መልቲዎችን እንዴት ማቸነፍ ይቻላል? በደጉ ማረው

“የአሁኑ የኢትዮጵያ መሪዎችና መልቲነት” በሚለው ጽሁፍ በአጠቃላይ መልቲዎች ምን ዐይነት ፀባይ እንደሚያራምዱ ለማሳያት ተመክሯል። በዚህ ፅሁፍ ደግሞ በፖለቲካ አመራር ላይ ያሉ መልቲዎች ምን አይነት ጸባይ አንደሚያሳዩና እነሱን እንዴት መዋጋት እንደሚቻል ለማሳየት እንሞክራለን።

ከዚህ በፊት ለማሳየት እንደተሞከረው መልቲዎች እጅግ ቀዝቃዛ ስሜት ያላቸው የሞራል ግዴታ የማያውቁ ናቸው። ይህም የስሜት ቅዝቃዜ ብዙ ሰዎች ያላቸውን ዐይነት የፍቅር፣ የሰው ችግር የመረዳትና በሰው ላይ የሚደርሱት አደጋ እራሳቸው ላይ ሊደርስ ይችላል (empathy) ብለው የማይጨነቁ፣ ፈሪሃ-እግዚአብሄር ጨርሶ የሌላቸው ናቸው። ብዙ የስነ ልቦና ተመራማሪዎች መልቲዎችን በህክምናም ሆነ በምክር መመለስ እንደማይቻል የገልጻሉ። እንደውም የአዋቂ ምክር (counseling) የማታለል ጸባያቸውን ስለሚያጎለምሰው ባይሞከር ይሻላል ይላሉ።

የመጀመርያው የመልቲ መለያ ቅጥፈቱ ነው። ነገር ግን ቅጥፈቱ እንዲህ በቀላል የሚታውቅ አይደለም። ምን ያህል ማራኪና አሳማኝ እንደሆኑ ለማሳየት የሚከተለውን ምሳሌ ላጫውታችሁ። ግዜውን በትክክል በላስታውሰውም እነአቶ ስዬ አብረሃ ለመጨረሻ ጊዜ የተሳተፉበት የህዋሀት ጉባኤ በመቀሌ በተካሄደበት ጊዜ አንዳንድ የድርጅቱ አመራሮች አቶ መለስ በኤርትራ ጦርነት ጊዜ ባሳዩት የማደናቀፍ ሥራ ከፍተኛ ወቀሳ እንዲደረግባቸው ከማደርግ በላይ እንድየውም በግልጽ የድርጅት አመራር ሥልጣናቸውን እንዲለቁ ይገፉ እንደነበር አቶ መለሰ በቅድሚያ ስለተረዱ ተቃዋሚ ባልንጀሮቻቸው ሳይቅድሟቸው አስቀድመው ለጉባኢው ንግግር ያቀርባሉ። ይህ ንግግር እጅግ ማራኪና አሳማኝ ከመሆኑ የተነሳ ተቃዋሚዎቻቸውን ሁሉ ሳይቀር ወደእሳቸው ጎራ እንዲመጣ ለማድረግ አስችሏቸዋል። በንግግራቸው የተማረከው የጉባኤው ተሳታፊም ተያይዞ ሲላቀስ እንደነበር በሥፍራው የነበሩ ሰዎች የሚመሰክሩት ነው። አቶ መለስ ግን ጉባኤውን አላቅሰው አዲስ አበባ ከተመለሱ በኋላ የአብዴን (ANDM) ወታደሮች በመጠቀም ተቃዋሚዎቻቸውን ግማሹን ለእሥር የቀረውንም ከህዋሀት (TPLF) አባረዋል። እሳቸው የአብዴንን ወታደሮች የተጠቀሙት የህዋሀት ወታደሮች በዚህ ጉዳይ ላይ አይተባበሩኝም ብለው ስለፈሩ ነበር።

ሁለተኛው የመልቲ መሪ መለያ በመሪው ዙሪያ ያሉ ሰዎች ደካማና የታዘዙትን ያለምንም ጥያቄ ፈጻሚ መሆናቸው ነው። ይህ መመዘኛ በአገራችን ምን ያህል እውነት እንደሆነ ለአንባቢያን ማስረዳት ቀባሪን እንደማርዳት ይሆናል።

ሌላው የመልቲ መሪ መለያ ደግሞ ዜጋቸውን መብት እንዳለው የሰው ፍጡር ሳይሆን ለእነሱ ለመገልገያ ብቻ የሚውል እቃ አድርገው መቁጠር ነው። ይህንንም ለማድረግ ያላቸውን ሀይልና ገንዘብ ይጠቀማሉ። ለምሳሌ በአገራችን ያለውን የመገናኛ ብዙሃን እፈና ልብ ይሏል።

መልቲዎች የተከታዮቻቸውን ቅስም በመስበር ወይም በሙስና እንዲዘፈቁ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ወይም እርስ በእርስ በመከፋፈል የእነርሱ አገልጋይ ማድረግ ትልቁ ችሎታቸው ነው። መልቲዎች አብረዋቸው የሚሰሩትን እንዲህ አድርገው ከስለቡ በኋላ በዙሪአቸው ያሉ ሰዎች አንድ ምርጫ ብቻ እንዲኖራቸው ይሀውም እነሱን ማገልገል እንዲሆን ያደርጋሉ።

በአገር መሪነት ላይ የሚገኙ መልቲዎች ብዙ ጊዜ ወደ ሥልጣን የሚደርሱበት አንዱ መንገድ “የቀድሞው ሥርዓት” መለውጥ አለበት የሚል መፈክር በማንገብ ሲሆን ለዚህ ይረዳ ዘንድ የተወስነ ክፍልን ነጥሎ የህብረተሰብ ጠላት አድርጎ በማስቀመጥ ተከታዮችን ለማፍራት በመቀስቀስ ነው። እንደሚታወቀው እውነት የመሰለ ውሸትን ለመለየት እጅግ አስቸጋሪ ከመሆኑም በላይ አደገኛ ነው። ይህንን ደግሞ መልቲዎች ጠንቅቀው ያውቃሉ። መልቲዎች ይህን ነጥለው ያወጡትን የህብረተሰብ ክፍል ለሁሉም የህብረተስብ ችግር መንሰኤ እንደሆነና ይህ ክፍል ሲወገድ ወይም በቁጥጥር ሥር ሲውል ህብረተሰቡም ወደፊት እንደሚራመድ ይቀሰቅሳሉ። ለምሳሌ ሂትለር የአይሁዶች ጉዳይ ለአንዴና የዘላለም መፍትሄ ሊገኝለት እንደሚገባ በመቁጠር የጀርመንን ህዝብ አስተባብሮበታል። ይህም ቅስቀሳ ምን ያህል ትልቅ ወንጀል እንደስከተል አንባብያን ያውቃሉ። ወደአገራችንም ስንመለስ በኡሁኑ ስዓት በስልጣን ላይ ያለው ፓርቲ “ነፍጠኛ” የሚል ቅጽል ስም የሰጣቸውን አማራዎች አንደሀገር ጠላት አድርጎ በማቅረብ ሌሎች የኢትዮጵያ ህብረተስብ ከፍሎችን ለማስተባበር ሞክሯል። ነገር ግን በመረጋጋት ሁኔታው ቢጤን ሕውሃት አማራን በሚከስበት “ነፍጠኝነት” የትግራይ ህዝብ ዋነኛ ተዋናኝ እንደሆነ በቀላሉ ከታሪክ መረዳት ይቻላል:፡እንዲሁም አማራ ያልሆኑ ነገር ግን ይህን ውሸት ያልተቀበሉ ኢትዮጵያውያንን ደግሞ “የደርግ ርዝራዥ” በሚል በጠላትነት ይፈርጃቸዋል። ሆኖም ይህ ቅስቀሳ መሪዎቹ የተመኙትን ያህል አልሰራም (እግዚአብሄር ይመስገን)። በተለይ ባሁኑ ስዓት አብዛኛው የህብረተሰብ አባል ይህን ውሸት የነቃበት ይመስላል።

በሥልጣን ላይ ያሉ መልቲዎች የሚመሩትን አገር ሀብት በከፍተኛ ደረጃ የነሱን ሥልጣን ማራዘሚያና ተቃዋሚዎቻቸውን ማኮላሻ ስለሚጠቀሙበት እነሱን በቀላሉ ለማቸነፍ ያስቸግራል። በተጨማሪም የሚመሩትን አገር ህግና ደምብም በነሱ ሥልጣን ማቆያ ዙሪያ ስለሚያደራጁት እነሱን በህግ ማቸነፍም አይቻልም. እነርሱ ራሳቸው ግን ከሀግ በላይ ስለሚሁኑ የማይስማማቸውንም ደንብ በፈለጉ ጊዜ ይቀይሩታልና።

መልቲዎችን ለማጥቃትና ለማቸነፍ የሚቻለው ጸባያቸውን በሚገባ ጠንቅቆ በመለየት ነው። ይህ እውቀት ደግሞ መልቲዎች ተመልሰው ወደስልጣን እንዳይመጡም ለመከላከል ይስችላል። አንባቢያን እነዚህን መመዘኛ መጠይቆች በማንኛውም አስፈላጊ ቦታ (በሥራ ቦታ፣ የትዳር ጓደኛ ለመምረጥ፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ መሪዎችን ለመለየት) በመጠቀም እራሳቸውን ከመልቲዎች ጥቃት ለመከላከል ይችላሉ።መልቲዎችን ለማወቅ የሚከተሉትን ጥያቄዎች በሚገባ መመለስ ይገባል፡፡ በመልቲነት ይሚጠረጠረው
1. ግለሰቡ ወይም ግለሰቧ ሰውን (ጅርጅቱን/አገሩን) በተደጋጋሚ ያለፀፀት ይጎዳሉ ወይ?
2. ግለሰቡ ወይም ግለሰቧ ሰውን የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሰማቸው ማድረ ግ ያስደስታቸዋል ወይ (የብርቱካንን የይቅርታ ረቂቅ መመልከት ጥሩ ምሳሌ ነው)?
3. ግለሰቡ ወይም ግለሰቧ ሲቀጥፉ ያለምንም ዕፍረት ነው ወይ?
4. ግለሰቡ ወይም ግለሰቧ ስሜታቸው (mood swing) በየጊዜው ይለዋወጣል ወይ?
5. ግለሰቡ ወይም ግለሰቧ የማይገባቸውን ንብረትና ገንዝብ ይውስዳሉ ወይ? መልቲዎች ቢቻል በመስረቅ/በማታለል አልበልዚያም በመበደር የወሰዱትን ገንዘብ አይመልሱም
6. ግለሰቡ ወይም ግለሰቧ ለሰዎችና ለእንሰሳዎች ሞገደኛ የሆነ ጭካኔ ያሳያሉ ወይ (እጅ እንቆርጣልን፣ በእስር ቤት እናበሰብሳለን፤ ኢንተርሃውሜ፣ የሚባሉ ንግግሮችን ልብ ይሏል።)
7. ግለሰቡ ወይም ግለሰቧ እራሳቸውን ከፍ ከፍ ከማድረግም በላይ ብዙ ድሎችን እንደአስመዘገቡ ወይም እንደሚያስመዘግቡ ጉራ ይነዛሉ ወይ? (የእትዮጵያ ህዝብ ከእንግዲህ በኋላ ሻማ የሚበራው ለልደት ነው፤ ረሃብን በአምስት አምት እናጠፋለን እንዲሁም በቅርቡ ደግሞ እትዮጵያ በሚቀጥሉት አምስት አመታት መሃከለኛ ገቢ ካሏቸው አገራት መደዳ ትመደባለች የሚሉትን አነጋገርን ልብ ይሏል – አንዳቸውም ግባቸውን እንደአልመቱ መታዘብ ይገባል።
8. ግለሰቡ ወይም ግለሰቧ እንደተጠቀሙቦዎት ሆኖ ይሰማዎታል ወይ?
9. ግለሰቡ ወይም ግለሰቧ ያለ ግብ የመነዳት አዝማሚያ ያሳያሉ ወይ?
10. ግለሰቡ ወይም ግለሰቧ ሃላፊነት የጎደለው ስራ ከመስራታቸውም በላይ በስራቸው መጥፎ ውጤት ይፀፀታሉ ወይ? ሃላፊነትስ ይወስዳሉ ወይ?
11. በወጣትነት ጊዜያቸው ፀረ-ህብረተስብ ፀባይ ያሳዩ ነበር ወይ? አስተዳደጋቸውስ ሞገደኛነት የሞላበት ነበር ወይ?
12. መልካም ጓደኞች አሏቸው ወይ ወይስ ጓደኝነታቸው የይስሙላ ነው?
ከላይ የተጠቀሱት መልኪያውች በብዙ ሰዎች ላይ አልፎ አልፎ የሚታይ ቢሆንም በመልቲነት ሊይስቆጥራቸው አያስችልም። እነዚህ ፀባያት በመልቲዎች ላይ ዘወትር የሚንፀባረቁ ናቸው። አንዳንድ የስነ ልቦና ተመራማሪዎች መልቲዎች ይህን አይነት ፀባይ መጥፎ መሆኑን አይገነዘቡትም በመሁኑም መልቲዎች እንደ እንደእዕምሮ በሽታኛ መታይት አለባቸው ይላሉ።

እራሳችንን እንዴት ከመልቲዎች እንገላግላለን?

የስነልቦና ሀኪሞች ከተራ መልቲዎች ሰለባ ለመላቀቅ በተቻለ መጠን ከመልቲዎች እጅግ አድርገን እንድንርቅ ይመክራሉ። ለመልቲዎችም የህክምና እርዳታ እንዲያገኙ መሞከርም ከንቱ ጥረት ነው ይላሉ። ነገር ግን እራስን በማግለል የማይገላገሉትን መልቲ ምን ያደርጉታል?

አንዴ መልቲነት ከተረጋገጠ በኋላ መልቲዎችን እነሱ በማያቁት ሁኔታ፣ የሚሉትንና የሚያደርጉትን በመከታተል ስለእነሱ መረጃ መሰብሰብ ይስፈልጋል። መልቲዎች በምንም ዓይነት ሁኔታ ስለማይቀየሩ በየጊዜው ስሲዋሹ መገኘታቸው አይቀሬ ነው። የህን ውሸታችውን በማስረጃ በማስደገፍ ለዜጎች ማሳወቅ እጅግ ጠቃሚ ነው። ይህም መልቲዎች እጅግ የባሰና አላማ የለሽ ጥፋት እንዲያደርጉ ስለሚያደርጋቸው (erratic behaviour) እውነተኛ ማንነታቸው በደጋፊዎቻቸው እንኳን ሳይቀር እየተጋለጠ ይመጣል።

በሌላ በኩል ደግሞ የመልቲዎች የጥፋት ዕቅድ እንዳይሳካ ማድረግ እጅግ ጠቃሚ ነው። ዕቅዳቸው ሲፈርስ መልቲዎች እጅግ የበሳጫሉ በዙሪይቸው ያሉትን ሁሉ ማበሳጨት ስለሚጀምሩ ያለደጋፊ እንዲቀሩ ያደርጋቸዋል።

በተጨማሪ የመልቲዎች እውነተኛ ማንነት ለህብረተሰቡ በሚገባ መሰራጨት አለበት። የተንኮል ዕቅዳቸውን ለደጋፊዎቻቸው ማስታውቅ ይገባል። ለምሳሌ ከፋፍሎ መግዛት የአሁኑ ያኢትዮጵያ መሪዎች ዋነኛ መሳሪያ ነው። ለአማራው የኢትዮጵያ ክፍል ኦሮሞ ስልጣን ላይ ከወጣ ይጨርስሃል በማለት ለኦሮሞው የኢትዮጵያ ክፍል ደግሞ አማራ ሊገዛህ ነው፤ በደምህ ያገኘሀውን እራስን በእራስ ማስተዳደር አማራ ሊነጥቅህ ነው በማለት ያስፈራራሉ። ነገር ግን አማራም ሆነ ኦሮሞ የህብረተሰብ ክፍል መረዳት ያለበት እራስን በራስ ማስተዳደር የሚቻለው የሚተዳደር አገር ሲኖር ብቻ ነው። በአሁኑ ጊዜ የእትዮጵያ መሬት በከፍተኛ ደረጃና ስፋት እየተሸጠ ባለበት ወቅት እርስ በእርስ መከፋፈል ነገ እራስን በራስ የሚተዳደር አገር ማጣትን ያስከትላል እንጂ ለህብረተሰቡ የሚጠቅም ውጤት አያስገኝም።

መልቲ መሪዎችን ለአለም አቀፍ ደጋፊዎቻቸው ሁሉ ማጋለጥ ተገቢ ነው። አለም አቀፍ ደጋፊዎች እንዲህ ያሉ መሪዎችን መደገፋቸውን ወዲያውኑ ሊያቆሙ አይችሉ ይሆናል ነገር ግን መልቲነታቸውን ከማጋልጥ ወደኋላ ማለት አያስፈልግም።

በመጨረሻም መልቲ መሪዎችን በፈጣንና በተሳካ ሁኔታ ለማስወገድ በአንድ ድርጅት ጥላ ሥር መደራጀት እጅግ አስፈላጊ ነው። ሁሉም ድርጅቶች በህብረት ሆነው ሊያስማም በሚችል ግልፅ የአቋም መርህ መተባበር ይገባቸዋል። እንዲህ የማያደርጉ የተቃዋሚ ድርጅት መሪዎች ምናልባትም መልቲ ሊሆኑ ስለሚችሉ መጋለጥ ይገባቸዋል። (ምክንያቱም የኢትዮጵያ ህዝብ ሰቆቃ አንተሰማቸውምና)።

መልቲ መሪ በሞት ሲለይ ወይም ከሥልጣን ሲወርድ በውሸት የገነባው ዝና ሁሉ የፈርሳል። አደርግሁ ያለው የዕድገት ውጤት ሁሉ ቅጥፈት እንደነበረ ገሀድ ይሆናል፡፡ ሚስጥሩ ያለው መልቲ መሪ በስልጣን ላይ በሚቆይባት ደቂቃ ሁሉ የሚያደርስው ጥፋት እጅግ ብዙ ስለሆነ ሳይውል ሳያድር ከሃላፊነት ላይ ማስወገድ ላይ ነው።