ስታሊኒስቶችን ማመን ቀብሮ ነዉ! ሸንቃጣዉ ዘካሊፎርኒያ

በቅርቡ በEthiomedia.com ላይ በወጣዉ ዜና የኢትዮጵያ አርበኞች ግንባር ተዋጊዎች በሻቢያ እንደተረሸኑ የሚገልጽ ዜና ሳነብ በጣም አዘንኩ። ሻቢያ አያደርገዉም አልልምም። እ. አ. አ. በታህሳስ ወር 2010 ዓ. ም. “ሻቢያን ማመን ጉም እንደመዝገን ይቆጠራል” በሚል ርዕስ አንድ ያወጣሁት መጣጥፍ በድህረ ገጾች ላይ ሰፍሮ የቆየዉ ብዙ ነገሮችን እንዳስታዉስ አደረገኝ። በመጣጥፉ ያወጣሁት ፍራቻዬ እንደእዉን ሆኖ በዜና ሲወጣ ለማመን ተቸግሬ ነበር። በእዉነትም “የፈሩት ይደርሳል፣ የጠሉት ይወርሳል” የሚባለዉ የአባቶች ተረት እያደር እየተከሰተ ሲመጣ ለክስተቱ መንስኤ ሊሆኑ ይችላሉ የሚባሉትን ሁኔታዎች ለመቃኘት ተገደድኩ። በኢትዮጵያ አርበኞች ግንባር ላይ እንዲህ አይነቱ አደጋ ሲደርስ ይህ መጀመሪያዉ አይደለም። ሆኖም ግን ለምንስ ይህ ሁኔታ እስከሚደርስ ድረስ አመራሩ አልተጠነቀቀም? ለምንስ ሌላ አማራጭ አልፈለገም? እንደነዚህ ያሉት ሁኔታዎች ደግሞ ለግንቦት ሰባት፣ ለኦነግና ለምዕራብ ሶማሌ ነጻ አዉጪ ግንባር ምን አይነት ትምህርት ይሰጣሉ ብለን መጠየቁ ተገቢ መልስን ለመሻት ይረዳል ብዬ አምናለሁ።

በአንድ ወቅት በ1990ዎቹ ዓመታት ኢሳያስ አፈወርቂ እዚህ ዩናይትድ ሰቴትስ ዓለም አቀፋዊ ስብሰባ ለመካፈል መጥቶ ኤርትራዉያንን በዚያ አጋጣሚ ሲያነጋግር “…ኢትዮጵያ የስድሳ አመት የቤት ስራ ሰጥታን ነበር፤ ሆኖም ግን እኛ የመቶ አመት ስራ ሰጥተናታል…” ብሎ እንደተናገረ አንባብያን ሳትሰሙ እንዳልቀራችሁ እገምታለሁ። ኤርትራ ልትጠነክር የምትችለዉ ኢትዮጵያ ስትዳከም ብቻ እንደሆነ የተረዳዉ ሻቢያ ከደርግ መዉደቅ በፊት ጀምሮ ስለኢትዮጵያ መዳከምና መበዝበዝ ባጠነጠነዉ አጀንዳ መሰረት በወያኔ/ኢህአዴግ አጋዥነት ኢትዮጵያን ሲመዘብር ለዓመታት እንደቆየ የምናስታዉሰዉ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ነዉ። ኤርትራ በዓለም ገበያ እንደቡና ነጋዴ መቅረቧ ዓለም አቀፍ የቡና ነጋዴዎች እንኳ እስከሚገረሙ ድረስ ነበር ሁኔተዎች ሲካሄዱ የቆዩት። የሻቢያ አልጠግብ ባይነትና እብሪት ነዉ ናቅፋ ከኢትዮጵያ ብር በላይ በገበያ ላይ ዋጋ እንዲኖረዉ ወያኔን ሲወሰዉስ የነበረዉ። ሻቢያ ለወያኔ ሳያሳዉቅ ናቅፋን ቀይሮ ኢትዮጵያ ብሯን እንድታረክስ ሙጥኝ ቢልም ሳይሳካለት ቀረ። ኢትዮጵያም ደግሞ ለሻቢያ ሳታሳዉቅ አዲስ ብር በጀርመን አገር እንዲታተም አድርጋ ለሻቢያ ሴራ ምላሹን ሰጠች። ይህ ሁኔታ ሻቢያን አንገፍግፎ ያለአንዳችም ቅድመ ዝግጅት ሻቢያ ለጦርነት እንዲነሳ ገፋፋዉ። ወያኔ/ ኢህአዴግ ደግሞ እንደበፊቱ ሻቢያን ሊሸከም ያልቻለበት ደረጃ ደረሰና የኤርትራና የኢትዮጵያ ጦርነት በ ”ድንበር” ሽፋን ተጀምሮ በሁለቱም አገሮች ለብዙ ሺህ ዜጎች መሞት ምክንያት ሆነ። እስከዛሬ ድረስ ሻቢያ በኢትዮጵያ ላይ ሊያደርስ የሞከረዉን ሁሉ ልብ ብለን ብናስተዉል ኢትዮጵያን እንደ ቅኝ ገዥነት ከመጥላት አልፎ ስሟ እንኳ እስከነድራሹ ቢጠፋ ደስ እንደሚለዉ ለመረዳት አያዳግትም።

ታዲያ ይህ ሁኔታ እየታወቀ “የጠላትህ ጠላት ወዳጅህ ነዉ” ከሚል ስትራቴጂ የተነሳ ሻቢያ ላይ ብዙ እምነትና መመኪያነት ጥሎ ለእንደዚህ አይነቱ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ዉድቀት መንገድ መክፈት የሚያሳየን ነገር ቢኖር በአርበኞች ግንባሩ ዉስጥ ምን ዓይነት ድክመት እንዳለ ለመረዳት ብዙ መፈላሰፍ እንደማያስፈልግ ነዉ የምረዳዉ። ወያኔና ሻቢያ ምንም ቢጠላሉ ሌላ ሶስተኛ ወገን መጥቶ የእነርሱን ህልዉና የሚፈታተን እንዲከሰት አይፈልጉም። የአማራ ወይንም የኦሮሞ ወገን አይሎ ካዩ ወያኔና ሻቢያ ተባብረዉ ከማዳከም ወደሗላ እንደማይሉ ለአንዳችም ሰከንድ እንኳ አልጠራጠርም። ወያኔ የኤርትራ ተቃዋሚ ድርጅት የሆነዉን ጀበሀ (ELF)ን በማደራጀት ብዙ ጊዜና ገንዘብ አባክኗል። ባለፈዉ አመት በየአገሩ ያሉትን የሻቢያ ድርጅት ተወካዮች አዲስ አበባ በራሱ ወጪ በማስመጣትና ለአንድ ሳምንት ሆቴል አርፈዉ ሴሚናር እንዲያካሂዱ ወያኔ አስፈላጊዉን መስዋእት ከፍሏል። የቀረዉ ነገር ቢኖር የኤርትራን ህገ-መንግስት መንደፍ ብቻ ነዉ። ከዚያም በሗላ መቼ ሻቢያ መዉደቅ እንዳለበት የሚወሰነዉ መለስ የዩናትድ ሰቴትስ መንግስትን አማክሮ በሚሰጠዉ መመሪያ መሰረት የሚሆን ይመስለኛል። መለስ ይህን የሚያደርገዉ ደግሞ ሌላ ሶስተኛ ሀይል መጠቶ የራሱን ህልዉና የማይነሳዉ መሆኑን ሲያረጋግጥ ብቻ የሆናል ብዬ እገምታለሁ። ይህ ሰትራቴጂ ተሳክቶ ሻቢያ ከወደቀ መለስ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ አዉራ አምባገነን መሪ (Regional demagogue) በመሆን ይባስኑ ብሎ ምዕራባዉያን አገሮች መለስን እንዲንከባከቡትና እንዲለምኑት የሚገደዱበትን ሁኔታ ይፈጥራል ብዬ እሰጋለሁ።

በአንጻሩም ደግሞ ሻቢያ ኢትዮጵያን ለማጥቃት የወያኔን ጠላቶች አሰባስቦ አሰልጥኖና አስታጥቆ ለዉጊያ ሲልክ ቅድመ ሁኔታዎችን በማስቀመጥ ተዋጊዎቹ የሚያካሂዱትን በሙሉ ለመቆጣጠርና ለማወቅ ብርቱ ፍላጎት አለዉ። የምዕራብ ሱማሌ ነጻ አዉጪ ግንባር፣ የኦሮሞ ነጻ አዉጪ ግንባርና ግንቦት ሰባት ተባብረዉ ወያኔ/ ኢህአዴግን በወታደራዊ ንቅናቄ ከስልጣን ካስወገዱ ሻቢያ ኢትዮጵያን በእነዚህ ድርጅቶች አማካኝነት መቆጣጠር እችላለሁ ብሎ ቅዠት ዉስጥ ገብቶ የወጠነዉ ባይሳካለትም ለወያኔ እረፍት አለመስጠቱ ራሱ እንደ ትልቅ ነገር እንደሚቆጥር ይገባኛል። ሆኖም ግን ሻቢያ ወያኔ ላይ ካሰበዉ ሸር ይልቅ ወያኔ ሻቢያ ላይ ያጠነጠነዉ ሸር እያየለ የመጣ ይመስላል። የአርበኞች ግንባር አመራር በሻቢያ ድራማ ተከፋፍሎ ለዚህ ዉድቀት መከሰት ምክንያት ሆኖ ከሆነ ጥፋቱ ከሻቢያ ሳይሆን ከአርበኞች ግንባር ነዉ። ምክንያቱም የአርበኞች ግንባር እንዲህ ዓይነቱ ድራማ ሊከሰት እንደሚችል ቀድሞዉኑ መጠበቅ ነበረበት። የኢትዮጵያ ጠላት ከሆነ ድርጅት ጋር ሊደረግ የሚገባዉ ወዳጅነት ልኩና ገደቡ መወሰን አለበት። ምክንያቱም የሻቢያ አቋም እንደ ወንዝ ሙላት ሳይታሰብ የሚጎርፍና ጠራርጎ የሚወስድ ሊሆን ይችላልና።

እንደማንኛዉም ነጻ አዉጪ ግንባር አመራር አካል ዉስጥ የሚካሄድ የሀይል አሰላለፍ ዉስጣዊ ትግል መካሄድ ለአሁኑ ዉድቀት አስተዋጽኦ አድርጎ ሊሆን ይችል ይሆናል። ሆኖም ግን ከሻቢያ ጋር አብሮ ለዚህ ዉድቀት መከሰት ምክንያት ሊሆን ይችላል ብዬ የምገምተዉ በግድያዉ ወቅት በአካል ነበሩ የተባሉት የአርበኞች ግንባር አመራር አካላት እንደ አንጀኛ ሆነዉ ድርጅቱን ለዉድቀት አድርሰዋል የሚል የእምነት ዝንባሌ አለኝ። ይህ ሁኔታ በነጻ ጋዜጦች ወይም ነጻ ሪፖርተሮች ተዘግቦ ሊተላለፍ የሚችል ሁኔታ አይደለም። ምክንያቱም እንዲህ አይነት ፖለቲካዊና ወታደራዊ እርምጃ በጣም ምስጢራዊ በሆነ ሁኔታ የሚካሄድ ስለሆነ የዉስጥ አዋቂዎች አንድ ቀን እስከሚያወጡት መጠበቅ ግድ ይሆናል። ለዚህም ነዉ የግድያዉን ሁኔታ ለማወቅ ረጅም ጊዜም የወሰደዉ። ወጣም ወረደ ሻቢያ ጨካኝ ነፍሰ ገዳይ ድርጅት መሆኑን በተደጋጋሚ ስለገለጸ የሚቀጥሉት ጭዳዎች ከየትኛዉ ድርጅት እንደሚሆኑ ለማወቅ ብዙ ማሰብ የሚያሰፈልገዉ አይመስለኝም።

ይህ የሻቢያ ግድያ ሻቢያ ከወያኔ ጋር ለመታረቅ ሲል ያደረገዉ ይሁን ወይንም ነጻ አዉጪ ግንባሮች ሻቢያ ከሚፈልገዉ ዉጪ ድርጊት ስለፈጸሙ ይሁን አይሁን ሙሉ በሙሉ በእርግጠኝነት ለመናገር ባይቻልም ከነዚህ ሁለት አበይት ምክንያቶች ዉጪ እንደማይሆን ከዱለት ንድፈ-ሀሳብ (conspiracy theory) በመነሳት ለመገመት አልቸገርም። ኢሳያስ አፈወርቂ ለኤርትራዉያኑ ነባር ታጋዮች እንኳ ያላዘነ ለኢትዮጵያዉያን ያዝናል ብዬ ለአንድም ሰከንድ እንኳ አልጠራጠርም። በስልጣን ላይ ለመቆየት ሲል ኢሳያስ አፈወርቂ ከዲያቢሎስ ጋር ቢሆንም አብሮ የሚደረገዉን ሁሉ ያደርጋል። ሻቢያ ያን ካላደረገ በስልጣን ላይ እንደማይቆይ አጥብቆ ስለሚያዉቅ ያለአንዳች ህፍረት ወይም ህሊና ግድያዎችንም ሆነ ጭፍጨፋዎችን ማካሄድ እንደአስፈላጊ የህይወት ጉዳይ ይቆጥረዋል።

ማንኛዉም ነባርም ሆነ አዲስ የወያኔ ተቃዋሚ ይህን ሁኔታ አዉቆ መግባት አለበት። “የጠላትህ ጠላት ወዳጅህ ነዉ” የሚለዉ ተረት ለሻቢያ አይሰራም። ቢሰራም በጊዚያዊነት ነዉ እንጂ። ሻቢያ ስታሊኒስታዊ ባህሪዉ እየተጋለጠ ከመጣ ቢሰነብትም አማራጭ ሁኔታ በመታጣቱ ምክንያት ብቻ እንደወዳጅ ተቆጥሮ አላስፈላጊ ወደሆነ የፖለቲካ አጣብቂኝ ዉስጥ መግባቱ ከጥቅሙ ጉዳቱ በእጅግ ሊያመዝን ይችላል ብዬ አምናለሁ። ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል ዘለዓለም ሲያለቅስ እንደሚኖር ሁሉ ከሻቢያ ጋር መወዳጀትም ተመሳሳይ ትርፍ ያስከትላልና። ምንም ጊዜ ቢሆን ስታሊኒስቶችን ማመን ቀብሮ ነዉ።

[email protected]