ስጋት አርግዘን ስጋት ለብሰናል-የመን በግሩም ተ/ሀይማኖት
በየመን ያለ ሀበሻ ቁጥሩ ሲጠራ የሚያምን የለም::ትክክል የማይመስል ነገር ነው::በህጋዊና ህጋዊ ባልሆነ ሁኔታ የመን ውስጥ ያለ ኢትዮጵያዊ ከ80,000 በላይ ነው::5000 የምንጠጋው በUNHCR ስር ያለን ስንሆን ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለማቋረጥ እና የመን ለመኖር ከጅቡቲ..ከሱማሊያ..ተነስተው በባህር በየእለቱ የሚገቡትን መገመት ይከብዳል::ከ4,000,000 በላይ ትውልደ ሀበሻ አለ::ከአረብኛው ቀጥሎ ህዝቡ በሰፊው የሚናገረው አማርኛ ቋንቋ ነው ማለት ይቻላል::ይህ የሚያሳየው የመናዊያን እና ኢትዮጵያዊያን አብረው የኖሩ ህዝቦች መሆናቸውን ነው::ነገር ተገልብጦ ሆኗል::ትላንት ችግራቸውን ለመቅረፍ ወደ ሀገራችን እንዳልተሰደዱ ለሀበሻ ያላቸው ጥላቻ ኢትዮጵያን እጀ ሰባራ ያሰኛታል::ለነገሩ እንኳን የተጠለለባት ከአብራኳ የወጣውስ ነካሽ እንጂ አይዞሽ ባይ መች ሆናት?…ቢሆን ኖሮ ከነቀዞች ማላቀቂያው ሰዓት አሁን ነበር::
የመን ስላለ ሀበሻ ይህን ያህል ካልኩ ወደ ተነሳሁበት የስጋት መስመር ላቆልቁል::በአረቡ አለም እየተቀጣጠለ ያለው የለውጥ ማዕበል ማነው ባለተራ እያለ የሚያዳርስ ይመስላል::ወጉ አይቅርብኝ ብለው ነካ..ነካ..የሚያደርጉ ሀገራትም አልጠፉም::እኛ በስደት ከእጅ አይሻል ዶማ ኑሮ የምንኖርባት የመን አንዷ የእንቅስቃሴው ማዕበል የሚያናውጣት ነች::የመፋጠጡን ነገር ትውኝ::ተፋጠዋል….እኛም ሊመጣ የሚችለውን ችግር አስበን ስጋት አርግዘን…አጋት ለብሰን…በስጋት አንሾካሹከን ነው ያለነው::ለ32 አመታት ሀገሪቷን ሲመሩ የነበሩት አሊ አብደላ ሳላህን ከስልጣን እንዲለቁ የሚጠይቁ ወገኖች ብቅ ካሱ ሳምንታትን እያስቆጠሩ ነው::በዛው መጠን ደጋፊዎቻቸውም “ማፊሽ አህሰን አሊ አብደላ ሳላህ!!”የሚል የዘውትር መፈክራቸውን እያሰሙ ፎቶ ይዘው አደባባይ ይውላሉ::”..እንደ አሊ አብደላ ሳላህ ጥሩ የለም “ማለት ነው::ይህ በሰነዓ ነው::በትእዝና በአደን ደግሞ ከዚህ የተለየ አመጹ የከፋና ሰልፍ የሚወጡትም ቁጥር የበዛ ነው::በተለያየ ቦታ ውጥረት ውስጥ ያለችው የመን የእርስ በእርስ ጦርነቱ ረገብ በማለቱ ህዝቡ ተደስቶ ነበር::አሁን ከቱኒዝ የተነሳው የአመጽ ማዕበል ግብጽን..የመንን ጆርዳንን..ሊቢያን,ባህሬንን..ሳዑዲ..ኦማንን. መነካካቱ የሚታወቅ ነው::የመን በዩንቨርስቲ ተማሪዎች የተጀመረው ሰላማዊ ሰልፍ በቶሎ እንዲበርድ ፕ/ት አሊ አብደላ ሳላህ አስበው በዩንቨርስቲ ውስጥ የሚከፈለውን ክፍያ ከመቀነስ ጀምሮ በነጻ እስከማድረግ ያለ እርምጃ ወስደዋል::
የሀገሪቷ ፕሬዘዳንት የስልጣን ዘመን ማብቂያ 2013 ነው::ፕሬዘዳንት አሊ አብደላህ ሳላህ ከ30 አመት በላይ አስተዳድረዋል::ሀገሪቷን አሳድገዋታል የሚሉ ሞልተዋል::ምን ያሳድጋታል ኑሮው ከፋ የሚሉት ሕዝቡ ሁኔታው እና ያለው ችግር ፈንቅሎት ነው ተቃውሞ የወጣው የሚሉ ናቸው::መንግስት ሰሞኑን በተቃዋሚዎቸ የተደረገውን የሰላማዊ ሰልፍ ሙከራ በማየት 10% የደሞዝ ጭማሪ ለወታደሩ ክፍል 4% ደግሞ ለመንግስት ስራተኞች ጭማሪ ቢያደርግም ካለው የኑሮ ውድነት አንጻር ተነጻጻሪ አይደለም የሚሉ ወገኖች አሉ::ሁኔታው ለፕሬዘዳንት አሊ አብደላ ሳላህ አሳሳቢ ስለሆነ እንደሆነ የደሞዝ ማሻሻያ ያደረጉት ተቃዋሚዎችም ሆን የመገናኛ ብዙሀን ይጠቅሳሉ::ፕሬዘዳንቱን ለ2011 ማብቂያ ስልጣናቸውን እንዲለቁ የጠየቁት ተቃዋሚዎች ሰነዓ ውስጥ ዳይሪ የሚባል ዩንቨርስቲው ያለበት አካባቢ ድንኳን ጥለው ሲቀመጡ የፕሬዘዳንቱ ደጋፊዎችም ያንኑ አድርገው ፊት ለፊት ተፋጠዋል::አሁን አሁን የድንኳኑም መጠን እየጨመረ ነው::ታህሪር የሚባለው ቦታም እንዲሁ የፕሬዘዳንቱ ደጋፊዎች ድንኳን ጥለው ተቀምጠዋል::ትላንት/08/03/11 ማታ ላይ ስለሁኔታው ለማወቅ ሄጄ ሳለ ድንኳን የጣሉበት ቦታ መጠን ጨምሮ አካባቢው በሰው ተጨናንቆ መንገድ ተዘግቶ አየሁ::የሚገርመው ደግሞ ዝግጅታቸው ተጠናክሮ ድንኳኖቹ ውስጥ ለምሽግ ይሁን ብርድ ለመከላከል ባላወኩት ሁኔታ በብሎኬት ግንብ ይገነባል::ያለው የጥበቃ ሁኔታም እየተጠናከረ ፍተሻው እየከበደ ነው::ያሳስባል አስጊ ነገር አርግዧል::ደጋፊዎቹ ምግብም ሆነ የቀን ወጭ ተችለው እንደሆነ የተቀመጡት ተቃዋሚዎች ይናገራሉ::ይህ ህዝቡ ሁሉ የሚያውቀው ነገር ነው::
በየመን ካለው የውጭ ዜጋ ከብዛት አንጻር ተጎጂ የሚሆነው ሀበሻ እንደሆነ ይታወቃል::ኤምባሲውም ባለፈው አርብ ህዝቡን ሰብስቦ “..በጊዜ ወደቤት ግቡ….”ብሏል::
“ሰውየው ንግግር አደርጉ..”ያሉት ትናንሽ ጥቅማ ጥቅም ናፋቂዎች ወደ ኤምባሲ እየቃረሙ የሚወስዱትን ወሬ ጥለው የኤምባሲውን ለእኛ ሲያቀብሉ “..በጊዜ ወደቤት ግቡ ሞባይላችሁን ካርድ ሞልታችሁ አስቀምጡ አደጋ ወይም ችግር ሲገጥማችሁ ወዲያው ደውሉ..ኮሚኒቲ ተመዝገቡ ችግር ቢነሳ እንኳን ኢትዮጵያዊነታችሁን ታውቆ ወደ ሀገር እንድትገቡ…”አሉ አዲሱ ቆንጵላ ሲሉ አበሰሩን ::ጽድቁ ቀርቶ በቅጡ በኮነነኝ ይላሉ አባቶቸ::በሞባይል ተጠርተው ሊደርሱ አይደለም::ግፍ የሚፈጸምባቸው ዜጎቸ ኤምባሲ ሄደው አቤት!!!..ሲሉ እኛ ለገረድ አልመጣንም ማለታቸው ያቆሰለው ሁሉ አረ!!…ዛሬ ምን ታያቸው?ገንዘብ ፈልገው?ሲል ተደምጧል:: ኮሚኒቲ ለመመዝገብ ፓስፖርት ወይም መታወቂያ የሚያስፈልግ ሲሆን ያ-ካለ ኮሚኒቲ መመዝገቡ ለምን አስፈለገ?ኢትዮጵያዊነትን አይገልጽም?
አንደኛ አልቀርብ ያለውን ህዝብ ወደ ኤምባሲውና ኮሚኒቲው ማቅርቢያ መንገድ ነው ፍላጎታቸው::ምንም እንደማይጠቅማቸው ያወቁትን ኤምባሲ ቅንጣት እምነት አይጥሉበትም::የተበደሉ ወገኖች እንኳን ሲግጥም..ኩሩቤል ጋር ሄዱ ነው የሚባለው::ማንም ኤምባሲ ሂድ አይልም::ኩሩቤል ማነው?ትሉ ይሆናል ዛሬ ርዕሴ ስላልሆነ በቀጣይ ከunhcr ጋር በተያያዘ እመለስበታለሁ::
ሁለተኛ 3000 ሺሀ የነበረውን ቀንሰን በ2000 የየመን ሪያል እያሉ እያስከፈሉ ስለሆነ የሚመዘግቡት ለጥቅም ሲሉ ነው እያለ ስደተኛው ሲያማርር ተሰምቷል::መሸጥ የለመደ እናቱን ያስማማል ነው::ሁሉን መሸጥ የለመደ መንግስት ጭፍራ ሆነው ሌላ ምን ያርጉ?እዚህ ያሉ እህቶች ያሳዝኑኛል::በጉለበታቸው ፋገው ያመጡትን ዝቅተኛ ክፍያ ሊበላቸው ያሰፈሰፈው ብዛቱ…ዳላላው:መኖሪያ ፍቃድ አስሪው..የትዳር ጭንብል ያጠለቅው ወንድ..ኤምባሲው..ብቻ ሁሉ የያዘትን ሊያራግፋቸው ነው የሚጥረው::በእርግጥም አራግፈው መታከሚያ…ሀገር መግቢያ የሚያጡ ሞልተዋል::
ማንም በኤምባሲው እምነት አላሳደረም::ምክንያቱም ከዚህ በፊት ኤምባሲው ለዜጋው ምንም ሲያደርግ አይታወቅም::ከ80 ሺህ በላይ ዜጎች ያሉት ኤምባሲ የቀብር ቦታ ጥይቆ ያላዘጋጀ ዜጋው ሲሞት ለመቅበር ቦታ ጥፍቶ በየፍሪጅ ውስጥ ሬሳ ሲበሰብስ ዝም የሚል ኤምባሲ..ተበደልን ሲባል የራሳችሁ ጉዳይ የሚል ኤምባሲ…ዜጎቹ የመኖሪያ ፍቃድ ማሰሪያ ቦታ አጥተው ጀበሀ የሚባል የኤርትራ ተቃዋሚ ቡደን የየመንን መንግስት አስፈቅዶ ማሰራት ሲጀምር,,ብሎም ከ5000 በላይ ኢትዮጵያዊያን ከ100-300 ዶላር ተበልተው ሲቀሩ ምን አገባን ያለ ኤምባሲ ሞባይላችሁን ካርድ ሙሉ የሚሉት ቢጠሩ ሊመጡ ነው? ሁሉን ያነጋገረ ጉዳይ ነበር::የቀብር ቦታ እንኳን ከቻይኖች ጋር ጥገኛ ሆነን ነበር::እነሱም ከልክለው የተቀበረውንም የሀበሻ ሬሳ አውጥተው ሲጥሉ ዝም ያለ ኤምባሲ ቢደወልለት ይደርሳል?እዚህ ያለ ሀበሻ በሙሉ የሚያውቀው ነገር አለ ሲሞት የመስሊም ስም እየተቀየረለት ነው የሚቀበረው::ይህን ኤምባሲውም ያውቃል::
ውጥረቱ ያየለበት ምስኪን ስደተኛ ወደ UNHCR ቢሮ ብቅ ቢልም ተሰፋ አስቆራጭ ምላሽ አግኝቶ ተስፋው ጭልሞበት ስጋት ባቻ ሳይሆን ፍርሀቱም አይሎበት እንዳለ….አለ::<<..ምንም ልናረግላችሁ አንችልም::ባለው ሁኔታ ሁለት ቦታ ቢሯችንን ዘግተናል::የከፋ ነገር ቢምጣ እዚህ ያለውን ቢሮም ዘግተን እንሄዳለን::ባጀት ስለሌለን ዘግተን ከመሄድ ውጭ ምንም ልናረግላችሁ አንችልም::..>>ለሚመለከተው ሁሉ አቤት ቢባል ምላሽ የለም::
እዚህ ያለ ሀበሻ የየመን ፖለቲካ አይደለም ችግሩ::ሀገርስ ቢገባ የሚጠብቀው ምንድን ነው?ብዙውም አሁን ያሉት ፕሬዘዳንት አሊ አብደላ ሳላህ እንዲቀጥሉ ነው ፈጣሪውን የሚለምነው::ምክንያቱም ህዝቡ ለሀበሻ ያለው አመለካከት ጥሩ ስላልሆነ ችግር ቢነሳ ይጨርሱናል የሚል ፍርሀት አለው::በእርግጥም ሀቅ ነው::ሼህ የሚባሉ የጎሳ መሪዎች.አሉ እያንዳንዳቸው የታጠቀ ሰራዊት አላቸው::ለሀበሻ ፍርሀቱ ብዙ ነው::የምናሳዝን ፍጥረት…ኤምባሲው በስሩ ላሉ አልሆነላቸው:unhcrም ቢሆን የፈለጋችሁትን ሁኑ ነው ያለው መጨረሻችን ምን ይሆን?
ሀገር አንገባ እኛስ ጫንቃችን ላይ የተጎበረ ነቀርሳ አለ አይደል? እስከመቼ በመንከራተት እና በስደት እንኑር?
እስኪ ሰላም ያሰንብተንና እንገናኝ
ቸር ሰንብቱ