከፈለው የኪራይ ዋጋ በሦስት እጥፍ ጨምረው በመከራየታቸው፣ ሆን ብለው ግለሰቦችን አላግባብ ለመጥቀም ሲሉ የመንግሥትና የሕዝብ ገንዘብ እንዲባክን ማድረጋቸው በግምገማው ተሳታፊዎች ቀርቧል፡፡
በእነዚህና በመሰል ምክንያቶች የከተማው ማዘጋጃ ቤትና የንግድና ኢንዱስትሪ ጽሕፈት ቤት ኃላፊን ጨምሮ አምስት የሥራ አስፈጻሚ አባላት ከሥልጣናቸው እንዲነሱ፣ የፈጸሙት ሙስናና ብልሹ አሠራርም ተጣርቶ ለሕግ እንዲቀርቡ የግምገማው ተሳታፊዎች መወሰናቸው ታውቋል፡፡
የአድዋ ከተማ ከንቲባ አቶ ዓርአያ መርዕድ ከሄዱበት አሜሪካ የተመለሱ ሲሆን፣ በክልሉ መንግሥት ገለልተኛ አጣሪ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጉዳዩን እስኪያጣራ ድረስ በኃላፊነታቸው ላይ እንዲቆዩ መወሰኑን የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
ግምገማውን በተመለከተ የተገኘው የሕዝብ አስተያየት እንደሚያሳየው፣ የተደረገው ግምገማና ውጤቱ አስደሳች መሆኑን፣ ነገር ግን ግምገማው በየአምስት ዓመት ወይም በተወሰነ ጊዜ ብቻ ሳይሆን መካሄድ ያለበት፣ የየቀኑን የሥራ አፈጻጸም መሠረት ያደረገና ቶሎ ቶሎ መሆን እንዳለበት ነው፡፡