የመድብለ ፓርቲ ዕጣ በኢትዮጵያ!

«መድበለ ፓርቲ ከ2002ቱ ምርጫ በኋላ አብቅቶለታል፤» የሚሉ ወገኖች «ኢትዮጵያ ወደ አንድ ብቸኛ ፓርቲ አገርነት እያመራች ነው፤» ሲሉ፤ ይሄን የሚከራከሩት ደግሞ «ሊባል የሚችለው፤ ኢትዮጵያ አብላጫ ድምፅ ባገኘ ጉልህ ፓርቲ እየተመራች ነው፤» ይላሉ።

«የአንድ ፓርቲ በተቀባይነት ጎልቶ መውጣት ወይስ የአንድ ፓርቲ ብቸኛ ሁሉን አድራጊነት?» በግራና ቀኝ የሚሰሙ የሁለት ወገን ጥያቄዎች ናቸው።

የገዢውን የኢህአዴግ ፓርቲን በመደገፍና በመቃወም በሁለት ጎራ የተሠለፉ ተከራካሪዎች፥ «መድብለ ፓርቲ፤» በኢትዮጵያ ያለውን ዕጣ አስመልክቶ እሰጥ አገባ ገጥመዋል።

የግንቦቱን የኢትዮጵያ ብሄራዊ የምርጫ ውጤት ተከትሎ፥ በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከምርጫው በኋላ ዛሬ ያላቸው ድርሻና ሊጫወቱ የሚችሉት ቀጣይ ሚና በአንድ ወገን፤ የምርጫውን ውጤት ሙሉ ሊባል በሚችል ድምፅ የወሰደው ገዢው ኢህአዴግ ቢያንስ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት አገሪቱ የምትጓዝበትን አቅጣጫና መዳረሻ በሁሉም መልኩ የመወሰን ሥልጣኑ፤ ያለው አቅምና ችሎታ፤ እንዲሁም የፖለቲካ ዕይታ ለሁለት ወገኑ ክርክር መነሻ ሆኗል።

የእሰጥ አገባ ተከራካሪዎች በሁለት ተቃራኒ ጫፎች የቆሙ ይመስላል። ያድምጧቸው።