በኢትዮጵያ እየተከሰተ ያለው የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት ከመጠን በላይ እየተባባሰ በመምጣት ላይ የገኛል

ኢትዮ እማማ
ከ2000ዓ/ም ጀምሮ በኢትዮጵያ እየተከሰተ ያለው የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት አፋጣኝ መፍትሄ ካላገኘ በሂደት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ አሽመድምዶ ሊጥለው እንደሚችል አስቀድሞ ቢገለፅም የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርም ሆኑ ተከታዮቻቸው ጉዳዩን እንደቀላል ከመቁጠራቸውም በላይ ከወቅቱ ከጉንፋን በሽታ ጋር በማነፃፀር በቁጥጥር ስር እንደሚያውሉት በሀገሪቱ ፓርላማ ላይ እስከመናገር ደርሰው የነበረ ቢሆንም ተገቢና ወቅታዊ እርምጃ በወቅቱ ባለመወሰዱ በአሁኑ ወቅት የኑሮው ውድነት ከመጠን በላይ እየተባባሰ በመምጣት ላይ የገኛል።

በተለይም የመለስ አስተዳደር የውጪ ምንዛሬ ማስተካከያ ካደረገ በኋላም በአሁኑ ወቅት የዋጋ ንረቱ ከመባባስ አልፎ ከቁጥጥር ውጪ ከመሆኑም ባሻገር ይህ ሳይበቃ ይብስ ብሎ ከሰሞኑ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ በ3 ወር ውስጥ ለ3ተኛ ጊዜ 22 በመቶ ጭማሪ ማድረጉ ሕዝቡን ወደ ባሰ ድህነት እየከተተው መሆኑ ታውቋል።
የሀገሪቱ ንግድ ሚኒስቴር በወቅቱ እንዳሳወቀው ከውጪ ምንዛሬ ማስተካከያና ከዓለም የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ጋር ተያይዞ ባለፈው ወር በሊትር 14 ብር ከ87 ሣንቲም የነበረው የቤንዝን ዋጋ ወደ 15 ብር ከ88 ሣንቲም አሻቅቧል።

ይህም ካለፈው ጥቅምት ወር በ10 በመቶ እድገት አሳይቷል። የነጭ ናፍጣ ዋጋ ወደ 13 ብር ከ24 ሣንቲም ፣ ኬሮዥን 11 ብር ከ75 ሣንቲም፣ቀላሉ ጥቁር ናፍጣ 12 ብር ከ13 ሣንቲም ፣ከበድ ያለው ጥቁር ናፍጣ 11 ብር ከ76 ሣንቲም ፣የአውሮፕላን ቤንዚል 15 ብር ከ15 ሣንቲም በሊትር ይሸጣል።አንድ በርሜል በዓለም አቀፍ ደረጃ 85 ዶላር ነው የሚሸጠው።ይህ ዋጋ እስከ መጪው ጃንዋሪ 2011 ድረስ ሲሆን ከዛ በኋላ ሌላ የዋጋ ማስተካከያ እንደሚደረግ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አስታውቋል። ይህ ደግሞ ሌላ ሕዝቡን ወደ ባሰና አስከፊ ሕይወት ይከተዋል ተብሎ ተፈርቷል።

ሌላው ስጋት በመጪው ፌብርዋሪ 1 ቀን 2011 ከኢትዮጵያ ፔትሮልዬም ኢንተርፕራይስ (EPE) ጋር ነዳጅ ለማቅረብ የተስማማው የሱዳን ፔትሮልዬም ኮርፕሬሽን(SPC) በሱዳን ሪፍረንደም የሚካሄድበት ወቅት በመሆኑ ለሦስት ወር ነዳጅ መላኩን ያቋርጣል።በዚህም የተነሳ በሀገሪቱ ውስጥ የነዳጅ እጥረት ስለሚከሰት ከዋጋው ጭማሪ ጋር ተዳምሮ ሕዝቡን ወደ ባሰ ችግር ሊከተው እንደሚችል ከወዲሁ እየተነገረ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ፔትሮልዬም ኢንተርፕራይስ ግን በቂ የነዳጅ ክምችት ስላለው ሁኔታው እንደማያሳስበውና በሱዳን በጃንዋሪ 9ቀን 2011 በሚካሄደው የሪፍረንደም ውሳኔ መጥፎ ሁኔታ እንኳን በሱዳን ቢፈጠር ከሌላ ካምፓኒ ጋር ውል ለመፈፀም እንደተዘጋጀ ይገልፃሉ።ኃላፊዎቹ ይህን ይበሉ እንጂ አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ከሆነ በሱዳን ያለው ሁኔታ ድምፀ ውሳኔው ተካሂዶ መረጋጋት እስከሚፈጠር ድረስ በጎሮቤት ሀገሮች ላይ አሉታዊ ተፅእኖ መፍጠሩ አይቀሬ እንደሆነ ይገልጻሉ።

በተለይም የነዳጅ ሀብት ባለቤት የሆነችው ደቡብ ሱዳን በድምፀ ውሳኔ ነፃነቷን ካወጀች በኋላ እስከምትረጋጋ ደረስ ጊዜ ሊወስድባት ይችላል። ይህ ብቻ አይደለም የሱዳኑ መሪ ዑመር ሐሰን አልባሽር” ምንም ተባለ ምን ውጤቱን በፀጋ እንቀበላለን “እያሉ ሲሆን በተለይም ከውጪ እየተደረገባቸው ያለው አንዳንድ ጫናዎችና የቃላት እንካሰልምትያ በዓለም አቀፍ ፍርድቤት የመታደናቸው ሁኔታ ተዳምሮ በፕሬዝዳንቱ ላይ የፈጠረባቸው ጫናን ለማስወገድና ስማቸውን ለማደስ ሲሉ ቃላቸውን ሊጠብቁ ይችላሉ ቢባልም ሀገሪቱ እስከምትረጋጋ ድረስ ግን ምንም ተባለ ምን ነዳጅ የማምጣቱ ሁኔታ ጊዜ መውሰዱ አይቀርም ባይ ናቸው። በዚህም የተነሳ የኢትዮጵያ ፔትሮልዬም ኢንተርፕራይስ ምንም የነዳጅ ክምችት ቢኖረውም እጥረቱ መከሰቱ አይቀሬ ነው ይላሉ።ይህንን ችግር ለመቅረፍ ከሌላ ካምፓኒ ጋር ውል ለመፈፀም ቢገደዱ እንኳን ወደ ሀገሪቱ ነዳጁን ለማስገባት የሚያመጣበት የመጓጓዣ ዋጋ ስለሚጨምር ይህንን ወጪ ለማካካስ ሲባል የሀገሪቱ መንግስት ጫናውን መሸከም ስለማይፈልግ ጫናውን ወደ ሕዝቡ ላይ ስለ ሚያወርደው ችግሩ ከአሁን በባሰ መልኩ እየተባባሰ ሊሄድ እንደሚችል ነው አስተያይት ሰጪዎች የሚገለጹት።

በመሆኑም 10,000ቶን ነዳጅ በየወሩ ከነዳጅ ክምችቱ የሚነሳ ስለሆነ ይህንን በመረዳት ይመስላል የኢትዮጵያ ፔትሮልዬም ኢንተርፕራይስ (EPE) ከሱዳን ተጨማሪ ነዳጆችን ለማምጣት አቅዷል። ስለሆነም የቶታል ኢትዮጵያ 200 የነዳጅ መኪናዎች ሱዳን የሚገኙ ሲሆን ተጨማሪ መኪናዎችን ለመላክም ሰዎች መመደባቸው ታውቋል።ያም ሆነ ይህ በሀገሪቱ በየጊዜው እየጨመረ በሚሄደው የነዳጅ ዋጋ ሳቢያ የሰዉ የኑሮ ሁኔታ እየላሸቀ ከመሄዱም ባሻገር የመኖር አቅሙና ተስፋውም እየተሟጠጠ ይገኛል።ለሕዝብ ሀሳቢ ነኝ የሚለው መንግስት ለአራተኛ ጊዜ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ለማድረግ እየተዘጋጀ ሲሆን በተለይም በቀጣዩ ወር በሚያደርገው ጭማሪ የአብዛኛውን ህብረተሰብ ኑሮ ያናጋዋል የሚል ፍራቻ አሳድሯል።

በየጊዜው በሚደረገው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ በተለይም በከተማ ነዋሪውና በመንግስት ሠራተኛው ላይ ከፍተኛ ችግር ከመፍጠሩም ባሻገር በኑሮው ውድነት ሳቢያ ኑሮን መቋቋም ተስኖት ተስፋው ተሟጦ ለሚገኘው ለኢትዮጵያ ሕዝብ የመለስ መንግስት የነዳጅ ዋጋ ድጎማ ፣ የደሞዝና የጡረታ ማስተካከያ ካላደረገ ፣የዋጋ ንረትን የሚያባብሱ ነጋዴዎችን ካልተቆጣጠረ፣ተጨማሪ የእሴት ታክስና ከኑሮ ጋር ተያያዥነት ባላቸው ምርቶች ላይ ክፍያዎችን ካላስወገደ ወዘተ. የሰዉ ብሶት ፈንድቶ የሀገሪቱ መንግስትን ሊቆጣጠረው ወደ ማይችለው አዝቅት ውስጥ ሕዝቡን ሊከተው ይችላል በማለት አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከወዲሁ መንግስትን በማሳሰብ ላይ ይገኛሉ።