በቴሌ ሠራተኞች ላይ ያለመረጋጋትን የፈጠረው የምደባ ጉዳይ በቀጣዩ ሳምንት የለይለታል

ኢትዮ እማማ)
በቴሌ ሠራተኞች ላይ ያለመረጋጋትን ፈጥሮ የነበረው የምደባ ጉዳይ በቀጣዩ ሳምንት ሊለይለት ነው ። የፈረንሳይ ንብረት የሆነው ፍራንስ ቴሌኮም የተባለው ኩባንያ ለሁለት ዓመታት ኮንትራት በኢትዮጵያ መንግሥት 30 ሚሊዮን ዩሮ እየተከፈለው የቀድሞው የኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሸን ኮርፖሬሽን የቴሌን የሥራ አመራር ለሁለት ዓመት ለማስተዳደር በኮንትራት መውሰዱ የታወሳል። በአዲስ ሁኔታ የተዋቀረው ኢትዮ ቴሌኮም ኩባንያ ምደባ በቴሌ ሠራተኞች ላይ ያለመረጋጋትን የፈጠረ ከመሆኑም ባሻገር በድርጅቱ ሥራ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ማሳደሩ ታውቋል።

በጥቅሉ 5 የስራ ኃላፊነት መደብ ባለበት አዲሱ ተቋም እስካሁን የአራቱ የስራ ምደባ የተጠናቀቀ ሲሆን አብዛኛዎቹ የቀድሞው የቴሌ ሠራተኞች ይካተቱበታል ተብሎ የሚጠበቀው ኤን5 የተባለው የሥራ መደብ እስካሁን ሠራተኛ ያልተመደበበት በመሆኑ አብዛኛው የድርጅቱ ሠራተኞች ስለመጪው ዕጣ ፈንታቸው እያሰቡ የሚገኝ ሲሆን በሚቀጥለው ሳምንት ውስጥ ቁርጣቸውን እንደሚያውቁ ታውቋል።

በመሆኑም ከአብዛኛው የቴሌ ሠራተኞች መካከል ጥቂቶቹ በዚሁ ምድብ ከተመደቡ በኋላ ቀሪዎቹ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ደግሞ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር የተያያዙ ሌሎች ፕሮጀክቶች ውስጥ የሚመደቡ አሊያም የሚንሳፈፉ እንደሚኖሩ ተገልጿል፡፡ ኩባንያው ለሚያቅፋቸው ሠራተኞች የደሞዝ ጭማሪ የሚያደርግ ሲሆን የሚቀንሳቸው ሠራተኞች የወደፊት ዕጣ ፈንታቸው ምን እንደሚሆን የታወቀ ነገር የለም።

ኩባንያው የሥራ አፈጻጸሙ ከ60 በመቶ በታች ከወረደ ኮንትራቱን እንዲሰረዝ ለወያኔ መንግሥት ቃል ከመግባት አልፎ ውል ስለፈረመ እንዲሁም የአገልግሎት ብቃቱን ማሳደግና ገቢውን በመጨመር ትርፋማነቱን ማሳደግ እንደሚኖርበት ትእዛዝ ስለተቀበለ ከብዙ ሺህ ከሚቆጠሩ ሠራተኞች ውስጥ ጥቂቶችን ብቻ እንደሚያስቀር ተጠቁሟል።ከዚህ ሌላ በቀጣይነት በኅብረተሰቡ ላይ የታሪፍ ጭማሪ ለማድረግ መዘጋጀቱም ታውቋል።ምክንያቱም ገቢውን ማሳደግ አለበት ስለተባለ ይህንን ተግባራዊ የሚያደርገው ደግሞ በኅብረተሰቡ ላይ የታሪፍ ጭማሪ በማድረግ ይሆናል።

ሌላውና ዋናው አሳሳቢው ነገር ከመስራቤቱ የሚቀነሱ ሰራተኞች የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል? የሚለው ነው።በርካታዎቹ የቤተሰብ አስተዳዳሪ በመሆናቸው ከሥራዬ የምቀነስ ከሆነ ቤተሰቤን እንዴት አድርጌ ላስተዳድር ነው? በማለት ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ፣ ድንጋጤና መረበሽን በአብዛኛው ሠራተኛ ላይ መፍጠሩ ታውቋል ።