ጠ/ሚኒስትሩ እንዴት ቀልድ ጨምሯል ጃል!
ይነጋል በላቸው
በቤቴ ኢቲቪ አይከፈትም። ከወያኔ ጋር ንክኪ ያለው ሬዲዮም እንዲሁ። ትክክል እንዳልሆንኩ ይገባኛል። ምን ላድርግ? ስለሚያመኝ እኮ ነው፤ ወድጄን መሰላችሁ? ይህቺን አልፎ አልፎ የምሞነጫጭራትን ነገር እንኳን የማቀራስመው ባብዛኛው በስማ በለው ከማገኘውና ከውጭ ሚዲያዎች ከምከታተለው ነው። ይሁንና እኔ አልሰማም ብልም ሰው እያመጣ ሳልወድ በግዴ ይነግረኛል። እምቢ አልል ነገር ከሰው ጋር ነው የምውል። ጓደኞቼ እየተናደዱ ትናንት ማታ ‘እገሌ እንዲህ አለ፤ እገሊት እንዲህ አለች’ ሲሉ ስለምሰማ አንዳንዴ እቤቴ አለማዳመጤን ሳስበው አልሸሹም ዘወር አሉ ዓይነት ነገር ይሆንብኛል። ጠበል ሄጄ ትግስቱን እንዲሰጠኝ ልለማመን ይሆን?