ወያኔ ዳያስፖራ ወጣቶችን ሊሸነግል? ሸንቃታዉ ዘካሊፎረኒያ

የመለስ ዜናዊ ፕሮፓንዳ መሳሪያዎች፣ ካድሬዎቻቸዉና ጋዜጣዎቻቸዉ በአሁኑ ወቅት በሰፊዉ የተያያዙት ፈሊጥ ቢኖር በዉጪ አገር የሚገኙ ወጣት ኢትዮጵያዉያን እንደ እስራኤላዉያን ወይም እንደ ደቡብ ኮርያዉያን ወይም እንደ ህንዶች ወጣቶች የኢትዮጵያ ወጣቶች የዉጭ አገር ቴክኖሎጂን ወደ ኢትዮጵያ ማስገባት እንዲችሉ የቅስቀሳ ዘመቻ እያካሄዱ ናቸዉ። አርከበ እቁባይ የመለስ ዜናዊ አማካሪ ሆኖ ሲሾም ለሚቀጥሉት አምስት አመታት በተነደፈዉ የቴክኖሎጂ ወደ ኢትዮጵያ መግባት ስኬታማ እንዲሆን በዉጭ አገር የሚገኙትን ኢትዮጵያዉያን ወጣቶችን ማስተባበር ይችላል ከሚል ሰትራተጂ የተነደፈ ፕላን ይመስላል የአሁኑ ቅስቀሳ አጀማመር። በዉጭ አገር የሚገኙ ወጣት ኢትዮጵያዉያን በአርከበ እቁባይ ላይ ብዙ ጥላቻ የላቸዉም ከሚል እምነት የተደረገም ይመስላል። ሆኖም ግን መለስ ዜናዊና የፕሮፓጋንዳ መሳሪያ የሆኑት ሆዳሞች ያልተረዱት ብዙ ነገሮች አሉ።

በአንደኛ ደረጃ፦ የእስራኤልም ሆነ የህንድ ወይም የደቡብ ኮርያ መንግስት “በዘር ከፋፍለህ ግዛ” የመንግስት ፖሊሲ ህዝባቸዉን ከፋፍለዉ ገዝተዉ አያዉቁም። ይልቁንም ይከተሉት የነበረዉና አሁንም የሚከተሉት ፖሊሲ የየአገራቸዉን ብሄራዊ አንድነትና የህዝባቸዉን አንድነት የሚያጠናክር ፖሊሲ እንጂ ሌላ ከፋፋይ ፖሊሲ አይደለም። ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚካሄደዉ የአምባገነንነትና የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ በዉጭ አገር በሚገኙ ኢትዮጵያዉያን ላይ ቀጥተኛ ነጸብራቅ አለዉ። በዘር፣ በፖለቲካና በሀይማኖት የተከፋፈለን ወጣት ዳያስፖራ ቴክኖሎጂን ይዘህ ተመለስ ወይንም ገዝተህ ላክ ወይንም ሰርቀህ በአገርህ ላይ አዉል ማለት ተጨባጭ ሁኔታዎች ካለመገንዘብ የተነሳ ወይንም በጥቅም እየሸነገልን የፖለቲካ ኩርፊያዉን እንወጣለን ከሚል ግምት የተነሳ የተደረገ ይመስላል።

በሁለተኛ ደረጃ፦ በዉጭ አገር ይኖሩ የነበሩ እስራኤላዉያን ሆኑ ህንዶች ሆኑ ደቡብ ኮርያዉያን እናት አገሮቻቸዉ አብዮታዊ ዲሞክራሲ በሚል የፖለቲካና የኢኮኖሚ እድገት ፈለግ ተከትለዉ ከቻይና ጋር አልሰሩም። እነዚህ አገሮች በከፈቱት የነጻ ገበያ ፖሊሲ መሰረት አገሮቻቸዉ በኢኮኖሚና በቴክኖሎጂ እንዲያድጉ በዉጭ አገር የሚኖሩት ዜጎቻቸዉ በአገር ወዳድነት ቴክኖሎጂ እየገዙም ሆን እየሰረቁ ወደ እናት አገሮቻቸዉ በብዛት ልከዋል። በግል ደረጃ ቴክኖሎጂ ገዝተዉ ወደ አገራቸዉ ለተመለሱ ሁሉ መንግስት አስፈላጊዉን ሁኔታ እያመቻቸ የሚያደርጉት ኢንቨስትመንት ፈሬያማ እንዲሆን ብዙ ድጋፍ ሰጥቷል። አንድ ኢትዮጵያዊ ገንዘብ ወይም ቴክኖሎጂ ወይም የኢንቨስትመንት ፕላን ይዞ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ ተግባራዊ ለማድረግ ሲሯሯጥ ባለጊዜዎች በአሻጥር ተመክተዉ በጎን ኢኒቨስትመንቱን ለራሳቸዉ ጥቅም ተግባራዊ አድርገዉ ከጫወታ ዉጪ ያደርጉታል። እንዲህ ያለ ሁኔታ በእስራኤል ወይም በህንድ ወይም በደቡብ ኮሪያ ተከስቶ አያዉቅም። ሙስና፣ ዘረኝነትና ምግባረ-ብልሹነት እናት አገራችን ኢትዮጵያን ከፉኛ ጎድተዉ ሳለ እንዲህ አይነቱ የቴክኖሎጂ ማስገባት ስትራቴጂ መነደፉ እንደተለመደዉ የፖለቲካ ቧልት ለመጫወት ካለሆነ በቀር በቀላሉ የሚሳካ አይመስልም።

በሶስተኛ ደረጃ፦ መለስ ዜናዊ 40 ሚሊዮን ብር በጀት መድቦ የዳያስፖራ ሚኒስትር ሰይሞ በዳያስፖራዉ ላይ በሚስጥር የስለላ ተግባር እየፈጸመ ነዉ ያለዉ። ይህ የስለላ ተግባር በዳያስፖራዉ ዘንድ በሚገባ ታዉቆ ነዉ ያለዉ። የግንቦት 2010 ምርጫ የዘመኑ ቀልድ በሆነበት ማግስት ብሄራዊ እርቅ እንኳ ሳይደረግ መለስ ዜናዊ አንዲያዉ “ድህነትን በሚቀጥለዉ አምስት አመት እናጠፋለን” በማለቱ ብቻ ዳያስፖራዉ በቀላሉ ተፎግሮ ይሸነፋል ተብሎ የተነደፈ ሰትራቴጂም ይመስላል። ወይንስ ተቃዋሚ ድርጅቶችን ያጠፋዉ የምርጫ 2010 ዉጤት ማዘናጊያ እንዲሆን የተነደፈ የመነጋገሪያ ነጥብ ነዉ? በወያኔና በዳያስፖራዉ መካከል ያለዉ የፖለቲካ ልዩነት ይባስኑ ብሎ ተካረረ እንጂ ጨርሶ አልተቀራረበም።

በአራተኛ ደረጃ፦ “የጉልቻ መቀያየር ወጥ አያጣፍጥም” የሚባለዉን የአባቶች ተረት መለስ ዜናዊ ጨርሶ የዘነጋዉ ይመስላል። አፄ ሀይለ ስላሴና መንግስቱ ሀይለ ማሪያም ካቢኔታቸዉን ቀያይረዉ እንደነበር ረሳ ወይ? እንደታየዉ ከሆነ ብዙ የወያኔ ባለስልጣናት ከአንዱ ሚኒሰቴርነት ወደ ሌላዉ ሲቀያየሩ ተስተዉለዋል። እስቲ እንደዉ ሰቴት ሚኒስትር ሆነዉ ከተሾሙት ስንቶቹ ናቸዉ ወያኔዎች? ደርግ “የለዉጥ ሀዋርያት” ብሎ የሾማቸዉ ወታደሮች በየሚኒስትር መስሪያ ቤቶች የደርግ ቁራኛ ጠባቂዎች አልነበሩምን? ለመሆኑ የትኛዉ ሚኒስትር ነዉ ከመለስ ዜናዊ እዉቅና ዉጪ በራሱ የፖሊሲ ወሳኝ የሆነዉ? ዳያስፖራዉ አዉነተኛ ለዉጥ ፈላጊ እንጂ የአሸር ባሸር ፖለቲካ ሽንገላ ፈላጊ አይደለም። እንደነዚህ ያሉ ሁኔታዎች ለዉጥ ፈላጊ ዳያስፖራዉን ማንቀሳቀስ ይቅርና ካንዴላዉን እንኳ አያሞቁም። ያዉም ተሯሩጦ ቴክኖሎጂ ይዞ አገር ቤት እንዲገባ። ድንቄም እቴ።

ወያኔዎች የጀመሩት የፕሮፓጋናዳ ዘመቻ ላይሳካ ይችላል ብዬ የምገምተዉ ከላይ የጠቀስኳቸዉ አበይት ነጥቦች ስንክሳር ስለሆኑ ነዉ። በኢትዮጵያ የሚካሄደዉ ፖለቲካ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ዳያስፖራዉ ላይ ይንጸባረቃል። የኢኮኖሚ ዘረኝነት (Economic racism) የኢትዮጵያን ህዝብ ክፉኛ ጎድቶታል። የትግራይ ልማት ድርጅት በግል ድርጅት ስምና በመንግስት ስም ከተራ ችርቻሮ እስከ ትላልቅ ኮርፖሬት ኮንትራክተርነት የአገሪቱን ኢኮኖሚ እየተቆጣጠረ ባለበት ሰአትና ዳያስፖራዉም ይህ ስርአት እንዲያከትም በሚሯሯጥበት ወቅት ድህነትን በአምስት እናጠፋለን ብሎ መመጻደቁ በህዝብ ላይ ከማሾፍ በስተቀር ምንም ትርጉም አልሰጠዉም። ወጣቱ ከየዩኒቨርስቲዉ ተመርቆ የወያኔ/ኢህአዴግ አባል ሆኖ ካልተመዘገበ ስራ እንኳን አያገኝም። ምንስ አይነት ስታቴጂ እንደሆነ ግራ ይገባኛል።

በምዕራባዉይን አገሮች ለብዙ አመታት ተምረዉና ኖረዉ የነበሩ በአሁኑ ወቅት በብዛት ወደ ህንድ ተመልሰዉ ታላቅ ኢንቨስትመንቶችን በቡድን በቡድን ጀምረዉ አገራቸዉን እያሳደጉ ይገኛሉ። ለመጀመሪያ ጊዜ በብዛት የተማረ ዜጋ ወደ ትዉልድ አገሩ ሲገባ የታየዉ በህንድ አገር ነዉ። ይህም Reverse brain drain እየተባለ ይጠራል። ቀደም ሲል ምዕራባዉያን አገሮች ከሶስተኛዉ አለም የተማረ የሰዉ ሀይል እየወሰዱ የሶስተኛ አለም አገሮችን የባለሙያ ድሀ ያደርጓቸዉ ነበር። አሁን ግን ጫወታዉ ተቀይሮ የህንድ መንግስት በሚያደርገዉ ትብብርና በዉጭ አገር የሚኖሩት ዜጎች ሁሉ እናት አገራቸዉን እንዲወዱ የአገር ዉስጥና የዉጪ ፖሊሲዉ በሁሉም ዜጎች ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረዉ ያደርጋል። ህንዶች እኔ እስካየሗቸዉ ድረስ አገራቸዉን በጣም ይወዳሉ። ወደ አገራቸዉ የማይልኩት ነገር ለም። እርስ በርሳቸዉ በጣም ይረዳዳሉ። ብዙ የተማረ የሰዉ ሀይል አላቸዉ። በተለይ በኮምፒዉተርና በኤሌክትሮኒክስ ቴክኖሎጂ አካባቢ በአሜሪካን አገር በቁጥር የሚስተካከላቸዉ የለም። የአገራቸዉ መንግስት በጣም እንዲማሩ የገፋፋቸዋል፡ ይረዳቸዋል። በተለይም በቴክኖሎጂ መስክ፣ በዩናይትድ ኔሽን፣ በአይ ኤም ኤፍና በአለም ባንክ ብዙ ባለሙያተኞች እንዲገቡ እርዳታ አድርጓል። ከስትራቴጂ አኳያ ሲታይ ይህ የመንግስት ድጎማ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለዉ። በአሁኑ ወቅት ህንድ የዚህ ሁሉ ኢንቨስትመንት ተጠቃሚ ሆና ትገኛለች።

የእኛዎቹ ገዢዎች ግን ከዘር ፖለቲካ አጣብቂኝ ሳይወጡ በምግባረ ብሉሹነትና በትምክህተኝነት ተጠምቀዉ በእብሪትና በማን አህሎኝነት ተዘፍቀዉ ነዉ የቀሩት።

አንድ ኢንቨስተር ኢትዮጵያ ዉስጥ ቴክኖሎጂ በማስገባት ወይም ገንዘብ በማሰገባት የሚያካሂደዉ ኢንቨስትመንት ብዙ ትርፍ የሚያስገኝና ፈጣን እድገት የሚያመጣ መሆኑን ወያኔዎች ካዩ ወይ በሽርክነት እንስራና ትርፉን እንቃረጥ ወይንም ኢንቨስትመንቱ እንዲከስር እናደርገዋለን ከማለት ወደ ሗላ አይሉም። ወያኔዎች ከራሳቸዉ በስተቀር እንሞትልሀለን ለሚሉት የትግራይ ህዝብ እንኳን ደንታ የላቸዉም። ምናልባት በዉጭ አገር ያሉ የወያኔ ካድሬዎችና መሰሎቻቸዉ ካልሆኑ በስተቀር ጥሪዉን ተቀብሎ ተግባራዊ ያደርጋል የምለዉ ሰዉ የለም።

የወያኔ መንግስት ያልዘራዉን ሊያጭድ ይፈልጋል። ወያኔዎች ከተንኮልና ከጠማማ ስራ በስተቀር ለዳያስፖራዉ የሰሩት ጥሩ ነገር የለም። አብዛኛዉ ዳያስፖራ ይህን ሁኔታ ደግሞ ጠንቅቆ ያዉቃል ብዬ አገምታለሁ። የእስራኤል፣ የህንድና የደቡብ ኮርያ መንግስታት በዉጭ አገር ለሚኖሩ፣ ለሚሰሩና ለሚማሩ ዜጎቻቸዉ ታላቅ ድጋፍ በመስጠት ቴክኖሎጂ ወደ አገሮቻቸዉ እንዲገባ ምክንያት ሆነዋል። ዛሬ እነዚህ አገሮች በታላቅ ታሪካዊ የእድገት ጎዳና ላይ ይገኛሉ። እነዚህ አገሮች ዉጭ አገር በሚኖሩ ዜጎቻቸዉ ላይ ለብዙ አመታት ያደረጉት ኢንቨስትመንት እነሆ ዛሬ ምን ያህል አገሮቻቸዉን እያሳደገ እንዳለ በየቀኑ ከዜና ማሰራጫ ጣቢያዎች፣ ከጋዜጦችና ከድህረ ገጾች አይተን የምንረዳዉ ነገር ሆኖ ቀርቷል። ወያኔዎች “ያልዘሩት አይበቅልም” የሚለዉን የአባቶች ተረት አይረዱም። “ሞኝ የእለቱን ብልህ ግን የአመቱን” ያስባል የሚለዉን ተረት የእስራኤል፣ የህንድና የደቡብ ኮርያ መንግስታት በቅጡ የተረዱ ለመሆናቸዉ ማወቅ አያዳግትም። መቼ ይሆን ወያኔዎች የሚረዱት? ህምምምም……….።

[email protected]