በቫንኩቨር የኢትዮጵያዊያን የክርምት ፌስቲቫል ደምቃ ዋለች

በቫንኩቨር ካናዳ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው የኢትዮጵያ የክረምት ፌስቲቫል ከአሁን ቀደም ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በፖለቲካ በሀይማኖትና በተለያዩ የማህበራዊ ችግሮች ምክንያት ተራርቆ የነበረው ነዋሪ በሙሉ በአንድ ላይ በመሰባሰብ በደማቅ ሁኔታ መከበሩ ታወቀ።

በፌስቲቫሉ ላይ የቫንኩቨር ነዋሪዎችን ጨምሮ ከአምስት ሺህ በላይ ከሲያትልና ከካልጋሪ የመጡ ኢትዮጵያወያን፣ አሜሪካዊያንና ካናዳዊያን የተመለከቱት ሲሆን በከተማዋ ተወልደው ያደጉ ታዳጊ ወጣቶችና ህጻናቶች ያቋቋሙት ውቢት ኢትዮጵያ የሴቶች የሙዚቃ ክለብ በተላያዩ ባህላዊና ዘመናዊ ዘፈኖች ታዳሚውን ሲያዝናኑ ቆይተዋል። በቦታው የካናዳና የፊሊፒን የባህላዊና ዘመናዊ ሙዚቀኞች እንዲሁም ወጣት የራፕና የሬጌ ሙዚቃ ተጨዋቾችም በተለይ ወጣቱን ክፍል ሲያዝናኑ ቆይተዋል።

ይሄው በኢትዮጵያ ማህበረሰብ አስተባባሪነት በርናቢ በሚባለው ክፍለ ከተማ በተካሄደው ፌስቲቫል ላይ የበርናቢ ከተማ ከንቲባ ሚስተር ዴሪክ ኮሪጋንን ጨምሮ የኤን.ዲ.ፒ ፓርቲ የአካባቢው የህዝብ ተመራጮችና ታዋቂ ፖለቲከኞች አቶ ራጅ ቹሀንና የሰው ልጆችን መብት በማስከበር የሚታወቀውና የብርቱካን ሚዴቅሳን መፈታት በካናዳ ፓርላማ በማንሳት ዘወትር እንድትፈታ የሚወተውተው የፓርላማ ተመራጭ ሚስተር ፒተር ጁሊያን በእንግድነት ተገኝተው ንግግር አድርገዋል።

በብሪቲሽ ኮሉምቢያ ማህበረሰብ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ከበደ ሀይለማሪያም ጋባዥነት የማህበረሰቡ ፕሬዝዳንት ተክለሚካኤል አበበ የካናዳን ህዝብ መዝሙር ከህጻናቶች ጋር በማዘመር ንግግሩን ከፍቶ፡ ስለኢትዮጵያ ታሪካዊነት ጥቂት ከጠቀሰ በኋላ ካናዳ ለኢትዮጵያዊያን የመከራ ጊዜ መጠለያ በመሆኗ ምስጋላውን አቅርቧል።

ሚስተር ራጅ ኢትዮጵያዊያኖች ትልቅ ታሪክ ያላቸውና በአፍሪካ ቅኝ ግዛትን በመከላከል የሚታወቁ ታላቅ ህዝብ መሆናቸውን ገልጸው ለማናቸውም የመንግስት ስራዎች ቢሯቸው ለኢትዮጵያዊያን ክፍት መሆኑን ገልጸዋል። በፌስቲቫሉ ሌላው ተናጋሪ የነበሩት ሚስተር ፒተር ሲሆኑ ከኢትዮጵያዊያኖች ጋር ያላቸውን ትስስር አውስተው በእስር ላይ የምትገኘው ዳኛ ብርቱካን ሚደቅሳ መፈታት አለባት ብለው “Birtukan Must be released” ለዚህም ቀን ተሌት እንሰራለን ሲሉ በአጽንኦት ገልጸዋል።

በፌስቲቫሉ ላይ የከተማው ኢትዮጵያዊ በሙሉ ነቅሎ እንዲወጣ ኮሚቴው ከስድስት ወር በላይ መስራቱን የገለጹልን የፌስቲቫሉ አስተባባሪዎች ከዚህ በኋላ ፌስቲቫሉ በየአመቱ እንደሚካሄድና ኢትዮጵያዊያን ባህላቸውን፣ ፖለቲካቸውን፣ ታሪካቸውንና ሀይማኖታቸውን ለማስተዋወቅ አንድ ተጨማሪ ዴሞክራሲያዊ መድረክ እንደተከሉ ተናግረዋል።

በፌስቲቫሉ ላይ ከሰላሳ በላይ የአካባቢው የንግድ፣ የሀይማኖትና የሲቪክ ድርጅቶች እንዲሁም ከአምስት በላይ የሙዚቃ ቡድኖች የተሳተፉ ሲሆን በቫንኩቨር ከተማ የምሽት ክለብ DJ ዎች ውድድር ሁለተኛ በመውጣት የተሸለመው DJ BZ BLACK (አሉላ) እና አትክልት አሰፋ የውጭ ሀገርና የሀገር ቤት ሙዚቃዎችን በማሰማትና መድረኩን በማስተባበር (master of ceremony) በመሆን ህዝቡን ሲያዝናኑ ቆይተዋል።