በዓለም ዋንጫ ስም በጠራራ ፀሐይ የዘረፉት ተቀጡ ፤ ገንዘቡ ግን መና ሆኖ እንደቀረ ነው

(ኢትዮ እማማ)
ባለፈው አምት ክረምት ላይ ወደ ደቡብ አፍሪካ የአለም እግር ኳስ ዋንጫ ለመመልከት እወስዳችኋላሁ በማለት በጠራራ ፀሐይ የዘረፉት የአስካሉካን ድርጅትና አራት ተባባሪ ሰዎች ላይ በማታለል ወንጀልና ከተሰጣቸው የስራ ፈቃድ ውጭ በመስራታቸው እንደ ተቀጡ ተገለፀ። ገንዘቡ ግን አሁንም መና ሆኖ እንደቀረ ነው።

ወደ ደቡብ አፍሪካ የአለም እግር ኳስ ዋንጫ ለመመልከት እወስዳችኋላሁ በማለት ከወራቶች በፊት ከ1,200 ሰዎች ላይ ከየአንዳንዳቸው ላይ 37,582.65 ብርና ከዚያ በላይ በማጭበረበ በአጠቃላይ ከ45,099,180 (ከአርባ አምስት ሚሊዮን ዘጠና ዘጠኝ ሺህ አንድ መቶ ሰማኒያ) ብር በላይ በመቀበል ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመሔድ ገንዘብ ከፍለው ከተመዘገቡት መካከል 47 ወጣቶች ወደዚያው ሲጓዙ ቀሪዎቹ ግን መጓዝ አልቻሉም።የተጓዙትም ቢሆኑ ተጉሏልተው ነው የተመለሱት ከዚህም ሌላ 70 ዶላር የሚሸጠው የመግቢያ ቲኬት ዋጋ አስካሉካን ትሬዲንግ የተባለው ኩባንያ ባለቤቶች ከሆኑት መካከል አንዱ የሆኑት፣ አቶ ግርማይ ገብረ ሚካኤል ይሕደጎ ያስከፈላቸው 950 ዶላር ነው።

ስንዴና በርበሬ ፣ቤቱንና መሬቱን ፣ታክሲውንና ሌሎች ንብረታቸውን ሸጠው ወዘተ. ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመጓዝ ተስፋ ሰንቀው የነበሩ ወገኖቻችንን ያጭበረበረው አቶ ግርማይ ገብረ ሚካኤል አገር ለቆ ከመውጣቱ በፊት ተበዳዮች መንግሥት እንዲያውቅ ያደረጉ ቢሆንም፤ የሀገሪቱ መንግሥት ተገቢ ዕርምጃ አልወሰደም። ከዚህ ሌላ መንግሥት አዳራሹን በመፍቀድ በርካታ ሰዎች ለመጭበርበራቸው መንስሄ ከመሆኑም በላይ ግለሰቡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ስፖንሰር እንደተደረገ መነገሩ ፣የአስካሉካን ማስታወቂያ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መተላለፉ ፣በመንግስትም ሆነ በሚዲያው ከፍተኛ ድጋፍ እንድነበረው ያመላክታል ።

ከዚህ ሌላ ግለሰቡ በአዲስ አበባ መስተዳድር በኤፍ ኤም አዲስ 98.1 ኢትዮፒካ ሊንክ በተባለው ፕሮግራም ላይ በሱ ስፖንሰር አድራጊነት በርካታ ቅስቀሳዎች ተደርጎለታል። እንግዲህ ኢትዮፒካ ሊንክ የተባለው የኤፍ ኤም 98.1 ፕሮግራም ተጽእኖ ፈጣሪ ከሚባሉት ፕሮግራሞች መካከል አንዱ እንደሆነ የሚታወቅ ነው። ታዲያ ወደ ደቡብ አፍሪካ እግርኳሱን ለማየትም ሆነ ለሌላ ነገር ለመሄድ የሚፈልግ ሰው ካለ ይህን የማስታወቂያ መስማቱ ብቻ በቂ ነው ።መንግስት በግል ንግድ ላይ የተሰማራውን የታሜሶል ኮምኒኬሽን ባለቤት የሆነውን አቶ ሰለሞንን የመስተዳድሩ የመገናኛ ብዙሐን ሥራ አሰኪያጅ በማድረግ ከነ አቶ በረከት፣ ከነ አቶ አባይ ፀሐዬና ከነአቶ ህላዊ ዮሴፍ በስልክ የሚሰጠውን ትእዛዝ ተግባራዊ በማድረግ ከአንዳንድ የግል ተብዬ የስፖርት ጋዜጠኞች ጋር በመመሳጠር በብዙ ሚሊየን የሚቆጠር የሕዝብ ብር እንደቅርጫ መከፋፈላቸው አንሶ የንፁሀንን ላብ በጠራራ ፀሐይ እንዲዘረፉ ማድረጉ በመንግስት በኩል ያሉ ግለሰቦች ላይ እና በሚዲያውም ላይ ከፍተኛ የማጣራት ስራ ሳይሰራ የፌዴራሉ ዓቃቤ ሕግ በአስካሉካን ድርጅት የ30 ሺህ ብር ቅጣትና በአራት ተባባሪ ተከሳሶች ላይ የ4 ዓመት ከ6 ወር ጽኑ እስራት እንደተወሰነባቸው ተነግሯል።

የፍርድ ቤቱ 2ኛ ወንጀል ችሎት ሕዳር 10 ቀን 2003 ዓም የጥፋተኛ ውሳኔ ከሰጠ በኋላ ትናንትና ታህሳስ 14 ቀን 2003 ባስቻለው ችሎት በድርጅቱ ምክትል ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ መና ተረፈ አልሰሙ፣ በድርጅቱ ገንዘብ ያዥ አቶ ግርማ በቀለ ወዳጆ፣ በአቶ ብርሃኑ ቢንጫም ሚሊኪሶና በአቶ ደረጃ ባና ላይ እያንዳዳቸው በ4 ዓመት ከ 6 ወር ጽኑ እስራትና ከሕዝባዊ መብቶቻቸው ለ2 ዓመት አንዲታገዱና በተጨማሪም የ5 ሺህ ብር መቀጮ እንዲከፍሉ እንዲሁም በአስካሉካን ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማሕበር ላይ የ30 ሺህ ብር ቅጣት መወሰኑን ገልጾ የፍትሐ ብሔር ጉዳይ ራሱን ችሎ በመታየት ላይ እንደሆነና የድርጅቱን ንብረት እንዳይንቀሳቀስ በፍርድ ቤት ትእዛዝ መታገዱ ተገልጿል።

በውሳኔው አብዛኛው ደስተኞች አለመሆናቸው ታውቋል። ዛሬም ያልተመለሱ በርካታ ጥያቄዎች አሉ። ይህ የወያኔ ድርጅት ወደ ደቡብ አፍሪካ ለሚሔዱ ሰዎች ቪዛ የሚሰጠው እሱ እንደሆነ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ተገልጿል፡፡ ይሁንና ይህ ሁሉ ማስታወቂያ ሲተላለፍ ይመለከተናል ያሉ የመንግስት አካላት የት ነበሩ?የማስታወቂያ ድርጅቶች ይህ ድርጅት ሕጋዊ መሆኑን ሳይረጋገጡ ወይስ በትህዛዝ ነው ማስታወቂያውን የሠሩት ?ያም ሆነ ይህ ሕዝቡን እንዲያጭበረብር አስተዋጽኦ ስላደረጉ ለምን አልተጠየቁም? በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ የኮሚዩኒኬሽን ቢሮዎች ይህ ድርጅት ሰዎችን ሰብስቦ ስለሚሠራው ሥራ መግለጫ እንዲሰጥ የመንግሥት አዳራሽ እስከመፍቀድ ደርሰዋል።እነሱስ ለምን ፈቀዳችሁ ተብለው አልተጠየቁም?….

በወያኔዎች የተቋቋመው ወጋገን ባንክ ሰዎቹ ያስገቡት ገንዘብ በአስካሉካን አካውንት መሆኑን ብቻ ከመግለጽ ይልቅ፣ 45 ሚሊዮን ብር ይሆናል የተባለውን ገንዘብ በምን ያህል ጊዜ ማውጣት እንደሚችልና ያወጣበትን ጊዜ በባንኩ ሕግ መሠረት ትክክል መሆኑን ማረጋገጥ ሲገባው የባንኩ ኃላፊዎች በወቅቱ ለመገናኛ ብዙሐን እንደተናገሩት “በባንኩ ውስጥ አካውንት ለሚከፍቱ ማናቸውም ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች የምናደርገውን የደንበኝነት አገልግሎት ነው ለደንበኛችን የሰጠነው፤” ብለዋል፡፡

ኃላፊዎቹ እንደሉት፣ የባንክ ሒሳቡ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዳይንቀሳቀስ እስካልተከለከለ ድረስ ሒሳቡን ማንቀሳቀስና መጠቀም የባለቤቱ ኃላፊነት መሆኑንም በወቅቱ ገልፀው ነበር።ይህ ደግሞ የሚያሳየው ግለሰቡ ገንዘቡን እንዲያሸሽ ሁኔታዎች እንደተመቻቸለት የሚያሳይ ነው፡፡ ምክንያቱም ተጎጂዎቹ በእርግጠኝነት ይህ ድርጅት ቢሮ አምጥታችሁ ክፈሉ ቢላቸው ኖሮ ስለሚጠራጠሩት የባንኩን የሕግ ከለላ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ በመንግስት አይዞ ባይነት ለማጭበርበር ተጠቅሞበታል።

ከዚህ ሌላ የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በሕዳር 16 ቀን 2002 ዓ.ም. “ለሚመለከተው ሁሉ” በሚል ርዕስ የተፃፈው የድጋፍ ደብዳቤ፣ “ድርጅቱ የዓለም ዋንጫ ቲኬት ሽያጭ ከማከናወን በተጨማሪ፣ የአገራችንን መልካም ገጽታ ለመቀየር የሚያደርገው ጥረት የሚደገፍ በመሆኑ፣ የሚመለከተው ሁሉ አስፈላጊውን ሁሉ ትብብር እንዲያደርግለት እንጠይቃለን፤” የሚል ደብዳቤ መፃፉ በመንግስት በኩልም ከፍተኛ ድጋፍ እንደነበረው ያሳያል።

በሌላ በኩል “በሌሎቹ ላይ ይህን ያህል እስራት ተፈርዶባቸውል ፤ ዋናው ግለሰብ ከሚገኝበት ከጀርመን ሀገር በዓለም አቀፉ ኢንተርፖል አማካይነት ተይዞ ሊመጣ ነው፤ የድርጅቱን ንብረት እንዳይንቀሳቀስ በፍርድ ቤት ትእዛዝ ስላገድን በፍትሐ ብሔር ጉዳይ ራሱን ችሎ በመታየት ሰለሆነ አይዟችሁ ፤ገንዘባችሁን ታገኛላችሁ ” እያሉ የተስፋ ዳቦ እያስገመጧቸው እንደሆነ ታውቋል። የሰለባዎቹ ገንዘብ ግን አሁንም መና ሆኖ እንደቀረ ነው።