የኢትዮጵያ ወጣት እንደፈንጂ ቦምብ
ከዶ/ር አለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም በህልምአለኝ
በአትዮጵያ ውስጥ በመታየት ላይ ያለው ሁኔታ ወጣቱ የመፈንጃ ጊዜውን እንደሚቆጥር ፈንጂ መሆኑን ያመላክታል፡፡የወጣቱ በሁለንተናዊ ፍርሃትና መሳቀቅ ውስጥ መሆን፤ተስፋ ማጣት፤በሃገሪቱ ላይ እያቆለቆለ በሚሄደው የኢኮኖሚ ውድቀት፤በሚተገበረው የኤኮኖሚ ቀውስ፤ እና የፖለቲካውና የሃገሪቱ እድገት መጨንገፍ ዋነኛ መረጋገጫዎች ናቸው፡፡ የወጣቱ የነጻነትና የለውጥ ጥመኛነቱ የሚታይ ሃቅ ነው፡፡ ጥያቄው ደግሞ ወጣቱ ይህን የሚመኘውንና ለማምጣት የሚጥርለትን ለውጥ ተገፍቶ በሚገባበት ማስገደድ አለያስ በሚወደውና በቆመለት ሰላማዊ መንገድ ነው የሚያመጣው? በርካታ ኢትዮጵያዊያን በተስፋ መቁረጥና በራእያቸው መጨፍለቅ ያዘኑና በኢትዮጵያቸው ብርሃን ማየት ማሰብ የተከለከሉት ወጣቶች ግራ ተጋብተው በእግሮቻቸው ጣቶች ድምጽ ለመስጠትም እየዳዳቸው ነው፡፡ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች ሃገራቸውን ሳይሆን በሃገራቸው ላይ የተጫነውን የግፍ ገዢ፤በመጥላትና ከሃገርና ከወገን በመነጠል ከደቡብ አፍሪካ እስከ ሰሜን አሜሪካ፤ከመካከለኛው ምስራቅ እስከ ሩቅ ምስራቅ ድረስ ስደተኞች ሆነዋል፡፡
በ1935 ዓ/ም እ አ አ አዶልፍ ሂትለር ለፓርቲው መደበኛ ስብሰባ ባደረገው ንግግር ላይ ‹‹ወጣቱን ንብረቱ ያደረገ ብቻ የነገው ባለቤት መሆን የሚችለው›› ነበር ያለው፡፡ ወጣቱን በናዚ ስሜትና ጠበል አጥምቆ የናዚን ፍልስፍና በዓለም ላይ እንዲረጩት ለማድረግ፡፡ ሆኖም ግን ወጣቱን በራሳቸው ቅርጽ ለመለወጥና አእምሮው የተሰለበ ወጣት በመፍጠር ቅዠታቸውን እውነት ላማድረግ ነው የአምባገነኖችና የፈላጭ ቆራጭ ገዢዎች ምኞትና ዓላማ
ሶቭየቶችም ወጣት ኮምሶሞልስን ፈጥረው በፓርቲያቸው ውስጥ በማካተትና በማጨንገፍ ሕዝቡን ለመግዛት ያደረጉት ዘዴም ነበር፡፡የቻይናው ማኦም ወጣቱን በሰፊው በማንቀሳቀስ በ1960ዎቹ ቀዩን ጦር በመፍጠር ‹‹ዘለዓለማዊ አብዮት››የሚል ራዕይ ፈጠረ፡፡የቀዩ ጦር ተግባርም የባሕል አብዮቱን ተግባራዊ ማድረግ ነበር፡፡
በሃገራችን ኢትዮጵያም የዘውዱ አገዛዝ ከተገረሰሰ በኋላ በተፈጠረውና ለ17 ዓመታት በገዛው የደርግ ስርአት ወቅት፤ወጣቱን የወታደራዊው ጁንታና የሲሻሊስት አብዮት አካል ለማድረግ ብዙ ጥረት ተደርጎ ነበር፡፡ይሄ የፍቅር ጎዳና ግን ብዙም ሳይቆይ በደርግ የጭካኔ ቀይ ሽብር በሺህ የሚቆጠረው ወጣት ከቤቱ እየታደነ፤ ከጎዳና ላይ እየታፈነ በመጨፍጨፉ ያ የፍቅር ጎዳና ደም በደም ያውም የነገው ተተኪ ትውልድ በአብላጫው የተጨፈጨፈበት ሆኖ ተደመደመ፡፡ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲታወስና ሲነገር የሚኖር የሟች ቤተሰቦች ልጆቻቸው የተገደሉበትን ጥይት ዋጋ እየከፈሉ አስከሬን እንዲወስዱ የሚያዝ መመርያ የወታደራዊው ደርግ የበላይ የሆነው መንግስቱ ሃይለማርያም አወጣ፡፡
በንብረተነት የሚያዙት ‹‹ባሮች ብቻ›› ናቸው
አሁን ደግሞ ፈላጭ ቆራጭ የሆነው አምባገነኑ ገዢ መለስ ዜናዊ በተራው የኢትዮጵያን ወጣት በንብረትነት ለመቆጣጠርና የግሉ በማድረግ የዘመናት ባለስልጣን ሆኖ የመቆየት ህልሙን ማስፈጸሚያ ለማድረግ የማይሆነውን ጉዞ ጀምሮታል፡፡ የመለስ እቅድና ቅዠት ግልጽ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ብልህ ወጣቶች በመምረጥና በመመልመል የተፈተኑና የነጠሩ በማለት ለአገልጋይነት ለማዋል ነው፡፡ለመማር፤ስራ ለመያዝ፤የጤና ዋስትና ለማግኘት፤በሰብአዊ አገልግሎት ተግባራት ተሳታፊ ለመሆን የፓርቲው ታማኝ አባል መሆን ወሳኝና አማራጭ የማይደረግለትግዴታ ነው በማለት አወጀ፡፡ ወጣቱ ያለው አማራጭም ህሊናውን ሸጦ የተባለውን መቀበል ሆነ፡፡ ይህን ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆነው ግን ያለው አማራጭ በችግር አለንጋ እየተገረፈ በችጋር መቆላትና ከሰብአዊነት ውጭ ሆኖ የዜግነት መብቱን መገፈፍ ነው፡፡ የገዢው ፓርቲ አባል ያልሆኑም ከሚኖሩበት ቀበሌ መብታቸው የሆነውን የስራ መፈለጊያ የድጋፍ ደብዳቤ ማግኘትና ሌላም የመኖር መብቱ የሆነውን ሁሉ ይከለከላል፡፡ አዳዲስ ተመራቂ የሆኑትን የኮሌጅ ተማሪዎችም የፓርቲው አባላት ለማድረግ ወጥሮ መያዣ ሰንሰለት መለስ አዘጋጅቶላቸዋል፡፡በ2008 እና 2009 የትምህርት ዘመናት ትምህርታቸውን የጨረሱትን የኮሌጅ ምሩቃን የትምህርት ማስረጃቸውን እንዳይወስዱ በማድረግ ሥራ ማግኘታቸውንና መጀመራቸውን ሲያረጋግጡና የተማሩበትን ለመክፈል መቻላቸው ሲታወቅ እንዲወስዱ የሚያግድ ህግ ደነገገ፡፡ ይህ ህግ ግን በገዢው ፓርቲ አባላት ላይ ተፈጻሚነት አይኖረውም፡፡
የአንድን ሕዝብ ወጣት አካል ‹‹በንብረትነት›› መያዝ ከአልባንያ እስከዝምባብዌ ላሉ አምባገነን ገዢ እርኩስ ባሀሪያቸው ነው፡ወጣትን እንደንብረት መያዝና መገልገያ ማድረግ ከባርያው ስርአት ጋር የተያያዘ የአምባገነኖች ባህሪ ነው፡፡አምነባ ገነኖች አስተዳዳሪዎች ሳይሆኑ ገዢዎች የሚባትም በዚህ የተነሳ ነው፡፡የባርያው ተግባር ጌታውን ማገልገል ብቻ ነው፡፡ጌታው የባርያውን ጉልበትና ሰውነት ይቆጣጠረዋል እንጂ ህሊናውን ጨርሶ አይገዛውም ስለዚህም አሳዳሪው የባርያውን ህሊና በማላሸቅ የጌታው መጠቀሚያነቱን ለማረጋገጥ ስብእናውን አላሽቆ፤ ህሊናውን አዘናግቶ፤ጌታው የሚያስበለት፤ ጌታው የሚያቅድለት ሆኖ እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡ይህንንም ለማረጋገጥ አሳዳሪው ባርያውን አቅመቢስ፤ተስፋ ቢስ እና ከርታታ ያደርገዋል፡፡
ወጣቱን-በንብረትነት ወይስ ወጣቱን- በኪራይ
መለስ ባለፈው ምርጫ ተቀዳጀሁ ያለውን የ99.6 በመቶ ምርጫ ፌሽታ ሲያከብር ባደረገው የካፈርኩ አይመልሰኝ ንግግሩ ላይ ‹‹በመካሄድ ላይ ባለው የልማት እንቅስቃሴ ውጤት ተጠቃሚ በሆነውና በተግባር ሊቀላቀልና ተጠቃሚ ለመሆን በወሰነው የኢትዮጵያ ወጣት እጅጉን ኮርተናል፡፡ምስጋናችን በማቅረብ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች ላደረጉልን አበረታች ድጋፍ ሁሉ ሰላምታችንን ተቀበሉን እንላለን ሲሉ ምን ማለት እንዳሰቡ ሲሰላ በ2009 በተደረገው ዓመታዊው የወጣቶች ስብሰባ ላይ የተደረገው ንግግር በግልጽ ያስረዳል፡፡አስቀድሞ በተዘጋጀው ዘዴ፤ በሰፊው አዳራሽ ውስጥ በጸጥታ ለተዋጠውና በር ላይ የታደለውን የህወሃት ፓርቲ ኮፊያ ያጠለቀውን በርካታ ወጣት የኢትዮጵያ ወጣቶች ወኪል የሆኑ በማስመሰል መለስ ስብሰቡን ለምን እንደተሰበሰበ በግልጽ ያላወቀውን ወጣት ለፓርቲ አባልነት መመልመያ እቅዳቸውን አስቀድመው ነድፈው ዘረጉለት፡፡ ላለፉት ሶስት ዓመታት ወጣቱን ወደ ፓርቲ አመራር ለማምጣትና ለስልጣን ለማብቃት ያላሰለሰ ጥረት ሲደረግ እንደነበርና ለዚህም የሚያስፈልጉትን ጠንካራ ወጣቶች ምልመላ እንደተካሄደና ከ 30 000 ያላነሱ ወጣቶች እንደተመለመሉ፤ እነዚህም ምርጦች አስፈላጊው ስልጠና ከተሰጣቸው በኋላ በአውራጃ በወረዳና በቀበሌ በስራ በመፈተን ነጥረው የወጡት ወደ ከፍተኛ የስልጣን ደረጃ እንደሚሸጋገሩ በማስረዳት የተሰበሰቡትን ወጣት ወንዶች በ2010 በሚደረገው ነጻና ሰላማዊ ምርጫም እያንዳንዳቸው ሊመዘኑበት የሚችሉትን የድጋፍ አስተዋጽኦ የሚያሳዩበት ወቅትም እንደሆነ አስረዱ፡፡በተጨማሪም ከአመራሩ ጋር በቅርብ በመስራት ለዚህ የምርጫ እንቅስቃሴ ችግር ነው ብለው የሚያስቡትንም ለአመራሮች በማሳወቅ ተጨማሪ ተግባር ማከናወን እንደሚጠበቅባቸው ለወጣቶቹ አስገነዘቡ፡፡
የዚህ የወጣቶች ስብሰባ ዋናው ምክንያት ወጣቱን በራሱ ህሊና ማሰብ እንዳይችልና ለአገዛዙ አሻንጉሊት በመሆን ሁን ያሉትን የሚሆን፤ አድርግ ያሉትን የሚያደርግ፤ ፈጽም ያሉትን ያላአንዳች ጥያቄ የሚያከናውን ስብእናውን ጨርሶ የዘነጋ ፍጡር ለማድረግና ቀጣዩ ዘመንም በወጣቱ ስብእና ማጣት የህወሃት የግል መፈንጫ እንዲሆን የታቀደ ነው፡፡ ወጣቶቹም የፓርቲው ሃቀኛ ተአማኒ ሆነው በመለስና አገልጋዮቻቸው ቅርጽ የተሰሩ ተደረጉ፡፡
አደጋ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ወጣት
እዚህ ላይ ስለ ኢትዮጵያ ወጣት ማንሳቴ ነቁጥር ተሰፍሮ የተቀረጸውን ከ15-24 ያለውን የእድሜ ገደብ መነሻ በማድረግ አይደለም፡፡በአፍሪካ የኢኮኖሚና በየሃገሩ ካለው እውነታ በመነሳት ከ30 በታች ያለውን መሰረት በማድረግ እንጂ፡፡
የኢትዮጵያ ሕገመንግሠት አንቀጽ 36 ለኢትዮጵያ ወጣቶችና ሕጻናት በጤና፤ ትምህርትና የኑሮ ዋስትና በርካታ መብቶችን በስፋት ይደነግጋል፡፡ በኢትዮጵያ ያለው የህጸናት ስታስቲክ ግን እጅጉን አሳዛኝና አስደንጋጭ ነው፡፡ከ18 ዓመት የእድሜ ገደብ በታች ያለው የሕዝብ ቁጥር 41 ሚሊዮን ወይም ከጠቅላላው የሕዝብ ቁጥር ግማሽ ሲሆን የዩኒሴፍ ዘገባ እንደሚያስረዳው ግን ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች በሆኑት በህጻናት ላይ የሚደርሰው ከግማሽ በላይ የሚሆነው የሞት አደጋ በምግብ እጦት አለያም የተመጣጠነ ምግብ አለማግኘት መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ኢትዮጵያ በግምት ከ5 ሚሊዮን ያላነሱ እናትና አባት አልባ ሕጻናት ሞግዚት ናት፡፡ይህም ከጠቅላላው ሕጻናት 15 በመቶ መሆኑ ነው፡፡ከ800 000 የማያንሱት ደግሞ ወላጆቻቸውን ያጡት በኤይድስ ጠንቅ ሲሆን እነዚሁ ህጻናትም ካሉበት ሁኔታ በመነሳት ለማንኛውም አደጋ የተጋለጡ ናቸው፡፡ያለእድሜ ወደ ስራ መግባት፤ባልተጠበቀ የወሲብ ተግባር ከመጠቃታቸውም ባሻገር በቂ ትምህርት አይገኙም፤ የሰብአዊ መብት ጥበቃና እንክብካቤም የላቸውም፡፡በከተሞች ያለው የወጣት ሥራአጥ ቁጥር 70 በመቶ እንደሆነ ይገመታል፤ወደ 85 በመቶ የሚሆነው ወጣት የሚኖረው በገጠር ሲሆን፤ በተለይ በሴቶች ላይና በገጠር ላለው ወጣት የትምህርት ደረጃው በጣም ያዘቀዘቀ ነው፡፡የሴቶቹ ወጣቶች ያለእድሜያቸው ለጋብቻ ይዳረጋሉ፤ ለምሳሌ በአማራው ክልል ከ45 በመቶ በላይ የሆኑት ጋብቻቸውን እንዲፈጥሙ የሚደረጉት በ15 ዓመት የእድሜ ክልል ነው፡፡
በሌላ ጎን፤2.5 ሚሊዮን የሚሆኑ ሕጻናት የአካል ጉዳተኞች ሲሆኑ ከመንግስት በኩል የሚደረግላቸው ድጋፍ እጅግ አባሳ ነው፡፡ ከሚያድርባቸው የተመሰቃቀለ ጫና የተነሳ ወጣቶቹ ተስፋ በመቁረጥ ወደ አደገኛ አዝማሚያ ይገባሉ፡፡ የጎጂ እጽ ተጠቃሚ ይሆናሉ፤ ይጠጣሉ፤ያጨሳሉ፤ ወደ ወንጀል ይገባሉ፤ ያለ፤ተጠበቀ የወሲብ ግንኚነት ይፈጽማሉ፤በዚህም የተለያየ በወሲብ በሚተላለፍ በሽታ ኤችአይቪን ጨምሮ ይለከፋሉ፡፡ የሕጻናት የንግድ ዝውውር በስፋት ይካሄዳል፤ በማደጎ ስም ምን አይነት ወንጀል እየተፈጸመ እንደሆነ በዓለም አቀፉ መገናኛ ብዙሃን በተደጋጋሚ ተወስቷል፡፡
ለመፈንዳት ያቆበቆበው የኢትዮጵያ ወጣት
ውጥንቅጡ የወጣው የኢትዮጵያ ወጣት ሁኔታ ጊዜው እንደተቃረበ ፈንጂ ነው፡፡በሃገሪቱ ውስጥ የሚታየው የኤኮኖሚ ውድቀት፤ ሥራ አጥነት፤ የፖለቲካው ጨቋኝነት፤ የኑሮ ውድነት፤ የገዢው ፓርቲ ከፋፍለህ ግዛ መመርያ፤ ወጣቱን የራሱ አዛዥ እንዳይሆን ያለበት እዝ፤ እነዚህ ሁሉ ለፍንዳታው ሰበብ ናቸው፡፡ ወጣቱ ከዚህ ለመላቀቅና በሃገሩ ላይ እንደዜጋ በነጻነትና በሰለም ለመኖር ለውጥ ያፈልጋል፡፡ጥያቄው ግን ለውጥን እንዴት ሊያመጣ ይችላል ነው፡፡ በተለመደው የጉልበት መንገድ ወይስ በሰለጠነው ሰላማዊ መንገድ? በሌላ በኩል ደግሞ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩት፤ በሃገራችን ላይ ያለውን ግፍና መከራ፤ ሰላም እጦት፤ተስፋ ቢስነት፤ በማየትና ራእይ በማጣት የሚወዷትን ሃገራቸውን፤ የሚያፈቅሩትን ቤተሰባቸውን እየጣሉ በመሰባሰብ ፈንታ በየሃገሩ እየተበተኑ ናቸው፡፡ዛሬ ከደቡብ አፍሪከ እስከ ሰሜን አሜሪካ ከመካከለኛው ምስራቅ እስከ ሩቅ ምስራቅ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች የማይገኙበት ሃገር የለም፡፡ስለዚህም ለውጥ መጥቶ የተበተነው ሁሉ ተሰባስቦ ሃገሩን በልማትና በእድገት መገንባት አማራጭ ያማይደረግለት ተግባር ነው፡፡ ለዚህ ደሞ አሰባሳቢና መሪ ያስፈልገዋል፡፡
ለወጣቱ ምን አይነት መሪ?
መመለስ ያለበት አንኳርና ወሳኝ ጥያቄ!
አሁን በሃገራችን በርካታ ተቃዋሚ ፓርቲ ነን ብለው በመንቀሳቀስም፤ በማዝገምም፤ በመኝታም ላይ ያሉ አሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ በሃቅ ለትግል ቆመው ግን ፍርሃትና ጥርጣሬ ያደረባቸው፤አለያም ትንሽ ትንሽ ተቃዋሚ ብዙ ብዙ ደጋፊ በመሆን ጊዜውን መግፋት የሚሉ፤በጎኑ ደግሞ መስለን ከጉልበተኛው ጋር ተሸጉጠን ሲያስፈልግ እዚህ ካለዚያም እዚያ እያልን ቀኑን መግፋት ብለው ያሾለቁ፤እስከዘለቄታው በተቃዋሚነት ብቻ ክፍም ዝቅም ሳንል መቆየት ያሉ፤ዋናውን ጠላት ትተው ምሩን መንገድ አሳዩን ያላቸውን ሕዝብ እንግዛህ ዝም በል እኛ እናውቅለሃለን በማለት ዓላማቸውን ስተው ሕዘቡን ረስተው ያሉ፤ዕድሜያቸውን በሙሉ በአመራር ላይ ተቀምጠው ጊዜው እያለፈ አዲስና የሰለጠነ የትግል ስልት ሲመጣ ያን መቀበል እያቃታቸው አመራሩን የሚጥኝ ብለው ለውጥ ሳያመጡ ሳይለወጡ ለመኖር የሚመኙ እና በራካታ አይነቶች እንደመኖራቸው ከመሃላቸው አንዳንድ አፈትልከው ወቅቱን ተገንዝበው ለለውጥ በቆራጥነት የሚቆሙ ብቅ ይላሉ፡፡ሁለቱን አይነቶች በአንድ ላይ አዋህዶ መጓዝ እጅግ አስቸጋሪ በመሆኑ ያለፈው ወይም ጊዜው ያለፈበት ለአዲሱ ተተኪ ትውልድ ሊያስረክብ የግድ ነው ስለዚህም ለወጣቱ የራሱ የሆነና እንደሱ የሚያስብ፤እንደወጣቱ ፈጣን አመለካከት ያለው፤ሃሳብን ተቀብሎ በማስተናገድ አባላቱንና አብረውት ያሉትን አመራሮች በማበረታታት አብሮ የሚጓዝ መሪ ነው የሚያስፈልጋቸው፡፡