ሲሞት አታልቅሱ!!! በይፍሩ ኅይሉ
ለክቡራንና ክቡራት አንባቢያን፤
ወገናችን የኢትዮጵያ ሕዝብ ግፍና መከራውን ሲቧጥጥ ይኸው ወደ አርባ አመታት እየተጠጋ ነው። (1974-2011) በነዚህ 37 አመታት ውስጥ ይህ ለተዕግስቱ መጠን የሌለው ቆራጥ ሕዝብ ከመቼውም የበለጠ፤ ብዞውችም እንደሚሉት ከኢጣሊያ የግፍ ወረራ የባሰ፤ አሁን ያልበት የመከራ ዘመን በጥፍ ያስከነዳል ይላሉ። ክቡር አቶ ከበደ ሚካኤል “መከራና ችግር ብልሃትንና ድፍረትን ይፈጥራሉ” ብለው እንደጻፉት ታዲያ ይህም የመከራ ዘመን ብዙ ጀግኖችን፤ ብዙ ሊቃውትንና ጠቢባንን፤ በተለይም በሥነ ጽሁፉ መስክ የበቀሉት ስፍር ቁጥር የሌላቸው ወንድሞችና እህቶች እጅግ የሚደነቁ ናቸው። ያገራቸውን ወቅታዊ ሁኔታ በሚጣፈጠው ቋንቋቸው እያንቀነባበሩ ሲያቀርቡልን የብዙዎቻችንን የተደበቀ ወኔ ይቀሰቅሳል። እኔም አልፎ አልፎም ቢሆን አንዳንድ ጽሁፎችን ለማቅረብ ስሞክር ከህሊናዬ ጋራ ብዙ እየተሟገትሁ ነው።፡በምንም ሚዛን ቢሆን፤ በማንኛውም መለኪያ እኔ ከነዚህ የታደሉ፤ ሙትን ከሚቀሰቅሱ የሥነጽሁፍ ባለሟያዎች መካከል አንዱ እንዳልሆንሁ አውቃለሁ። “ደም ከልጓም ይስባል” እንደሚሉ ሆነና ያቺው የስናፍጭ ቅንጣት የምታክለው ወኒዬ እየጎተጎተችኝ በድፍረት አንዳንድ ጽሁፎችን ሳቅርብ “ምነው ቦታውንና ጊዜውን ከኔ ለተሻሉት ብለቅ!!” እያልኩና ክራሴ ጋር እየተሟገትሁ ነው። ታድያ ዛሬም በድፍረት፤ እንደ ነብር በጠላቱ ላይ ሊቆለልበት ላደፈጠው፤ ለጀግናው፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ወገኔ የምትከተለዋን ግጥም ለክብሩና ለመታሰቢው አቀርባለሁ።
ሲሞት አታልቅሱ!!!
ነጋሪት አይመታም አይነግርም ባዋጅ፤
ድባቅ የሚመታው በድንገት ነው እንጂ፤
የከፋው ሲነሳ መች ጣጣ ያበዛል!
የሁዱን በሆዱ አምቆት ይጓዛል።
ቀፎው ተነቃንቆ እንድተቆጣ ንብ፤
ሆሆሆ!! ብሎ ተነስቶ ይነድፋል እንደ ተርብ።
ባድዋ፤ በማጮው፤ በኮንጎ፤ ኮሪያ፤
ማን ሆነና ጀግናው የጦ ር ባለሙያ?
ጀግንነት ከሌሎች ዛሬ ተማር ሲሉት
እነሰማይ ቅርቡ ሲፈላሰፉበት፤
ክምር አይመቶዎች ፤ዝናር በቅፋቸው፤
ወይ ልክ አለማወቅ! አደፋፈራቸው!!!
ተው! አታብጠልጥሉት! ተው ! አትፍረዱበት!
መቼ ጠፍቶት ለሱ፤ እናንተ የምትነግሩት?
ፈልቶ ሲገንፍል ሲሟጠጥ ትግስቱ፡
ይዋል፤ ይደር፤ እንጂ አይቀር፡ መነሳቱ!!
ያኔዬ ድረሱለት ቁሙለት ከጎኑ፤
ከፊት ፊታውራሪው፤ ከኋላው ደጀኑ።
ቢቆስል አክሙት፤ በጥይት፤ ቢመታ፤
ቢሰበር ጠግኑት፤ ቢወድቅ አጉል ቦታ፤
ቢታሰር አስፈቱት ወህኒ ቢንገላታ።
ቢመሽበት ይደር አስጠጉት ይተኛ፤
ቤታችሁ ክፍት ይሁን ለዚህ መንግደኛ።
ከቻላችሁ እርዱት ስንቁን አቀብሉ፤
ጭብጦና በሶ ፤ ፍትፍት ባገልግሉ።
ውሃ ጥም ቢያነደው ቢቃጠል አንጀቱ፤
ስጡት የሚጠጣው ቀና አርጉት ካንገቱ።
ጥይቱ ቢያልቅበት፤ ቢከዳው ክላሹ፤
የመውዜሩ ቃታ ቢግል ደመላሹ፤
ሁኑለት አለኝታ ለዚያን ቀን ደራሹ።
ጀግና ተራራ አይደል ዘላለም አይኖርም፤
ብርሌ ነውና መሰበሩ አይቀርም።
ሠርግና ፤ ምላሹ የጀግና ድግሱ፤
ሞት ዘውዱ ነውና ካባና፤ በርኖሱ፤
ፎክሩለት እንጂ ሲሞት አታልቅሱ።
ይፍሩ ኃይሉ
[email protected]