የአምባገነኖች የመጨረሻ ቀናትና የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ

ምዕራቡ ዓለም በዋናነነት በሁለት ዋና ምሰሶዎች ላይ የተመረኮዙ መርሆዎችን በማራመድ ከኮሚኒዝም ጋር የተያያዘውን ትንቅንቅ በድል ለማጠናቀቅ ትልሙን ጣለ፡፡ ሁሉን አቀፍ ፀረ-ኮሚኒዝም ጦር መስበቅ እና የተጠናከረችና የፈረጠመች እስራኤልን በመኮከለኛው መስራቅ ማደላደል፡፡ እነዚህ ሁለት ምሰሶዎች ላይ በመመርኮዝ ኮሚኒዝምን የሚያወግዙና የእስራኤልን ደህንነት አደጋ ላይ የማይጥሉ አምባገነኖች ሁሉ በዓለም ዙሪያ በሕዝባቸው ላይ ለሚያደርሱት ምሬትና ዋይታ ኬላው ከፍ ብሉ ተነሳላቸው፡፡ በኋላ ላይ በፀረ-ሽብር ዘመቻው ተባባሪ ለሆኑ አምባገነኖችም ይኸው ቡራኬ ተቸራቸው፡፡ ከምዕራቡ ዓለም ከፍ ሲል ከጠቀስናቸው ሦስት ጥቅሞች ጋር የሚጋጩ ሁሉ ግን በቀጥታና በእጅ አዙር የሰይፋቸው ሰለባ ሆኑ፡፡ ሃፍረትን የማያውቁት የአሜሪካ እና ሌሎች በርካታ የምዕራቡ ዓለም አገራት ተከታታይ መሪዎች ለተራ ጥቅሞች ሳይቀር በአራቱም ማዕዘናት አምባገነኖችን በማወደስ፣ አይተው እንዳላዩ በማለፍና አልፈው ተርፈውም የንፁሃንን ደም ለማፍሰስ የሚረዱ መሳሪያዎችን በመሸለም ለአምባገነኖች ማርገዳቸውን ቀጠሉበት፡፡ ይህን በመሠለው ተግባራቸው በየአገሮቻቸው እውን አድርገናል የሚሉትን የሕዝብ ልዕልና ጭቃ ውስጥ ጥለው እረገጡት፡፡ መገለጫቸውም ተራ ጥቅም ማሳደድ ብቻ ሆነ፡፡ ነገር ግን ውሎ አድሮ ሲጋልቧቸው የነበሩት ስናሮች እነርሱንም ከመርገጥና ለጥቅሞቻቸውም ደንቃራ ከመሆን አልዳኑም፡፡

የምዕራቡ ዓለም ይህን በመሠለው በራሱ መርሆዎችና በስብዕና ላይ በፈፀመው ደባና ክህደት፣ በዓለም ላይ በነበሩ ልዩ ልዩ የፖለቲካ መባዘቆች ለዘመናት ሕዝብን ያንገሸገሹ ሥርዓቶች በሕዝባዊ አቢዮቶች ሲመነገሉ ሌሎች በጎደሎ ስብእናቸው የሚታወቁ፣ ወገኖቻቸውን እንደ ሳር የሚያጭዱ የሕዝብን ዋይታ እንደ የሙዚቃ ጥዑም ዜማ የሚቆጥሩ መረን አምባገነኖች ዓለማችንን መናሃሪያ አደረጓት፡፡ በተለይም በመካከለኛው ምስራቅና የግፍ ቋት በሆነችው አፍሪካችን፡፡

በመካከለኛው ምስራቅና በአፍሪካ ሕዝብ ለዓስርተ-ዓመታት ከራሱ አብራክ በወጡ አምባገነኖች ሰይፍ በገፍ ተበላ፡፡ አሁንም ተደራጅቶ እራሱን መከላከል በማይችልበት ሁኔታ በትውልድ ቀየው በልጆቹ ፊት ይደበደባል፡፡ አልታረም እንዳለ ልጅ በአርጩሜ ይገረፋል፡፡ ባሎች ሚስቶቻቸውን ይነጠቃሉ፡፡ ሚስቶች ባሎቻቸውን በግፍ እስከ ዝንተ-ዓለም ይሰናበታሉ፡፡ በማያባራ ዋይታና በማይጠፋ የሃዘን ረመጥ እየተበሉ በችጋር የሙት ልጆችን ያሳድጋሉ፡፡ ይህን ከመሠለው የሕይወት አውድ ውስጥ ያልተላቀቀው ሕዝብ ይኸም አነሰህ ተብሎ በሚሊዬን የሚቆጠሩ አፋኝ ደህንነቶችና አልሞ ገዳይ ፖሊሶች የብረት መረብ ዘርግተው ጮክ ብሎ እንኳን በአደባባይ ሊቃወም ይቅርና ጮክ ብሎ እንዳያለቅስ ገደብ ጥለውበታል፡፡ ለቅሶውንም፣ ርሃቡንም ቁዘማውንም በዚያችው በጠባብ ማጀቱ በሩን ዘግቶ ይወጣል፡፡ ለአያሌ ዓመታት፡፡ በጭቆና ቀንበር ሥር ሕዝባቸውን የሚያማቅቁ አገሮች ያሏቸው ‹ሕገ-መንግሥቶች› ከብዙዎቹ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ከሰፈነባቸው ሃገሮች ቢልቁ እንጅ የሚያንሱ አይደሉም፡፡ ይሁን እንጅ ቃላት ሥጋ ለብሰው ሕዝብን ከጅምላ እስር፣ ርሸና፣ ችጋር፣ አይን ካወጣ ዘረፋና አድልኦ በአጠቃላይ ፍትህን ሞቶ ከመቀበር ሊታደጉ አልቻሉም፡፡ ሕገ-መንግሥት ማለት የአጤዎች ቃል ሆነ፡፡ ለዛውም ቃለ-መርገም፣ ቃለ-ውርደት፣ ቃለ-ውድቀትና ቃለ አጠቃላይ ጥፋት፡፡

የሕዝብ ጫንቃ ይህን ሁሉ ጉድ ቢሸከምም ስንክሳሩ በቀላሉ የሚቋጭ አልሆነም፡፡ በተለይም በአረብ አገሮች እንደተስተዋለው በአንድ ወቅት የሕዝብ ብሶት ወለደን ያሉን አምባገነኖች የተኳቸውን መሪዎች ስብዕና መላበስ ጀመሩ፡፡ ስዩመ-ፈጣሪ ለመሆን ተንደረደሩ፡፡ ልጆቻቸውን ለአልጋ ወራሽነት አጩ፡፡ የእኛው ‹መሪ› ደግሞ ባለቤታቸውን ከአጠገባቸው በመሻጥ በተግባር አልጋ ወራሽ ለማድረግ ይቻል ዘንድ ‹ከዓምስት ሚሊዬኑ› መሃል መንጥቀው ከደመና በላይ ቁብ አረጓቸው፡፡ እንደ ቢን አሊ መሆናቸው ነው፡፡

በዚህም አልበቃ፡፡ ሕዝብ ሰብዓዊ ክብሩን ብቻ ሳይሆን ሰብአዊ ቁሱንም በገፍ ተነጠቀ፡፡ ሀገርና ሕዝብ በአምባገነኖች ካዝና ውስጥ የሚቆጠሩ ቁሶች ሆኑ፡፡ በዓለማችን በታታሪነታቸው ከዚያም በሚመነጨው ባለፀግነታቸው የሚታወቁት ሃብታሞች ከእነዚህ ዘራፊዎች ተርታ በሀብት መጠን ሊሰለፉ የሚችሉበት አንዳች አቅም አጡ፡፡ በጣም የሚያስደምመው ግን እንደዚህ እንደቁስ የሚቆጥሩትና የላቡን ፍሬ የሚነጥቁትን ሕዝብ እንደሚያፈቅራቸው ደጋግሞም ኮንትራት እንደሚያሰፈርማቸው አምባገነኖቹ ይነግሩናል፡፡ ሲያስፈርማቸውም ከለግስና ጋር ነው፡፡ በግብጽ 95%
‹ድምፁን በመስጠት ሲሆን አቶ በረከት እንዳሉት ለ3ዐ ዓመታት ልማት ባላያት ግብጽ ይኸን ያህል ሕዝብ ሙባረክን ከወደደ የኢትዮጵያን ሕዝብ በማያባራ የእድገት ግስጋሴ የሚያነጉዱትን አቶ መለስን 99.6% ሰጥቶ ኮንትራት እንዳስፈረማቸው መከራከር ምክንያታዊ ለማስመሰል ሳይቀል አይቀርም፡፡ ደግሞስ ለአቢዮታዊ ደሞክራቶች አቢዩታዊ ውሽትስ ምን ይገዳቸዋል? በሌሎቹም የአረብና የአፍሪካ አገሮች የሆነው ይኸው ነው፡፡ የምርጫ ተውኔት፣ የምርጫ ፌዝ፡፡

የእነዚህ አገሮች ሌላው ሁነኛ መገለጫቸው የጫጨ የሲቪል ማህበረሰብ፣ የታፈነና የተመናተለ የግል መገናኛ አውታር፣ ከተሰመረላቸው መስመር እንዳያልፉ በደህንነት ወከባ የዛሉ የተቃዋሚ ፓርቲዎችና ከሥርዓቶቹ ጋር የተቆራኙ የኃይማኖት ተቋማት ናቸው፡፡ ሌሎችም አያሌ መገለጫወቻቸውን ማንሳት ይቻላል፡፡ የሚመሳሰሉበትን ብቻ ሳይሆን የሚለያዩባቸውን ልዩ አገራዊ ክንዋኔዎችንና ገጽታዎች ማውሳት ይቻላል፡፡ ነገር ግን በዚህ አጭር ጽሁፍ ይህንን መሰሉ ዝርዝር ውስጥ መግባት አስቸጋሪ ይሆናል፡፡

አምባገነኖች በሕዝብ ሁለንተና ላይ መቀለድን ሥራዬ ብለው ሲቀጥሉ፣ አዝጋሚም ቢሆን ሕዝብ ያጎበጠውን የጭቆናና የአፈና መርግ ከላዩ ለማውረድ ሥራውን ቀጥሏል፡፡ በተለይም ከእውቀት ማዕድ በቅጡ የተቋደሰ ነገር ግን አምባገነኖች ከሚዘርፉት ጥሪት ላቡን አፍስሶ እንኳን መሳተፍ የማይችል ወጣት መበራከት፣ የጭቆናው መስፋፋትና ውስጥ ውስጡን ሲብላላ የባጀ የሕዝብ ብሶት ክዳኑን መግፋት መጀመር፣ ለቴክኖሎጂ ምስጋና ይግባውና የማህበራዊ- መረብ (Social-networking) መስፋፋት፣ ዴሞክራሲና እውነተኛ የሕዝብ መንግሥት መምረጥ ምን ማለት እንደሆነ በማያሳስት መንገድ ሕዝብ መማር መቻሉ፣ ይኸም ፍርሃትን ለመስበር፣ ተስፋን ለመሰነቅ የማይናቅ ሚና መጫወቱን ልብ ማለት ይቻላል፡፡ በቀደሙ አቢዬቶች ወቅት ተስፋው በቀላሉ ሲሞት፣ ሕልሙ ሲጨናገፍ፣ ፍርሃት በአፈ-ሙዝ አስገዳጅነት በላዩ እንደሰፈረ ሁሉ፣ ከምናቡ ባይጠፋም፣ ጠባሳው ባይሰረዝም ተንገዋሎ እንደሚሄድ ሕዝብ በውል ተረዳ፡፡ ከቶውንስ በሞትና በህይወት መካከል ልዩነቱ ለጠፋበት፣ ለተራበ፣ ለተጠማና ስብእናውን ለተቀማ ሕዝብ ፍርሃት ምን ማለት ነው? ምኑ ምን እንዳይሆን ነው የሚፈራው? እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰው ሕዝብ ፍርሃትን አንኮታኩቶ በመጣል ሰብአዊ ክብሩን፣ ሀገሩንና ተስፋውን ከአምባገነኖች መዳፍ ለመንጠቅ ከተንቀሳቀሰ ወራት ተቆጠሩ፡፡ አምባገነኖችም ተራ በተራ ጽዋውን ለባለሳምንቱ እያስረከቡ ከሕዝብ ጫንቃ በሕዝብ ብርቱና የማይናወጽ ትግል እየተሸኙ ነው፡፡ አቶ መለስ እንዳሉት #ሕዝብ ከመሪዎቹ የተሻለ ነው$ና እነርሱ ያስጎነጩትን የግፍ ጽዋ አላስጎነጫቸውም፡፡ ከጫንቃው ላይ ግን አስፈንጥሯቸዋል፡፡ ገናም ያስፈነጥራቸዋል፡፡ አምባገነን መሪዎች መቼም ጥሩ የተውኔት ሰዎች ናቸውና ተውኔቱን ግን ቀጥለዋል፡፡

ቢደላን ኑሮ ትወናው እጅጉን እንድንስቅ ይረዳን ነበር፡፡ ነገር ግን የተሸከምነው መከራ የመሳቅ ኃይላችንንም ነስቶናል፡፡ ምዕራቡ ዓለም የአምባገነኖችን ተውኔት በሙዚቃ አቀነባብሮ ፈገግ እያለ ነው፡፡ እነሱ ቢስቁ ያምርባቸዋል፡፡ ግፉን ሁሉ አባቶቻቸው ከላያቸው አውርደውላቸዋል፡፡ እኛም ዛሬ ዋጋ መክፈል ታሪካዊ ግዴታችን ነው፡፡ ልንወጣው የማንችለው እዳ ግን አይደለም፡፡ ወደ መጀሪያው ሃሳቤ ልመለስ፡፡ ስለአንባገነኖች ተውኔት፡፡ ያለምንም ማጋነን ሁሉም አምባገነኖች የእኛዎቹን ጨምሮ ብርክ እንደያዛቸው መረዳት አዳጋች አይሆንም፡፡ የቢን አሊ ቢቀር በሚሊዬን የሚቆጠር ደህንነትና ፖሊስ የነበራቸው ሙባረክ አጠገባቸው ዘፍ ሲሉ አቶ መለስ ቢደነግጡ ምን ይገርማል? በሙባረክ መገንደስ ብዙ ሰው ቢደሰትም ክስተቱ የሕልም ያህል ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

የማያባራው የአምባገነኖች ተውኔት ብዙ አሳይቶናል፡፡ ሙባረክ ለ18 ቀናት ብዙ መቶዎችን በመግደልና አያሌዎችን በማቁሰል የግብጽን ሕዝብ ጽናት ተፈታተኑት፡፡ ሲያሰኛቸውም በዘመናዊነቷ የሚነገርላትን የካይሮን ከተማ ግመል የጋለቡ ደህንነቶቻቸውን በማዝመት ሠላማዊውን ትግል ለማኮላሽት ክተት አወጁ፡፡ ነገር ግን የግብጽ ወጣቶች ሞትን ባሸነፈው ፅኑ ሠላማዊ ትግላቸው አመከኑባቸው፡፡ ሙባረክ ደጋግመው ተውነዋል፡፡ ደጋግመን በኢትዮጵያችን እንደምንሰማው ሙባረክ አንድ ለእናቱ የግብጽ ዋልታ እና ማገር ነኝ አሉ፡፡ እርሳቸው ከሌሉ ግብጽ ውሃ እንደሚባላት፡፡ 7ዐ ቢሊዬኑንስ ማን ይዘርፋታል ብለው ሳይጨነቁላት የቀሩ አይመስልም፡፡ ወይ እንደ እኛ #ጠቅላይ ሚኒስትር በ64ዐዐ ብር ደመወዝ በችጋር ቢቆራመዱ በተሻላቸው ነበር፡፡ ሙባረክ እስከመጨረሻዋ ሰዓት የግብጽ ሕዝብ ኮንትራት እንዳስፈረማቸው፣ ሕገ-መንግሥቱ የሕዝብ በመሆኑ በሕይወት እያሉ እንዲጣስ እንደማይፈቅዱ ከፍ ብሎ የሚሰማ ቀረርቶ ሲያሰሙ ነበር፡፡ የግብጽ ሕዝብ ግን በታሪኩ ለመጀሪያ ጊዜ እውነተኛ ሕዝበ-ውሳኔ በማድረግ የእኔ የሚለውን ህገ-መንግሥትን እያፀደቀ ነው፡፡ ከሙባረክ ማግስት፡፡

ሊቀ-ጠበብቱ አቶ መለስም ካድሬዎቻቸው የኢትዮጵያን ሕዝብ እግር ከወርች አስረው የዘረፉትን የ99.6% ተውኔታ ቸውን ሕዝብ የሰጣቸው ኮንትራት አድርገው ተጨፈኑና ላሞኛችሁ ይሉናል፡፡ የሙባረክ አይነት ክርክር ልብ ከማድረቅ ባለፈ ምንም እንዳልፈየደ እያወቁ፡፡ ካስፈለገ ነገ ሌላ ማለት ይቻላል ብለው ነው? ወይንስ የተላበሱት ገፀ-ባህሪ ግድ ብሎዎት?

የሌሎቹን አገሮች ጉዳይ እንተወውና አገራችን ላይ እናተኩር፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከግብፁ ሠላማዊ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ጀምሮ አንፃራዊ በሆነ መልኩ ጥሩ ሽፋን እየሰጠ ይገኛል፡፡ ዋና ዋና ከተሞች አካባቢ እንኳን ለምንገኝ የአረብ ዲሽ ምስጋና ይግባውና ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የፕሮፓጋንዳ እሩምታ ነፃ ከወጣን ሰነባበትን፡፡ ስሌቱ ሌላ እንደሆነ መገመት ቢቻልም ነፃ ላልወጣው ወገናችን ቲኒሽ ፈንጠቅ ማድረጉ አይከፋም፡፡ ዝም ቢሉ ሕዝባዊ እንቅስቃሴው በኢትዮጵያ ይቀሰቀሳል ብለው እንደፈሩ ሊያሳብቅባቸው ሆነ፡፡ ይልቅስ እግረ መንገዳቸውን እራሳቸውን ከሌሎች እምባገነኖች እለይባቸዋለሁ የሚሏቸውን መላምቶች እያፈላለጉ የፃድቅነት መንገዳቸውን በቴሌቪዥናቸው ቀጠሉ፡፡ መሠረታዊ የአስተሳሰብ ለውጥ ተፈጥሮ ቢሆን ኑሮ ግን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የቸኩ ፕሮፓጋንዳዎች ተቀንሰው የህዝብን ድምፅ ማሠማት በጀመረ ነበር፡፡

ውሎ ሳያድር ተወዳዳሪ እንደሌለው የሚነገርለት ጭንቅላት መላምቱን አፈለቀ፡፡ አቶ በረከት በካፒታል ጋዜጣ ለ3ዐ ዓመታት እድገት ታይቶ በማይታወቅባቸው አገራት ሕዝባዊ እንቅስቃሴው እንደተቀጣጠለ ነገሩን፡፡ አክለውም በእርሳቸውና በአቶ መለስ መዳፍ ሥር ባለቸው ኢትዮጵያውያ ግን ይኸ ፈጽሞ እንደማይሳካ ምኞታቸውን አበሰሩን፡፡ ምክንያቱንም ሲቀጥሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ የእድገት ማማ ላይ ወጥቶ እየተምነሸነሸ በመሆኑ ከዚህ ድሎቱ ሊያላቀቀው የሚሻን አንዳች ኃይል እንደማይሻ በተለመደ አቢዬታዊ አነጋገራቸው ነገሩን፡፡ ልጅ ቢሮጥ አባቱን አይቀድምምና የእድገቱን ባቡር እያምዘገዘጉት ያሉት ሰው ከመፍትሔ ጋር በአንጡራ ሀብታቸው በኢ.ቲ.ቪ ብቅ አሉ፡፡ ተጠየቁ፡፡ በኢትዮጵያ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ የማይከሰተው ሕዝቡ በነፃ ምርጫ ውክልና የሰጣቸው በመሆኑ ኮንትራቱንም አክብሮ እንደሚሰራ ነገሩን፡፡ ይህን ይበሉ እንጂ አሁን ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ከሚታይባቸው የሰሜን አፍሪካና የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች የከፋ የኢኮኖሚ ድቀትና ፍፁም አፋኝ የሆነ የፖለቲካ ሥርዓት እየመሩ መሆናቸውን ለአፍታም ሊዘነጉት አይችሉም፡፡ ግራ መጋባት ይታይባቸዋል፡፡ ሕዝቡን ይተውትና ለምርጫ ዘረፋ በስራ ሸንግለው የሰበሰቧቸው አባላት በተለይም የወጣት ማህበራት እንዳይተዘቡዎት፡፡ ለነገሩ የወጣት ማህበራት አባላት ታሪካዊ ግዳጃቸውን ተወጥተው የባህር ላይ ኩበት በመሆናቸው ከጎነዎት እንደሌሉ አይዘነጉትም፡፡ አሁን ባደረጉት የማሞያ ምርጫ ደግሞ ሰዎች በማያውቁት በሌሉበት ‹ተመርጠው› መመረጣቸውን ጎረቤቶቻቸው እያበሰሯቸው ነው፡፡ ይኸን በመሰለ ሁኔታ ስለምን ኮንትራት ነው የሚያወሩት? ማነው ምስክረዎ? ለዚሁ ዓላማዎ ያቋቋሙት ጥላዎ የሆነው ምርጫ ቦርድ ወይንስ የአውሮፓ ሕብረት? ከዚህ ወዲያ ምን ተውኔት ይመጣል? ከዚህ ወዲያ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዴት ሊዋረድ ይችላል? ድምፁን የተነጠቀና አንደበቱን በግፍ የተሸበበ ሕዝብ መቼም ምንም አይልም ተብሎ ያልሰጠውን ኮንትራት መፈረሙ ይነገረዋል፡፡ ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ አይደል! ከአምባገነኖች መገለጫዎች አንዱ ይኸው ነው፡፡ ለሕዝብ ሥር የሰደደ ንቀት፡፡ ድሮውንም ሕዝብን ባይንቁ አምባገነን ባልሆኑ ነበር፡፡ ከሆኑ ደግሞ ንቀታቸውን በዚህ መልኩ ቢገልፁ አይገርምም፡፡ አንዳንዴ ምን አልባት የስለላ መዋቅራቸውና ካድሬዎቸቸው በሚሰጧቸው የተሳሳተ መረጃ ምክንያት ይሆን ብሎ ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን አራት ኪሎ ተቀምጠው አንገታቸው ሥር ያሉትን እጅግ ችምችም ብለው ተደጋግፈው የቆሙ የፊትበርን ጉረኖዎችና የሚኖርባቸውን የሕዝብ ብዛት እያዩ፣ ሕፃናት በገፍ በልመና አፋቸውን የሚፈቱባቸውን የአዲስ አበባ ጎዳናዎች እያዩ፣ አዛውንቶች በየፌርማታው ሲያጣጥሩና በየጥጉ ወድቀው ቁርና ሃሩር የሚፈራረቅባቸውን ኢትዮጵያውያን ድንገት ሳያማትሩ ቀርተው አይደለም ስለ ልማት የሚነግሩን፡፡ የኮንትራቱም ጉዳይ ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ ተራ ውሸት፣ አይን ያወጣ የሕዝብ ንቀት ነው፡፡

ሲጀምር አቶ መለስ ካሳለፏቸው 2ዐ ዓመታት እድገት አስመዘገብኩ የሚሉት በ7ቱ ነው፡፡ ቢሞቱ 13ቱን ዓመታት ማንሳትም አይፈልጉም፡፡ ማስረጃቸውም የእርሳቸው የማዕከላዊ ስታስቲክ ባለስልጣን ነው፡፡ ከዚያም ከዘለለ ካድሬዎቻቸው ናቸው፡፡ ካድሬ ደግሞ ምን አይነት ቁጥር እንደሚያቀርብ ግልጽ ነው፡፡ መረጃ እንዴት እንደሚሰበሰብ ጠጋ ብሎ ለሚያውቅ ሰው ይቅርና በሩቁ ያሉትም አጥኝዎች የመረጃዎቹን ታማኝነት ጥያቄ ውስጥ ማስገባታቸው አልቀረም፡፡ እነ አቶ መለሰ ግን የበሬ ወለደ የኢኮኖሚ ዕድገት ለጊዜውም ቢሆን ሕዝብን ለማዘናጋት ይበጃል እስካሉ ድረስ ይቀጥላሉ፡፡ የመሬት ይዞታው አልተቀየረም፡፡ የተቀየረ ነገር ካለ የህዝብ ቁጥር ነው፡፡ አሻቅቧል፡፡ መሬት ከተከፋፈለ በኋላ ወደ 14 ሚሊዬን
ለአቅመ አዳምና ሄዋን የደረሱ ኢትዮጵያውያን በወላጆቻቸውና በአያቶቻቸው ይጦራሉ፡፡ በችጋር እቶን ይበላሉ፡፡ ለእነ አቶ መለስ ይኸ እድገት ነው፡፡ ስለኢኮኖሚያዊው መስፈንጠር በሚያወራው ድርሰታቸውም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ከሚመረተው 94% ገደማ ለፍጆታነት እንደሚውል ተቀምጧል፡፡ በየትኛው ተረፈ ምርት ላይ ተመርኩዞ ኢኮኖሚው እንደሚስፈነጠር አቶ መለስ ብቻ ናቸው የሚያውቁት፡፡ አቶ ሶፊያን እንኳን ሊረዱት አይችሉም፡፡ ሃቀኛ የሙያ ሰው ከሆኑ፡፡ ከአዲስ አበባ ነዋሪ ወደ 5ዐ% ገደማ ሥራ አጥ ነው፡፡ ይኸም ለአቶ መለስ ዕድገት ነው፡፡ በዚህም ዕድገት ምክንያት ደግሞ በሰሜን አፍሪካ እና በመካከለኛው ምስራቅ የተከሰተው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ አይከሰትም፡፡ ትንታኔ የአቶ መለስ፡፡ ሕፃናትን ሻይ ለማጠጣት የብር ስኳር ፍለጋ ከሱቅ ሱቅ በአዲስ አበባ መንከራተት የተለመደ ሆኗል፡፡ ፈልጎ ማጣትም እንዲሁ፡፡ ይሁን እንጂ ይኸም ዕድገት ነው፡፡ በሥራ መግቢያ እና መውጫ ሰዓት የትራንስፖርት ዋጋ ሰማይ ቢነካም በእድገቱ ምክንያት ሰው ክብሩ ወድቆ በሀይገር እንደችቦ ታስሮ ሲሄድ ማየት በኢትዮጵያዊነት ላይ ተስፋ መቁረጥን ሊጋብዝ ይችላል፡፡ ይኸም ለእርሳቸው ዕድገት ነው፡፡ ይኸንም ትራንስፖርት በግፊያ እንኳን ማግኘት ያልቻለው ሕዝብ ረጅሙን ጉዞ ከመቅረት መዘግየት ይሻላል ብሎ እንደ ሲራራ ነጋዴ ይነጉዳል፡፡ ይኸ ከተማ አዲስ አበባ ወይንስ ሞቃዲሾ ብሎ መጠየቅ የማይጠበቅ አይደለም፡፡

በችጋር የሚቆራመደውን የገጠሩን ሕዝብ እንተወው፡፡ ለመሆኑ ከተሜው እንዴት ነው የሚኖረው? እንደ እቶ መለስ ተረት ላውራ፡፡ ልጁ አባቱን አስማት የሚያሳይ ሰው ት/ቤት ስለሚመጣ መግቢያ ስጠኝ ብሎ ይጠይቀዋል፡፡ አባትየው ሲመልስ እኔ አባትህ እያለሁልህ በ4ዐዐ ብር 7 ቤተሰብ አብልቼ አስተምሬ ሁሉን ችዬ የማኖር አስማተኛ እኔ ያለሁ የምን ሌላ አስማተኛ ያስፈልጋል አለ፡፡ ሁኔታው ከዚህም እጅግ የከፋ ነው፡፡ ይኸም ሆኖ ለአቶ መለስ እድገት ሞልቶ ተርፏል፡፡ ኢህአዴግ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ያሉ የጥራጥሬ እና ሌሎች ፍጆታዎችን ዋጋ በማስታወሻ ይመዘግቡ፡፡ እንዲሁም አሁን ያሉበትን ይመዝግቡ፡፡ በቲኒሹ 5ዐዐ% የዋጋ ጭማሪ በብዙዎቹ ላይ ማስተዋል ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ችጋርና ጭቆና አጉብጠውታል፡፡ ይሄ ግን ለእነ አቶ መለስ አይታያቸውም፡፡ ቢታያቸውም ማመን፣ ቢያምኑም መናገር አይፈልጉም፡፡ አዳዲስ ቃላት እየፈጠሩ ሕዝብን የተስፋ ሙልሙል ማስገመጥ እንጂ፡፡ ከዚያም ሲያልፍ ልዩ ልዩ በዓላትን መፍጠር ነው፡፡ ዳንኪራ ማስረገጥ፡፡ ኢህአዴግ ሥልጣን ከያዘ ያከበራቸው በዓላት ቁጥር ከፈጠራቸው ሥራዎች እኩል ሳይሆኑ አይቀሩም፡፡ ሕዝቡን በምን ያደንዝዙት?

ሌላም የማደንዘዣ ትንግርት ማስተዋል ይቻላል፡፡ የአውሮፓ እግር ኳስና የወጣቶች የፍቅር ሁኔታ በሬዲዬ፡፡ ከዚህ ውጭ ሌላ ያለ አይመስልም፡፡ ከጥዋቱ 1 ሰዓት እስከ ሌሊቱ አጋማሽ ድረስ ይቀጥላል፡፡ ኢህአዴግ ሥልጣን ከያዘ ጊዜ ጀምሮ ሲያሰኘው አደገኛ ቦዘኔ፣ ሲያሰኘው ባንክ ሰብሮ ለመግባት የሚከጀል እያለ የሚፈርጀውን ሲያሰኘውም ለእነ ቡጥሮስ ጋሊ ክብር ግዳይ የሚጥለውን ወጣት ከዚህ በዘለለ በጫት እና በአደንዛዥ እጽ ቢደነዝዝ ሰርግና ምላሹ ነው፡፡ ለምን ብሎ ለሚጠይቅ የግብጽ አይነት ገድል እንዳይሰራ ከፍተኛ ስጋት ስላለው ነው፡፡

የኢህአዴግ የማማለያ ሰነድ እንደሚያሳየው ከተሜነት ባለፉት 2ዐ ዓመታት አቅሙን አሟጦ ሊስፋፋ የቻለው 2% ብቻ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ኢህአዴግ የሳት አደጋ ማጥፊያ መኪና ያላቸው ከተሞች ከአዲስ አበባ ውጭ ይኸ ብሎ መንገር አይቻለውም፡፡ የጤናው ክፍል አደገ ተመነደገ በሚባልበት አገር የትኛው የመንግሥት ሆስፒታል ኤም.አር.አይ ይቅርና ሲቲ ስካን እንዳለው አቶ መለስ ሊነግሩን አቅም የላቸውም፡፡ ከተሜነት በገደምዳሜ መሆኑ ነው፡፡ ግን በደፈናው ስለኢኮኖሚው ማደግ አውርተው አይጠግቡም፡፡ ስራቸውን የሚወዱት እንዲሁ በዘፈቀደ መናገር ስለሚችሉ ይሆናል፡፡ ከ2ዐ ዓመት በኋላም የማይሰለች ድንቅ ሥራ፡፡ እንደጓዶቻቸው ከረጅም አመት ግልጋሎት በኋላ እንኳን የማይደክሙ እና የማይሰለቹ ድንቅ ፍጡር፡፡

በአጠቃላይ በሚከፍለው ግብረ እየተራበ የሚያበላቸውን፣ እየታረዘ የሚያለብሳቸውን፣ የእሳት አደጋ መኪና ሳይኖረው በኮብራ የሚያንፏልላቸውንና እንደግዑዝ በየታዛው ወድቆ እነርሱን በሰገነት የሚያኖረውን ኢትዮጵያዊ ጨርሶ መናቅ ከነውርም በላይ ነው፡፡ አይናቸው በንዋይ እና በስልጣን ግርዶሽ ተከልሏል፡፡ ንቀታቸውም ከፍተኛ ስለመሆኑ ብዙ አያነጋግረም፡፡ እነ አቶ መለስ በሚናኙበት አዲስ ዘመን ስማቸውን አንዴ ቶፊቅ ሌላ ጊዜ ሌላ በማለት የአምባገነን ትንተናቸውን ያስኮምኩምናል፡፡ በአፋቸው በኢትዮጵያ ሊከሰት አይችልም ይበሉ እንጂ በልባማቸው ግን የሚሉትን አያምኑም፡፡ ለዚህም ነው እንደለመዱት የኦሪት ፍየል ፍለጋውን ከወዲሁ የተያያዙት፡፡ በሌሎች አገሮች ሕዝብ ያለመሪ እና ተመሪ ምን አይነት ሚና እንደተጫወተ እያዩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን በተቃዋሚዎች ካልተመራ በራሱ ምንም ማድረግ እንደማይችል ይነግሩናል፡፡ አክለው ደግሞ አቶ መለስ
ሕዝብ ከመሪዎቹ የላቀ ስለመሆኑ ይነግሩናል፡፡ የሚሉትን ካመኑበት የኢትዮጵያ ሕዝብስ ለምን መሪዎቹን ይጠብቃል? ይኸ አይን ያወጣ ንቀት ነው፡፡ በሌላ ወገን ለገበያ ፍጆታ በማይቀርበው ትንታኔያቸው ኢትዮጵያም ውስጥ ሊከሰት እንደሚችል ያምናሉ፡፡ ስለዚህ ጥርሳቸውን ነቅለው ያደጉበትን ሴራቸውን ተግባራዊ ለማድረግ መደላድል እየፈጠሩ መሆኑ ነው፡፡ በዘመቻ አዲስ ዘመን፡፡ እንደለመዱት መሳሪያ እሰው ቤት በማስቀመጥ፣ ቦንብ አውቶብስ ውስጥ አሊያም ግንብ ስር በማኖር እነከሌ የመሩት ዘመቻ በረቂቁ ደህነነቶቻው አንደከሸፈ ይነግሩናል፡፡ እንዲህ ነው የ‹ሕዝብ ደህንነት› ሕዝቡም አደጋው በቁጥጥር ሥር በመዋሉ እንዲረጋጋ ይነገረዋል፡፡ ይኸ የተለመደ የማፍያ ታክቲካቸው ነው፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ የማይመጥን አመራር ከኢህአዴግ ወዲያ ከወዴት ይምጣ? አሁን ግን ነገሩ ሁሉ ለየቅል መሆኑን ልብ ቢሉ መልካም ነው፡፡

አቢዮታውያን ሆነው እንደቀሩ ሁሉ አሁንም የቀደመ ትወናቸውን የሙጥኝ ማለት የመረጡ ይመስላል፡፡ ይኸ ግን የማይማሩ ወይንም ሁልጊዜም ከማደናቆር ውጭ ከስህተታቸው ሊታረሙ እንደማይችሉ ማሳያ ነው፡፡ ነገር ግን ያልተቀየሩት እነርሱ እንጂ ዓለም እየተቀየረ ነው፡፡ ለጥቅሞቻቸው ሲሉ የንፁሃንን ደም አይተው እንዳላዩ ያልፉ የነበሩ አገሮች ከአምባገነኖች ጋር በመዶለት ለዓለም ሠላምም ሆነ ብልጽግና ሊያመጡ እንደማይችሉ ገብቷቸዋል፡፡ ሕዝቡም እየተለወጠ ነው፡፡ ሕዝብ በፍርሃት እርሃብና ጭቆናን ከመከናነነብ ፍርሃቱን አሸንፎ የክብር ሞት መሞትን መርጧል፡፡ ግብጽ ትመስክር፡፡ ሌሎችም፡፡ ስለዚህ ይልቅስ እራሳችሁን የኢትዮጵያን ሕዝብ ጥያቄ በአግባቡ መመለስን አስለምዱት፡፡ ይኸን ጊዜ ያምርባችኋል፡፡ ሕዝብ በመደለያ በአለቀ ሰዓት ቢመለስ ኑሮ በሳውዲ ወጭ እንዲሆን የታዘዘው 38 ቢሊዬን ዶላር በረዳው ነበር፡፡ ሕዝብን በመሸንገያ ዝም ማሰኘት እንደማይቻል ብዙ የማይሞቱ ምስክሮችን ማቅረብ ይቻላል፡፡

ያ አይሆንም፡፡ ሕዝብ ለነፃነቱና ለክብሩ የሚሰጠውን ዋጋ በገንዘብ ለመተመን ባይሞከር፡፡ የኢህአዴግን አስተሳሰብ ተቀብለው አሊያም ተገደው የኢህአዴግ አባላት የሆኑም አሁን ያለውን ልዩ ሁኔታ በጽሞና እንደሚረዱት እገምታለሁ፡፡ እነርሱም ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ችግሩም ዘልቆ እንደሚሰማቸው መገመት ይቻላል፡፡ በግብጽና በቱኒዚያ የነበሩ በሚሊዬኖች የሚቆጠሩ የገዥ ፓርቲዎች አባላትም ዞሮ ዞሮ ከወገናቸው ጋር መቆማቸውን በተግባር አይተናል፡፡ ከጥቂቶች በስተቀር፡፡ ደህንነቱና ፖሊሱም ቢሆን እንዲሁ፡፡ የመንንም ሌሎችንም ማከል ይቻላል፡፡ መልእክቴ ግልጽ ነው፡፡ ኢህአዴግ ማደናገሩንና ፌዙን ትቶ የኢትዮጵያን ሕዝብ ጥያቄዎች በአስቸኳይ ይመልስ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዚህ ያነሰም ከዚህ የበዛም አይፈልግም፡፡ በአሁኑ ሰዓት፡፡

እነ አቶ መለስ ይኸን መንገድ ካልመረጡ፤ አቶ በረከት በአንድ ወቀት እንዳሉት ይኸ ድርጅት ብዙ ፈተናዎችን በአሸናፊነት የተወጣ ድርጅት ነው እያሉ በየዋህ ዘላለማዊ ጀብደኝነታቸው ባይቀጥሉ ይመከራል፡፡ ኢህአዴግ ለ2ዐ ዓመታት የኢትዮጵያን ሕዝብ ከፋፍሎ ለመግዛት የአውተበተው የልዩነት መረብ በማንም ሳይሆን በራሱ በኢትዮጵያ ሕዝብ ተበጣጥሷል፡፡ አሁን በምናያቸው የሰሜን አፍሪካ እና የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች የሕዝብ አንድነት ብቻ ሳይሆን የዓላማ አንድነትም ምን ያህል ቁልፍ ሚና እየተጫወተ እንደሆነ መረዳት ይገባል፡፡ የኢህአዴግ መሪዎች አሁንም ከደመናው ካልወረዱ የኢትዮጵያን ሕዝብ በመከፋፈል የልዩነት ግንቦች መሆንን ሊመርጡ ይችላሉ፡፡ ያለፉት 2ዐ ዓመታት፣ ቀደምት የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክም በተለይም ደግሞ አሁን በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር እየተፈጠረ ያለው የኢትዮጵያውን መሰባሰብ ለዚህ የህልም ሩጫቸው ፍቱን ማርከሻ ነው፡፡ አቶ መለስ የጭቆና ቀንበረዎን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጫንቃ ላይ በአስቸኳይ ያንሱ፡፡ እርስዎም በአስቸኳይ ነፃ ይውጡ፡፡