የፍርሃት ግንብ ይፍረስ! በአንዱዓለም አራጌ

ይችን አጠር ያለች ፅሁፍ ለመፃፍ ያነሳሳኝ ከአንድ የቅርብ ጓደኛዬ ጋር የነበረኝ አጭር ጭውውት ነው፡፡ ጓደኛዬ አዘውትሮ ታክሲ ይጠቀማል፡፡ እናም በቅርቡ የታክሲ ሂሳብ ጭማሪ ተግባራዊ በሆነበት የሳምንቱ መጀመሪያ ዕለት የተለመደውን የታክሲ ደንበኝነቱን ቀጥሏል፡፡ ይሁን እንጂ ከታሪፉም በላይ የታክሲ ረዳቱ ሂሳብ ይቆርጥበታል፡፡ በዚህ የበገነው ጓደኛዬ እንደምንም ተሟግቶ ሳንቲሙን ካስመለሰ በኋላ አንድ ዐረፍተ ነገር አክሎ ይሰነዝራል፡፡ ‹‹የታክሲ ሂሳብ ሲጨምር ሰልፍ አለመውጣቴም በጣም ፈሪ በመሆኔ ነው›› ይለዋል፡፡ ታክሲው ጥርቅም ብሎ ሞልቷል፡፡ ከኋላ ተጣብቆ የተቀመጠ በግምት የኢህአዴግ አባል በመንግስት ላይ ሰልፍ መውጣት እንደሌለበት፣ እርሱ ደግሞ ፈሪ ባይሆን ኑሮ እንዴት መውጣት እንዳለበት ይከራከራሉ፡፡ ሌላው ተሳፋሪ ፀጥ ረጭ ብሏል፡፡ ታክሲው ይቆምና ሌላ ሰው ይገባል፡፡ ይኸም በግምት የኢህአዴግ አባል ወይንም ደጋፊ ነው፡፡ ቢያንስ እንደ ጓደኛዬ አስተያየት፡፡ ድንገት ሲገባ የሁለቱን ተሳፋሪዎች የጋለ ውይይት ሲሰማ ውይይቱ ስለምን እንደሆነ ለመረዳት ለራሱ ዕድል መስጠትን አልከጀለም፡፡ ‹‹አባይን ነው እንገድበዋለን፤ የምታመጡት አንዳች ነገር የለም›› ይላል፡፡ ሌላው ተሳፋሪ ሁሉ አንገቱን ሰብሮ ይነጉዳል፡፡ ሁለቱ የኢህአዴግ አባላት ወይንም ደጋፊዎች በደመ-ነፍስ ተግባብተው በደመ-ነፍስ ተቀባበሉት፡፡ ተሳፋሪዎች እንደተከዙ የኢህአዴግ ደጋፊዎች ወይንም አባላት ሌክቸር እየሰጡ ጉዞ ቀጥሏል፡፡ እንዲሁ እያለ ጓደኛዬ ከታክሲ በመውረድ ከሁለቱ ሰዎች ውኪ ደብልቂ እፎይ እንዳለ አሰበ፡፡ ጓደኛዬ እንደነገረኝ፡፡

ይህን መሰል የብዙሃን ኢትዮጵያውያን አርምሞ የጥቂቶች የስርዓቱ ተጠቃሚዎች ሽለላ ለአለፉት 20 የግዞት ዓመታት አዘውትረን ያስተዋልነው ጉዳይ ነው፡፡ ትንሽ ቀዝቀዝ ያሉት ባያጋጥሙት ኑሮ ተከራክረው መርታት ሲሳናቸው እንደተለመደው በሽጉጥ ለመርታት ሽጉጥ ማውጣታቸው የማይጠበቅ አይደለም፡፡ ተደጋግሞ የተከሰተ ነው፡፡ ሰሞኑን በአንድ ነዳጅ ማደያ ውስጥ አሁንም የኢህአዴግ አባል እንደሆነ የሚታመን ሰው ነዳጅ ሞልቶ ሲጨርስ መኪናው ውስጥ ሰነድ እንደጠፋበት ይረዳል፡፡ ቀጣዩ እርምጃው ነዳጅ ማደያ ውስጥ ያሉ ሰራተኞችን የሚያበራ ሽጉጡን በማውጣት እየቀጠቀጠ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ይወስዳቸዋል፡፡ ሕግ አስከባሪ ፖሊስ መጥራት ሳያስፈልገው፡፡ በሌላ ቀን ከተደብዳቢዎቹ አንዱ ፖለቲካው አካባቢ የሚታወቅ ጓደኛዬን ያገኝና ‘ለመሆኑ ቅኝ ግዛት ማለት ከዚህ ይከፋል ወይ’ ብሎ ይጠይቀዋል፡፡ ምላሹ ምን እንደሆነ እንተወው፡፡ ይህ የተፈፀመው ያውም በመሃል አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና በምትባለው ከተማችን ነው፡፡ በገጠሩ የሃገራችን ክፍልማ ለመከራከር ማን እድሉን ሰጥቶት፣ ይኸን የሚያደርግ ጀርባው ላይ ጅራፍ ወይ አጠና ያላረፈበት ከከተማ ወደ ገጠር ዘመድ ለመጠየቅ የሄደ ለዛውም ደፋር የሚባል አይነት ሰው መሆን አለበት፡፡ እሱም ቢሆን ሙከራውን ይሞክር እንጂ ሽመል፣ ጅራፍ፣ አሊያም ሰደፍ ጀርባው ወይንም ጥሰሩ ላይ መቅመሱ አይቀርም፡፡ ‹‹የማን አባቱ ደፋር ቢሆን ነው?››

በኢትዮጵያችን የገጠሩ ክፍል አካባቢ ምንም ያጣ የነጣ ደሃ ቢሆን 18 ዓመት የሞላው ወንድ ልጅ የመንግስት ባለሥልጣንም ይሁን አንቱ የተባለ ሃብታም አርጬሜ እላዩ ላይ ሊያሳርፍ ፈፅሞ አይችልም ነበር፡፡ እኔ እንደማቀው፡፡ አሁን አንድ ካድሬ መቶ ገበሬዎችን በጅራፍ እንደ በግ ሲነዳ ማየት ግርምት የሚያጭር ጉዳይ አይደለም፡፡ የሚያሳዝነው ኢህአዴግ አንዴ ሰው በላው ሌላ ጊዜ አረመኔ በሚለው በደርግ ስርዓት ወቅት እንኳን የገጠሩ ነዋሪ ኢትዮጵያዊ ስብዕና እንዲህ በዘመኑ ካድሬዎች እንደሚደረገው መሬት ላይ ተጥሎ ሲረገጥ አላየውም፡፡ ‹‹እንዲህ ነው እንጂ በሕዝብ የተመረጠ፣ ለሕዝብ የቆመ ዲሞክራሲያዊ መንግስት ማለት፡፡››

የገዥዎቻችንም ሆነ የአጠቃላይ ፖለቲካዊ ስነ-ልቦናችን በዋናነት ከዘመነ-መሳፍንት የተቀዳ ይመስለኛል፡፡ ዘመነ-መሳፍንት ብዙ የተነገረለት ዘመን በመሆኑ ብዙዎቻችን ለታሪኩ እንግዳ አንሆንም ብየ አምናለሁ፡፡ ዘመነ-መሳፍንት ከነገስታቱም ከመሳፈንቱም በላይ ጥይት የነገሰበት ዘመን ነበር፡፡ ያለ አፈሙዝ ለውጥ፣ ያለ አፈሙዝ ድል የሚታሰብ አልነበረም፡፡ የዛኑ ያህል የሃገር ጥቅም፣ የሕዝብ መብት በድንገትም ቢሆንም ወደ ገዥዎች አዕምሮ የሚመጣ ጉዳይ አልነበረም፡፡ የህዝብ ዋና ሚና የሚታዘዘውን መፈፀም ነበር፡፡ ለጦር ሲጠራ መዝመት፤ ዘማች እንዲያበላ ከታዘዘ ማብላት እንጂ፡፡ ነገስታቱ እና መኳንንቱ ምን ገዷቸው፣ ገንዘብ ሲጠየቅ ገንዘብ፣ ሕይወት ሲጠየቅ ሕይወት የሚሰጥ ሕዝብ እያለ፡፡ ለዛውም አንዱ ኢትዮጵያዊ የሌላውን ተከታዬች ጨርሶ በሌላው ላይ ድል ለመቀዳጀት፣ ብሎም ሕዝብን ረግጦ ለመግዛት ለሚፈፅመው የዕልቂት ተግባር፡፡ በዘፈኖቻችን እንደሚወሳው አንዱ የሌላውን የሠራዊት አባላት ለመጨረስ የሚፈልገው ጀግና ወይንም ደፋር ስለሆነ አይደለም፡፡ ነገር ግን በዋናነት በውስጣቸው ያለውን የስልጣን ጥም ለማርካት እና ፍርሃታቸውን ለማስታገስ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ የአንዱ ወገን ትንሸ አቅም ለሌላው ወገን ገደል የሚያክል ስጋትም ስለሚፈጥርም ነበር፡፡ የዘመነ-መሳፍንት ተዋናዬች ፍርሃትና የስልጣን ጥም የወለደው የአምባገነንነት ባህሪም ሰለባዎች ነበሩ፡፡ ሌላው መገለጫቸው ደግሞ ሕዝብን እንደሚረግጡት ቅጠል መቁጠር ነው፡፡ በተለያየ ወገን ተሰልፎ ሲጫረስ ለሚቀጠፈው ሕይወቱና ለሚፈሰው ደሙ ቅንጣት ደንታ አልነበራቸውም፡፡ ነገር ግን አብዛኛዎቹ የእነርሱ እጣ የደረሰ ከመሰላቸው ግን ተሰባብረው ገደል ሊገቡ ይችላሉ፡፡ ውስጣቸው የፍርሃት ምስጥ እንደበላው ግንድ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ አብዛኛዎቹ፡፡

ከላይ አለፍ አለፍ ብለን የገለፅናቸውን ጥቂት የዘመነ-መሳፍንት አምባገነኖች ባህሪያት ከአሁኖቹ ጋር ለማመሳሰል ብዙ መድከም ያለብን አይመስለኝም፡፡ በግልፅ ሊቀመጡ የሚችሉ መመሳሰሎች ስላሏቸው፡፡ ለእኔ ጓድ መንግስቱም ሆኑ ጓድ መለስ የፈፀሙትንና አሁን ጓድ መለስ እየፈፀሙ ያሉትን ግፍ ግዝፈት ሳይ በዘመነ-መሳፍንት ጊዜ ቢፈጠሩ ምን ያህል ከዚያ ዘመን አምባገነኖችም በላይ ሊሆኑ እንደሚችሉ እገምታለሁ፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው በጣም አምባገነን እየሆነ ሲሄድ የፍርሃቱ መጠንም የዛንኑ ያህል ሁለንተናውን እየተቆጣጠረው መሄዱ እርግጥ ነው፡፡ ስለዚህ የፈሪዎችም ቁንጮ መሆናቸውን ማስተዋል አያዳግትም፡፡ ያ ባይሆን በርሃብ የተቆራመደ ሕዝብ ላይ ሌላ ግፍ መፈፀም ባላሻቸው ነበር፡፡

የአሁኖቹ ገዥዎቻችን ዘመነ-መሳፍንትን ፍንትው አድርገው የሚያሳዩን መስታውቶች ናቸው፡፡ የፖለቲካ ባህላቸንም ቢሆን አንዱ የሌላው ዘመን መስታወት ነው፡፡ ሕዝቡም ቢሆን በዛን ወቅትም አሁንም የውጭ ወራሪዎችን ለመመከት ብሎም የሃገሩን ዳር ድንበር ለማስጠበቅ ለሕይወቱ እንኳን ሳይሳሳ ዋጋ የሚከፍል ጀግና የሚለው ስም የሚያንስበት ሕዝብ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ዳር ድንበርን ከማስጠበቅ አንፃር ካየነው፡፡ እንቆቅልሹ ግን ሁልጊዜም አምባገነን መሪዎቹ በሚፈጥሩት የአፈና መረብ ተተብትቦ በጭቆና ስር ለዘመናት እየማቀቀ መገኘቱ ነው፡፡ ውስጣዊ ነፃነቱን ለማረጋገጥ አለመቻሉ፡፡

በእርግጥ ገዥዎች ሕዝብ በሚከፍለው ግብር ልክ ተቃዋሚዎችን ይቅርና ሌላውን የኑሮ ማዕበል የመታውን ሕዝብ ለመሰለል በወገኑ ላይ የሚሰማራ ‹‹የደህንነት›› ሠራዊት ማሰማራታቸው አይካድም፡፡ በተለይ አሁንማ በርካታ ሚሊዬን ዶላሮችን የሚጠይቀው የቻይና የደህንነት ቴክኖሎጅና ለዚህ ተብለው የሚሰለጥኑት ‹‹ልጆቻችን›› ቁጥር ከጊዜ ጊዜ እጅግ አሻቅቧል፡፡ ይህ ሁሉ ፍርሃት የወለደው ሃላፊነት የጎደለውና የአምባገነኖች መቋጫ የሌለው የአፈና መዋቅር ነው፡፡ ይህም ሁሉ ሆኖ ፍርሃትን አሜን ብለን እንድንቀበል በቂ ምክንያት ሊሆነን አይችልም፡፡ ሌላ ፍርሃት ሊዘራ ይገባዋልን? በሕዝብ ላይ የሚዘራ ፍርሃትስ እስከመች ይዘልቃል? አምባገነኖችንስ ከፍርሃት ይታደጋቸዋል? የፍርሃት ማህበረሰብ ፈጥሮስ አገርን እንዴት አስተባብሮ ማልማት ይቻላል? እኒህ የመሠሉ ጥያቄዎች መነሳታቸው አይቀርም፡፡ በእርግጥ መልሶቻችን አሉታዊ ናቸው፡፡ ገዢዎቻችንም ፍርሃታቸው ባሰባቸው እንጂ ከፍርሃት ሲያገግሙ አላየንም፡፡ ወደፊትም ቢሆን ከሚነዳቸው የፍርሃት ጎርፍ ፍርሃት እራሱ መድህን ሊሆናቸው አይችልም፡፡ ነፃነት በሌለበት ልማት አለ እንኳን ከተባለ የባሮች ልማት ነው የሚሆነው፡፡ የአምባገነኖች ፍርሃትና መዘዙ ከዘመነ-መሳፍንተ እስከ አሁን ድረስ እየፈሰሰ ነው፡፡ ድህነትና ጭቆናውም እንዲሁ፡፡

ፍርሃት በፈሪነት አይገደብም፡፡ ጭቆናም በአርምሞ አይወገድም፡፡ ስነቃሎቻችን ስለድፍረት /ደፋርነት ብዙ ብለዋል፡፡ አሁን ድረስ እንኳን ‹‹ገዳይ እወዳለሁ ያልገደለ አልወድም አብሬው ስተኛ ይመስለኛል ወንድም$፣ #ገዳይ እወዳለሁ ገዳይም አልጠላ፡ ሲደክመኝ አርፋለሁ ከጎፈሬው ጥላ፡፡$ የሚሉና ሌሎች አያሌ ገዳዮችን እንደ የወንድ ሚዛን አድርገው የሚወስዱ ስነ-ቃሎችና ግጥሞች በሃገራችን አብዝተው ይስተዋላሉ፡፡ እነ አቶ መለስ በምርጫ 97 ወቅት በተለይ የኢትዮጵያውያንን ደረት እና ግንባር እየነጠሉ ግዳይ በየታዛውና እና በእየአደባባዩ ሲጥሉ የጠቀስኳቸው አይነት ግጥሞች በእዝነ-ልቦናቸው ሳያቃጭሉባቸው አይቀሩም፡፡ ፍርሃታቸው ሳይታከል ማለቴ ነው፡፡ ጥያቄው እነዚህን መሰል ስነ-ግጥሞችምና አይን ያወጣ ጭፍጨፋ ከፍርሃት ታደጓቸው ወይንስ አባባሱባቸው የሚለው ነው፡፡ ተግባራቸው ጥሩ አድርጎ ይናገራል፡፡ በምርጫ 97 ዋዜማ የነበሩ የድል መንገዶችን ሁሉ አዳፍነው፣ ፍርሃትና የውርደት አዘቅት ውስጥ እየዳከሩ ይገኛሉ፡፡

ከዕለት ወደ ዕለት ኑሮውን ለማሸነፍ ደፋ ቀና በሚል ሕዝብ ላይ አፈ-ሙዝ ወድረው የዛፍ ላይ እንቅልፋቸውን ይኮመኩማሉ፡፡ እንደ ዘመነ-መሳፍንት ሁሉ ዛሬም ሉአላዊነቱ የአፈ-ሙዝ ነው፡፡ በተግባር በኢትዮጵያ ምድር ሉአላዊ ግለሠብም ሆነ ሉዓላዊ ሕዝብ የለም ምንአልባት አቶ መለስ ብቸኛው ሉዓላዊ ግለሰብ ናቸው ማለት ይቻል ይሆናል፡፡ ዛሬም ስልጣን ከአፈ-ሙዝ እንጂ ስልጣን ከድምፅ መስጫ ኮረጆ ሲመጣ ለመታዘብ አልታደልንም፡፡ ዛሬም እንደዘመነ-መሳፍንት ኤርትራም ሆነ ሶማሊያ ሄዶ ለመሞት የአጤዎች የእልህ ፍልሚያ ወይንም ስልጣን ላይ ተንሰራፍቶ ለመዝለቅ ማለም ብቻ በቂ ነው፡፡ የሕዝብ ዕጣ-ፈንታ ገንዘብ ሲጠየቅ ከየትም ብሎ ማዋጣት፤ ሂድና ሙት ሲባል ሄዶ መርገፍ ነው፡፡ ልክ እንደ ዘመነ-መሳፍንት፡፡ ለምን ብሎ መጠየቅ፣ ችግሩን ማመላከትና ለሚለፈፈው ሁሉ የገደል ማሚቱ ላለመሆን መሞከር የነፍጠኛ ርዝራዝ፣ ያለፈው ስርዓት ናፋቂ፣ የጥፋት ሃይል ወይንም የሻቢያ እና የግብፅ መንግስት ጉዳይ አስፈፃሚ መሆን አለበት እንደ ኢህአዴግአዊያን ገዥዎቻችን፡፡ ስለታክሲ ሂሳብ ውይይት ሲደረግ አባይን እንገድብዋለን ብሎ እንደአቅራራው ግለሰብ፣ በደመነፍስ የተሞሉትን መተንፈስ ነው፡፡ ከተሞሉት ውጭ ከመጣ ማገናዘብም ሳያስፈልግ ማውገዝ ነው፡፡ መፈረጅ፡፡

የፍርሃት ምንጩ በዋናነት አምባገነኖች ከሕዝብ እምነትና ፈቃድ ውጭ ሕዝብን ረግጠው ለመግዛት የሚያደርጉት መውተርተር ነው፡፡ በኢፍትሃዊነት ላይ የተመሠረተ ተግባር ፍርሃትን መቀፍቀፉ የተለመደ ነው፡፡ ፍርሃት ደግሞ ወየውልህ ለሚባለውም ሆነ ለነጋሪት ጎሳሚው እፎይታን አያጎናፅፍም፡፡ ይልቅስ የጭቆና ቡልኮና የፍርሃት ቆፈንን እንጂ፡፡ ከፍርሃት ነፃ መውጣትን የመሰለ ትልቅ ከፈጣሪ የተቸረን ፀጋ የለም፡፡ በእኔ አስተያየት፡፡ ከፍርሃት ነፃ ስለመውጣት ስናወራ አነዱ ሌላውን ወንድሙን እንዲረግጠው አሊያም ሕይወቱን የማጥፋት ባህልን ያዳብር እያልን አይደለም፡፡ ይህን መሰሉን መንገድ ለብዙ ዘመን ይዘነው መጥተን አሁንም አቶ መለስ መዳፍ ውስጥ እንደ ቆሎ እንድንታሽ የበኩሉን አስተዋፆ እያበረከተ ነው፡፡ ፍርሃትን ድል መንሳት ማለት ፍትህን መቀበል ማለት ነው፡፡ ወይንም ፍትሃዊ ያልሆነውን ሁሉ ደግሞ አንገትን ቀና አድርጎ መጋፈጥ ማለት ነው፡፡

የምርጫ ካርድ መዝረፍ ፍትሃዊ አይደለም፡፡ የመገናኛ ብዙሃንን እንዳይሰማ ሕዝብን ማፈን በምንም መንገድ ፍትሃዊ ሊሆን አይችልም፡፡ ፍፁም አይን ያወጣ አምባገነንነት ነው፡፡ የነፃ ፕሬስ መዳፈን የፍትሃዊነት ሽታ ከቶውንም የለውም፡፡ በደህንነት ሃይሎች መዋከብ ከኢፍትሃዊነትም በላይ የከፋ በደል ነው፡፡ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት መታፈን ኢህፍትሃዊነት ነው፡፡ የናጠጠ ነጋዴ፣ ‹‹የነፃ ገበያ ስርዓቱን›› እንደፈለገው የሚዋኝበት ፓርቲ ባለበት አገር፣ ተቃዋሚዎች እርዳታ እንኳን እንዳያገኙ የሕዝብ አሻራ መሰብሰብ ከአፈናም በላይ የገዘፈ አፈና ነው፡፡ ተቃዋሚዎችም የራሳቸው ሕፀፆች እያሏቸውም፡፡ የመንግስትና የግሉ የሬዲዬ ጣቢያዎች ያሉት ፓርቲ ባለበት አገር ሦስት ሽህ ቅጅዎችን እንኳን አባዝተው ለመሸጥ እንዳይችሉ ዙሪያ መለስ የአፈና መዋቅር የሚዘረጋባቸው ተቃዋሚዎች መኖር ይች ሃገር የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳትሆን የአቶ መለስና የካድሬዎቻቸው ስለመሆኗ ምስክር መጥራት አያሻውም፡፡ ብዙ የአፈና አይቶችን ለመጥቀስ አንቸገርም ነገር ግን ከዚህ አጭር ጽሁፍ አንፃር የተጠቀሱት ለአብነት በቂ ናቸው፡፡

የጓደኞችን ገጠመኞች አንድ ላክል፡፡ ፀጉር አስተካካይ ወጣት ነች ፀጉሩን እያስተካከለችው ላለው ጓደኛዬ ‹‹አሁንስ እሰው አገር ተሰድጄ ብኖር ይሻለኛል›› ትለዋለች፡፡ አጠገቡ ያለ ሌላ ተስተካካይ ‹‹ይኽም የሰው አገር ስለሆነ ሌላ አገር መሄድ አያስፈልግሽም፡፡›› ይላታል፡፡ ይኸን መሰል አባባሎች ሕዝቡ በአገሩ ላይ ምን ያህል ተስፋ እንደቆረጠ ፍንትው አድርገው ያሳያሉ፡፡ ይህን መሰሉ አባባል ታዲያ ኢህአዴጎች ጋር ሲደርስ ጆሯቸው ላይ ነጥሮ ይመለሳል፡፡ እነርሱ የሚሰሙት የልማት እና የእድገት ፕሮፓጋንዳን ብቻ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ለ20 ዓመታት አገርን መቀመቅ እያወረደ ያለ ፓርቲ 99.6% የመራጭ ድምፅ አገኘው ብሎ በኢትዮጵያ ሕዝብ ጫቃ ላይ ተጥዶ በማን አለብኝነት ሲቀጥል የግፍ ፅዋ ሞልቶ እንደፈሰሰ ትክክለኛ ማሳያ ነው፡፡ ለዛውም በ21ኛው ክፍለ ዘመን፡፡

ይኸን ሁሉ የፍትህ መታጣት እንደሚያሳይ ሁሉ ይኸን ሁሉ እያዩ እንዳላዩ መሆን፣ ሲነጋ ይነጋል ማለት ከፈሪነትም በላይ እጅግ የበዛ የዋህነትም ነው፡፡ ከላይ ከፍ ብለን የጠቀስናቸውን የጭቆና አብነቶችን መቃወም የሚጠይቀው ሰው መሆንን ብቻ ነው፡፡ በወገን ላይ መነሳት ወይንም የመውደድ የመጥላትም ጉዳይ አይደለም፡፡ እነ አቶ መለስ እንደሚሉት፡፡ ሁሉም ሰው በእኩልነት የሚኖርባት የሁሉም ኢትዮጵያውያን ገነት የሆነች አገርን ለመፍጠር መመኘት ነው፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን መታገል ዋጋም መክፈል ፍርሃትን የመስበር ትግልም ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ እኛ በአደባባይ ከምንናገረውና ከምንፅፈው በላይ በዚህ መንግስት ላይ ያላቸውን ብሶት በየቤታቸውና በየካፍቴሪያው ያለማባራት የሚናገሩ ኢትዮጵያውያንን ቤታቸው ይቁጠራቸው፡፡ ነገር ግን የማያውቁት ሰው በአጠገባቸው ካለፈ አየር መሳብ የሚያቅታቸውም የዛኑ ያህል ናቸው፡፡ ይኸም ትክክል አለመሆኑን የሚነግራቸውን ሰው አላዋቂ፣ ጀብደኛና የኑሮ ዘዴ የማያውቅ አድርገው ይፈርጁታል፡፡ ኑሮ ካሉት መቃብርም… እንደሚሉት መሆኑ ነው፡፡ ኢህአዴግ አገር እያጠፋም ተሞዳሙዶ መኖር የብልህነት ተምሳሌት እየተደረገ ነው፡፡ ትልቅ ውድቀት ነው፡፡ የሚያሳዝነው የኢህአዴግም መሪዎች ፍርሃት ከዕለት ወደ ዕለት እያየለ መሄዱ ነው፡፡ እነ አቶ መለስ ቢደፍሩ ለፍትህ፣ ለዕውነትና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት በተገዙ ነበር፡፡ የሕዝብ ፍትህ ይገባኛል ብሎ አለመጠየቅም፣ ለአገሩ ዳር ድንበር መጠበቅ የሚያሳየውን የጀግንነት የስነ-ልቦና ደረጃ የራሱን ሁለንተናዊ ነፃነት ከአፋኝ መሪዎቹ ለመከላከል እንደ ቀመደው ጊዜ በህግ-አምላክ እንኳን ለማለት የማይችልበት ሁኔታ መድረሱ ትልቅ አሳዛኝም አሳሳቢም ጉዳይ ነው፡፡

የሃገራችን ሁለንተናዊ መስተጋብር መስመር ይይዝ ዘንድ ፍርሃት ከኢትዮጵያ ምድር ይወገድ፡፡ የፍርሃት ግንብ ይደርመስ፡፡ አንዱ ኢትዮጵያዊ በሌላው ኢትዮጵያዊ ላይ በአፈ ሙዝ ወይንም በስለላ መዋቅር አስገዳጅነት አሊያም ከስራ በማፈናቀል እና በአያሌ የመብት ጥሰቶች የሚፈፀመው የአፈናና የዘረፋ ተግባር ይብቃ፡፡ አንድ አማካኝ መንገድ አለ፡፡ ፍርሃት ሞቶ የሚቀበርበት፡፡ የፍትህ አደባባይ፡፡ ፍትህ በኢትዮጵያ ምድር እንደ አባይ ጅረት ያለማቋረጥ ይፍሰስ፡፡ ፍትህን ሲያከብሩ #መሪዎቻችንም$ ከፍርዓት ማዕበል ነፃ ይወጣሉ፡፡ ፍትህ ሲኖር ሕዝብ የመረጠው መንግስት ይመሰረታል፡፡ ፍትህ ሲሰፍን የሰው ልጅ ክብር በኢትዮጵያ ምድር እንደ ቀትር ፀሐይ ያበራል፡፡ እንደ ሃይለኛ ጅረትም ይፈሳል፡፡ ፍትህ በኢትዮጵያ ምድር ሲሰፍን የፍርሃት ግድብ ይደረመሳል፡፡ ፍርሃት ከየኢትዮጵያዊው ልብ እንደ ማለዳ ጤዛ ይተናል፡፡ አዎ! ፍርሃት ከኢህአዴግአውያን ልብ እንደ ጤዛ ይትነን፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ በአፈ-ሙዝ አንበርክከው ለመግዛት የሚያሳሙት ቅዥታቸውም እንዲሁ አውሎ ነፋስ ጠራርጎ እንደሚወስደው ትቢያ ይወገድ፡፡ ያለፍትህ ነፃነት የለም፡፡ ያለነፃነት ልማት፣ ሰላም፣ ወንድማማችነት የቀን ቅዥት ነው፡፡ ከአምባገነኖች ጋር ተሞዳሙዶ መልማትም ሆነ ፍትህ ማግኘትም የዚያኑ ያህል የቀን ቅዠት ነው፡፡ ፍትህ እንዲሰፍንና ያልተወለዱ ልጆቻችንም ጭምር ከአፈና ለመታደግ ዛሬ ከእያንዳንዳችን ልቦና ፍርሃት ጥፍፍ ብሎ ይውጣ፡፡ እያንዳንዳችን ለሁሉም መብት ሁሉም ለእያንዳንዱ ይታገል፡፡ ኢትዮጵያ ለውስጥ ነፃነቱ ዘብ የሚቆም የጀግና፣ የፍትህ ናፋቂ እና የፍትህ ባለቤት የሆነ የታላቅ ሕዝብ አገር እንድትሆን ፍርሃት ሞቶ ይቀበር፡፡ ፍትህ በተራሮቻችን ጫፍ ላይ ይምቦግቦግ፡፡ ከዚያ ወንድማማችነት ከመቸውም ጊዜ ይበልጥ ያብባል፡፡ ያን ጊዜ ወደ መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገሮች ደረጃ እየገሰገስን ነው እያልን ስኳር እንደ ሃሽሽ በድብቅ በወረቀት ተጠቅልሎ የሚሸጥበት ዘመን ያከትማል፡፡ የዛን ጊዜ ሚሊዬኖች ሬሽን ካርድ ይዘው በኢትፍሩት አይሰለፉም፡፡ ያኔ ለሚሊዬን ኢትዮጵያውያን የስንዴ ምጽዋት መጠየቅ ይቀራል፡፡ ያን ጊዜ ፍቅር በሚያፈረጥመው ክንዳችን፣ ፍትህ ላይ በሚገነባው ውስጣዊ ነፃነታችን በደምና በአጥንታችንም ጭምር የምንወዳትን ሃገራችንን እንገነባታለን፡፡ እጅ ለእጅ ተያይዘን ሀገራችንን የቀጣይ ትውልዶች ሁሉ ትምክህትን እንድትሆን እናደርጋታለን፡፡ አዎ ፍትህ በኢትዮጵያ ምድር እንደ ሀይለኛ ጅረት ለዘላለም ይፍሰስ፡፡

ፀሐፊውን Facebook ላይ Ruh Goh ብለው ወይንም በe-mail:[email protected] አስተያየተዎትን ሊያደርሷቸው ይችላሉ፡፡