የምሁራን ድርሻ በዘመነ ወያኔ ? ሎሚ ተራተራ ነኘ

ሐገሬን እያሉ ለወገን ነፃነት፤ ላንድነት የሞቱት ያለቁት፤
ለዳር ድንበራቸው፤ በጀግነነት ቆመው መስዋእት የሆኑት፤
ምነው በተነሱ፤ ምሁራኑን እና ይህን ትውልድ ባዩት፤

መማረ፤ ማወቅና መመራመር እጀግ መልካም ነው። የት እንዳለን ምን እንደሚያስፈልገን የምንፈለገውን እንዴት ልናገኝ እንደምንቸል ያመላክታል።ካልቻልንም ደግሞ ለመን እንዳልቻልን፤ምክነያቱን በብቃት መረጃዎችን በማቅረብ ያረጋገጣል። ምሁራንም ህዝብን ከተሳሳተ አካሄድ የመመለስና እውነትን ተናግሮ ካድርባይነት እራስን አንጽቶ ትውልድን አቅጣጫን የማሳየት ሃላፊነት ያለበት ክፍል እንደሆኑ አጠያያቂ አይደለም።

ዳሩ ምንያረጋል ይህ ትውልድ አልታደለም እና በመስለው መንገድ የሀገሩን ውድቀትና ቸግር ለመቅረፍ ሲታገል ይታያል። ከአገር ገንጣዩና ከፋፋዩ፤ ጨካኙ ወያኔ መንገጋ ለመላቀቅ በውስጥም በውጪም ጥረት እይደረግ ነው። ዋናው አላማዬና ላተኩረበት የፈለኩት ግን ለሃያ እረጅም አመት ውጤት ያላመጣ ትግል ልንታገልና የድል ባለቤት ልንሆን ያልቻልንበትን ጉዳይ ምሁራኖቸ እንዲያዩት ፈልጌ ነው። ለምሳሌ ያክል፦

አንድ የህክምና ባለሞያ ሜዳ ላይ ወድቆ በህመም የሚስቃይ ስው በመንገድ ሲያልፍ ቢያየው ምላሹ እንዴት ሊሆን ይችላል ? ቆም ብሎ ኮቱን አውልቆ የሞያዬ ግዴታ ነው በማለት የወደቀውን በሽተኛ አክሞ ለማዳን ባይቸልም እንኳን፤ እርዳታ ለመስጠት ፍቃደኛ በመሆን መልስ ይሰጣል? ወየስ “መሃንዲስ” ነኝ ብሎ አየት አርጎ ከሌላው ህብረተስብ ጋር ተቀላቅሎ ያልፋል? ይህንን ነው ምሁራኖች እንዲያዩት የምፈልገው።

ዛሬ አስከፊ የሆነው የወያኔ አገዛዝ ህዝባቸንን በረቀቀ ሁኔታ እያስቃየ ከአንደኛው የግፍና የጭካኔ አገዛዝ ወደሌላኝው እየተሸጋገር ይገኛል። በፍጹም ጭካኔና ስበአዊነትን ባላማከለ ሁኔታ የግፍና የጭካኔ እኩይ ተግባሩን በስፋት እንደወረርሺኝ በሽታ እያስፋፋ ባለበት በዚህ ዘመን፤ የምሁራኑ ድርሻ ከፍተኛ ነው። ምሁራኖቸ መድሃኒቱ እንዲህ ነው ብለው ሕዝብን አቅጣጫ ማሲያዝ ምነው አቃታቸው?

አዎ ምን አልባት አዬ ማን ያልሞከረ አለና እየተሰደብንና እየተዋረድን ስለምንባረረ ነው እንጂ የሚል መልስ ሊስጥ ይቸል ይሆናል። ሆኖም በ እኔ እምነት በቂ አይደለም፤ የሀገር መውደቅና መፍረስ ጉዳይ ያመረረውና ያንገሸገሸው ትውልድ ከዚሀም በላይ ቢል አይፈርድበትም ነው የምለው። መዘንጋት የሌልብን ነገር እኮ ምሁሮቻችንን እንዳናከብር እርስ በእርሳቸን እንድንራቆትና የመከባበሩ ባሕልና ወጉ እንዲጠፋ ተደርጎል። ሌትና ቀን የመጠላለፍን ሴራ እያሴሩ የሚከፋፍሉንና ኢትዮጵያዊ መንፈስ እንዲጠፋ የጥላቻ መርዛቸውን የሚረጩብን ወያኔዎችና አድርባይ ምሁራኖቸም ጭምር እንደሆኑ መርሳት የለብንም።

ሙሁራኑ ክፍል እኮ ሌላው ያላየውን ለማሳየት ያልተረዳውን ለማስረዳት ሲሞከር ሊገጥመው የሚቸለውንም ውጣ ውረድ ግምት እውስጥ ማስገባት አለበት።የተማርው ክፍል የሞያ ግዴታውን የመወጣት ኢትዮጵያዊ ታላቅ ሃላፊነትም አለበት። እንዳንዶቸ ምሁራን ነን ተብዬዎቸ እኮ እንደ አምላክ አምልኩን፤ የኛን ቃል እንደ እግዚአብሄር ቃል ካልስማችሁ ምን አጨቃጨቀኛ በሚል ጠባብ አስተሳስብ ውስጥ ያሉትን ቤት ይቁጠረው። የኔ ኑሮ ከተሟላ ቤተስቦቼን በስረአት ከመራሁና ካስተዳደርኩ ምንገዶኝ የሚሉም ሞልተዋል። ሕዝብ አክብሮና ቃላቸውን ስምቶ በተደጋጋሚ ለመመራት ፍቃደኝነቱን አሳይቷል አሁንም እያሳየ ነው።

የሃገር ውድቀት የተማረ ወይም ያልተማረ ጥያቄ አይደለም። ሐገር ሲፈርስና ህዝብ ሲበተን ግን ምሁራኑ በእትዮጰያዊ አንድነት በጽናት በመቆም ታግሎ በማታገል አገሩን ነፃ የማውጣት የውዴታ ግዴታም ነው። ከሁሉም በላይ በተለይ ምሁራኑ ክፍል ትልቅ የታሪክ ሃላፊነት አለበት እላለሁ። የኛ ምሁራኖቸ ግን በየተስማሩበት የሞያ መስክ በጥገኝነት ለሚኖሩበት አገር እያገለገሉ ይገኛሉ። ቤተስባቸውንና ልጆቻቸውን እየተንከባከቡ በመኖረ የ ኢትዮጵያ ውድቅት ከላይ እንደመአት እንደወረድ ዱብዳ ነገር በመቁጠር ፤ በየመስኩ ለሃገሩ የሚታገለውንና የሚጮኀውን ዜጋ እንደፊልም እየተመለከቱት ይመስላል። ይህን ስል ሌትና ቀን የሚታገሉና በቆራጥነት የሚሰሩ ምሁራን የሉንም ለማለት አይደለም፤ ምስጋናዬም የላቀ እንደሆነ ሳላወሳ አላልፍም።ሆኖም በምእራቡ አለም እንደአሸን ፍለተውና በጥገኝነት በሚኖሩበት አገር ሕዝብ አገልግሎት ከሚሰጡት ጋር ሲወዳደር ስማይና ምደር እንደሆነ ለመጠቆም ፈልጌ ነው።

ዋናውና ሁላቸንም እንደ ኢትዮጵያዊነታችን ልንጠይቅ የሚገባን ጥያቄ ከዚህ አሳዛኘ ውጥንቅ የወያኔ የተንኮል ሴራ እንዴት ልንወጣ እንቸላለን ነው?። የምሁራኑ ጥያቄም መሆን ያለበት ከወደቅነበት በእትዩጵያዊነት መንፈስ እንዴት እንነሣና ሃላፊነታችንን እንወጣ ነው። እንጄ ላለፈው ቸግራቸን ሁላችንም መከላከያችንን በማቅረብ እኔ በዚሀ ጊዜ ይሀን ሰርቼአልሁ፤ ይሀን አበርከቼአልሁ መልስ አይሆንም። ወይም በዚህ ጊዜ ደግሞ እንዲህ ሳደርግ ተዋርጄአለሁ ተስደቤአልሁ በቃኝ፤ ከሚለው አስተሳስብ እንውጣ። ባዲስ ጽኑ መንፈስ ምሁራን ልባችውን ስፋ በማድረግ በሃገር የነፃነት ጥያቄ ወደኃላ የለም ብለን ከዚህ ቸግር እንዴት ልንወጣ እንደምንቸል በጋራ መመካከር ነው እላለሁ።
*

አንቺ የውላድ መካን ከንቱ የደም አገር፤
መቼ ይሆን ዘምኑ ሕዝብሸ የሚከበር፤
አልኩኝ ጎንበስ ቀና ዘንድሮስ መረረኝ፤
ምሁራን ጥቅ ይዘው እየተንሳፈፍኩ ነኝ
ከደርጉ መንጋጋ ተረፍን ስንል እስይ፤
ሆንን እንደገና የወያኔ ሲሳይ
*

የክልል ሹማምንት ቤቱን ያፈርሱታል፤
እነሱም አንድ ቀን ፍርዱን ያገኙታል፤
ጀግና አልተፈጠርም ወይ በቴዎድሮስ ስፍራ
ጎበዝ አልቆመም ወይ በዮሃንስ ስፍራ፤
የሚስማን አጣን ብንጮህ ብንጣራ፤
*

ምሁራን ምን ማድረግ ይችላሉ?

 አዎ ምሁራን ለማይገባ ተግባር የጥቅም ኮሮጆቸውን ለመጎሰር፤ እራሳቸውንና ሞያቸውን አልሸጥም ሞያዬን አከብራልሁ የማለት ጽኑ አቋም መያዝ አለባቸው። ለ ኢትዮጵያ የነፃነት ትግል በሙሉ ልባቸው ከተነሱ የሚያበረክቱትን አስተዋጾ ለመገመት “መጸሃፍ ገላጭ” የሚያስፈልግ አይመስለኝም እጅግ የላቀ ነው። ዋናው ነገር ግን ወያኔ እንደምጽዋት ለሚያቀርበው የጥቅም ወይም የሥልጣን ስጦታ እንቢማለት። ለነፃነት በቆራጥነት መቆምና ሕዝብን በማስተማርና በማስተባበር የሃቅኝ እትዮጵያዊ ምሁር ሃላፊነትና ግዴታ መሆኑን መረዳት የመጀመሪያውና ወሳኙ ተግባር ነው።

 ምሁራን ታሪክ ተመራማሪው፤ የ ኢኮኖሚ ጠበብቱ፤ የስነልቦና ተመራማሪውና ሳይንቲስቱ ሣይቀር የወያኔን ህገወጥ ተግባር ሌትና ቅን በመመርመር ማጋለጥ አላባቸው። ህገወጥነቱን ለሕዝብ፤ በውስጥም በውጭ ለሚታገለው ኢትዮጵያዊ በማሳወቅ ለአለም ህብረትስብ በማስረዳት ከሌሎቸም አጋር ምሁራን ጋር የሃሳብና (ኢንፎርማሽን) ልውውጥ በማድረግ ሳይሰለቹና ሳይታክቱ ለነፃነት ትግል የመስራት ግዴታ አላባችው።

 በተለይም አገራቸንን ኢትዮጵያ ወያኔ በሃይልና በአፈና ከፋፍሎ መግዛት ከጀመር ጊዜ ጀምሮ፤ ኢትዮጵያን ምሁራን ሊስሩ የሚችሉት ተግባር እጅግ የላቀ ነው። በአልም ላይ ታይቶ በማይታወቅ የወያኔን የውሸትና ቅጥፈት እሪፖርቶችን ለአለም ህብረተስብ በማስተጋባት፤ሕዝብን እንዴት እንደሚያሰቃይና የአለም መንግስታትን እንዴት እንደሚዋሸ በመረጃ በማስደገፍ ማጋለጥና ሳይሰልቹ መታገል የሙህር ተግባር ነው።

 የሙሀር ተግባር ክቡር ነው። የሃገርንና የህዝብን የወደፊት እጣ ፋንታም የመመልከትና የመወስን ሃይል አለው። ሆኖም ክቡሩን ሞያ በስንካላ ምክነያቶች “በጅ ጨብጠው የማይገምጡት ዳቦ፡ ስብቀው የማይወጉበት ጦር” እንዳናደርገው አክብረን ልንይዘው ግን ይገባል። ምሁራን እውቀታቸው ለውጥ እንዲያመጥ ካላደርጉትና ካልስሩበት ግን ምሁር መባሉ ቀርቶ ስም ብቻ ይሆናልና ከስም ምሁራንነት ለመውጣትና ከታሪክ ተጠያቂነት ለማምለጥ ለነፃነት ትግል ሳይታክቱ መስራት ይጠበቅባቸዋል።

 በተለይ ባሁኑ ስዓት የነፃነት ትግሉ ውጤታማ እንዳይሆን በ ሕዝብ መካከልና በፖሎቲካ ድርጅቶቸ መሃል ያለውን አለመግባባቶቸ የመፍታት ሃላፊነት የምሁራን ተግባር ነው። በአለም ዙሪያ የሚገኙ ኢትዮጵያን ወዳድ ምሁራን ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በመገናኘት፤ ውይይቶቸን በማደርግ ትግላቸን የነፃነት ትግል መሆኑን በማስረገጥ እንዲሁም የማሳወቅ ግዴታ አለባቸው። ህብረተስቡም አቅጣጫ ይዞ እጅ ለ እጅ ተያይዞ የግፍ አገዛዙን ባፋጣኝ ማስወገድ የሚችልበትን የመፍትሄ ጭብጥ አላማን የማስያዝ ከፍተኛ ሃላፊነት የወደቅው አሁንም በምሁራኑ ላይ ነው እላልሁ። የምሁር ግዴታን ለመወጣት ጠንክሮ መስራት ከምሁር የሚጠበቅ አገራዊ ግዴታ መሆኑን በመረዳት ለውጤት መስራት አለባቸው።

 በተለይ የአሁኑ ዘመን ትውልድ የወያኔ ፐሮፓጋንዳ ስለባ ሆኗል ። እውነተኛ የሆነውንና ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን ሃገርን የመውደድና የኢትዮጵያዊነት ጀግንነት መንፈስ ከልቡናውና ከአዕምሮው እንዲጠፋም ተደርጎል። ይህን በመረዳት ያን የጥንቱን ስሜት ለመቀስቀስ ምሁራኖቸ ሴሚናሮችን በማዘጋጀት ትምህርት በመስጠት ሕዝብን የማስተማርና የመቅስቀስ ሃላፊነት አለባቸው። በዚህ ተግባር ጠንክሮ በመስራት ይሀቺን የነፃነትና ባለታሪክ አገራቸንን ኢትዮጵያ እንደገና የሕዝብ ባለቤት የማድረግ ኢትዮጵያዊያን ምሁራን ግዴታ አለባቸው።

 በመጨረሻም እትዮጵያዊያን ሙህራን በስም ብቻ በዚህ አመትምህረት ተወለዱ; በዚህና በዚያ ምክነያት ተስደዱ። በንዲህ ያለ ሞያ ተምረው በከፍተኝ ምአረግ ተመርቀዋል እንዳይሆን ታሪካቸን እራሳችንን እንመርምር እላለሁ። የምሁር ግዴታን ለመፍጸምና አገር በወያኔ በተወረረበት ዘመን ለነፃነታቸው ይህንና ያንን ሰሩ። ሕዝብንም አስተምረውና አስማምተው ለድልና ለነፃነት አበቁ። መባል ይሻላልና ከአድርባይነት ስሜት በመራቅ ለ እውነትና ለሃገር ነፃነት በመቆም እውነትን ተናግሮ ለ እውነት መሞትን መርጦ ለዚሀ ታሪካዊ ወሳኝ ጊዜ እራስንና እውቀትን መስዋት አድርጎ ለማቅረብ በህብረት እንቁም እላለሁ።

ይህን በማድረግ የሞያ ግዴታቸንን እንወጣ። ያን ግዜ ታሪከም ይዘከረናል። እንበርታ እግዚአብሄርም ማስተዋልና ጥበብን ያብዛልን። እያልኩ ላዛሬ በዝች መጣጥፌ ደህና ሁኑልኝ እላልሁ። ብቸር ይግጠመን !

የናንተው አክባሪ
ሎሚ ተራተራ ነኘ
[email protected]