ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ታሰረ
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ በፒያሳ ከሚገኝ፡የኢንተርኔት ካፌ ሲወጡ ብዛት ባላቸዉ የፌደራል ፖሊሲ ታጣቂዎች መያዛቸዉን ከአዲስ አበባ የደረሰን ዜና ያመለክታል። የፌደራል ፖሊስ ታጣቂዎች ምንም አይነት የፍርድ ቤት መጥሪያም ሆነ ፍቃድ በእጃቸዉ ያልነበረ ሲሆን አቶ እስክንድርን በቀጥታ በፌደራል ፖሊሲ ጽ/ቤት ነበር የወሰዷቸዉ።
በፌዴራል ፖሊሲ ጽ/ቤት እንደደረሱ የፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር፣ ቁጣ በተሞላበት ሁኔታ እንዳነጋገሯቸዉ የደረሰን ዜና አክሎ ይገልጻል። «በቱኒዚያና በግብጽ እየሆነ ያለዉ በኢትዮጵያም እንዲነሳ አመጽ እያነሳሳህ ነህ። አንድ ነገር ቢፈጠር መጀመሪያ ተጠያቂ የምናደርገርዉ አንተን ነዉ» በማለት ጠንካራ ዛቻና ቁጣ እንደሰነዘሩባቸውም ለማወቅ ችለናል።
በቅርቡ አገር ዉስጥ በሚታተም ጋዜጣ «በቱኒዚያና በግብጽ የሚታየዉ በኢትዮጵያ እንዳይከሰት ምን መደረግ ያለበት ይመስልዎታል ?» ለሚለዉ ጥያቄ ፣ «በሕገ መንግስቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ ምርጫ መጥራት፣ፓርላማን ማፍረስ ይችላል። በመሆኑም አሁን ያለዉን ፓርላማ ፈርሶ ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንደገና አዲስ ምርጫ ቢደረግ፣ የፖለቲካ መረጋጋት ስለሚያመጣ በግብጽ የታየዉ ላይታይ ይችላል» የሚል መልስ በመመለሳቸውና በቅርቡ በተለያዩ ድህረ ገጾች የቀድሞ የኢታ ማጆር ሹም የነበሩትን ጄነራል ጻድቃንን በማንሳት በጻፉት ጽሁፍ፣ ባለስልጣናቱ እንደተናደዱ የሚገልጸዉ የደረሰን ዘገባ፣ የፖሊሱ ሃላፊ የጄነራል ጻድቃን ፎቶ ያለበትን የአቶ እስክንድር ጽሑፍ ቅጂዎች በእጃቸዉ ይዘዉ እንደነበረም ይገልጻል።
«ምን አድርግ ነዉ የምትሉኝ ? መጻፌን ላቁም ወይ ?» ብለዉ አቶ እስክንድር ሲጠይቁ፣ የፖሊስ ሃላፊዉ «እርሱን አላልንህም፤ መጻፍ ትችላለህ። ነገር ግን መስመር አልፈሃል። በእጃችን ብዙ መረጃዎች ከወዲሁ ይዘናል። አንድ ነገር ቢሆን አንለቅህም» የሚል ምላሽ ነበር የሰጡት።
የፖሊስ ሃላፊዉ ሕዝቡ እንደ ግብጽ ቢነሳ፣ አገዛዙ የሕዝቡን ግፊት መመከት እንደሚችል ሳይገልጹም አላለፉም። «ኢሕአዴግ ማንኛዉም ነገር ያከሽፋል፤ ይቆጣጠራልም» ነበር ያሉት።
አቶ እስክንድር በዚህ ሳምንት ለአንባቢያን ሊያቀርቡት ያዘጋጁትን ጽሁፍ ጨምሮ በርካታ በእጃቸዉ የነበሩ ወረቀቶች የተወሰዱባቸዉ ሲሆን ፣ የዛሬዉ ክስተት ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ቃሊቲ በግፍና በጭካኔ ከመወሰዷ በፊት ፌደራል ፖሊስ በርሷ ላይ ሲያደርግ የነበረዉን ዛቻና ወከባ የሚያስታወስ እንደሆነ የደረሰን ዘገባ ይጠቁማል።
በግብጽና በቱኒዚያ የተፈጠረዉ ሁኔታ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያንን ዉስጥ ዉስጡን እያነጋገረ ሲሆን በአቶ እስክድንር ላይ የተወሰደዉ እርምጃ ገዢዉ ፓርቲ ዉስጥ ድንጋጤና መረበሽ እንደፈጠረ የሚያሳይ እንደሆነም በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸዉ አንድ የፖለቲካ ተንታኝ ይናገራሉ። «የምንሰማቸዉ ዜናዎች ለመለስ ዜናዊ ደስ የሚያሰኙ አይደሉም። አስተዋይ ቢሆን ኖሮ ከሕዝብ ጋር ተጣልቶ የትም እንደማይደረስ ከሙባረክና ከቤን አሊ ይማር ነበር። እነ መለስ እስክንድርን አስሮ ከማስፈራራት ይልቅ የመከራቸዉን ምክር ያደምጡ ነበር።» ሲሉም አስተያየት ሰጥተዋል።