በብርቱካን ስም መወጋገዝና መለያየት ይቁም !በግርማ ካሳ
«ከፌዴሬሽኑ ጀርባ ልንሰለፍ ይገባል» በሚል ርእስ ባቀረብኩት ጽሁፍ፣ እጅግ በጣም በርካታ ምላሾች በኢሜል ደረሱኝ። ኢሜሎቹ በሙሉ የተቃዉሞ ኢሜሎች ናቸዉ። አንዳንዶቹ ከመቃወም አልፈዉ ስድብና ዛቻም አዝለዋል።
“ይህን የፌዴሬሽኑ ውሳኔ የማልስማማበት እንደሆነ በቅድሚያ እንዲታወቅልኝ እፈልጋለሁ። አስፈላጊ ከሆነ ለምን እንደማልስማማ ወደፊት በሰፊው የምመለስበት ጉዳይ ሊሆን ይችላል …. ነገር ግን ፌዴሬሽኑን ከማውገዝና ከመክሰስ በፊት ማነጋገር፣ ያለውን ሁኔታ በሚገባ መረዳት የሚያስፈልግ ይመስለኛል። የቀረቡትን ምክንያቶች በሰለጠነ መልኩ ቻሌንጅ በማድረግ፣ ነገሮች በተለየ ማእዘን እንዲታዩ ማድረግ ይቻላል። ሁሉም አሸናፊ የሆነበትን፣ የሁሉንም ቅሬታና ጥያቄ በሚመልስ መልኩ፣ ይህ በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ዙሪያ የተነሳውን አለመግባባት በሰላምና በንግግር ማንፈታበት ምንም ምክንያት የለም። ………ይህ ፌዴሬሽን፣ እስከነ ችግሮቹ፣ በሰሜን አሜሪካ ያለን ብቸኛ፣ ኢትዮጵያውያንን የሚያሰባሰብ አካል ነው። ልንከባከበው ይገባል። ከዳንኪራና ከስፖርት ባለፈ መልኩ፣ ኢትዮጵያውያንን ለቁም ነገር የሚያነሳሳ፣ በኢትዮጵያ የወገናችንን ሕይወት ለመለወጥ ትልቅ ራእይ ይዞ የሚንቀሳቀስ አካል እንዲሆን፣ ከዚህ ፌዴሬሽን ጀርባ ልንሰለፍ ይገባል። ይህ ፌዴሬሽን ብዙ ሊያደርግ የሚችል ፖቴንሻል ያለው አካል ነው። እንደግፈው እናጠናክረው እንጂ አናፍርሰው። …..…..በዚህ አጋጣሚም በወሰዱት ውሳኔ ባልስማማም፣ መልሰው ውሳኔያቸውን እንደሚመርምሩ ያለኝን ትልቅ እምነት በመግለጽ፣ ለሁሉም የፌዴሬሽኑ ቦርድ አባላት፣ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ያለኝን ምስጋናና አክብሮት መግለጽ እወዳለሁ …. “ (ከፌዴሬሽኑ ጀርባ ልንሰልፍ ይገባል ከሚለዉ ጽሁፍ የተወሰድ)
በዚህ ጽሁፍ አንዳንድ ወገኖች ምን ሊያስከፋቸዉ እንደቻለ በርግጥ ሊገባኝ አልቻለም። በሰለጠነዉ አለም እየኖርን የስድቡና የዛቻዉ ብዛት በርግጥ የሚያሳዝንና የሚያሳፋር ነዉ። ብዙዎቻችን ኢሕአዴግን እንቃወማለን እንላለን። ነገር ግን በምንሰራቸዉ ሥራዎችና ባሉን አስተሳሰቦች ከኢሕአዴግ ካድሬዎች በምንም አንደማንለይ እያሳየን ነዉ። በዳያስፖራ ያለዉ የመወጋገዝና ያለመቻቻል ፖለቲካ ኢሕአዴግ ከሚያራምደዉ ፖለቲካ ጋር እየተመሳሰለ ነዉ።
አንድ ሰዉ ከተሳሳተ፣ ወይንም ባይሳሳትም እኛ የማንፈልገዉ አስተያየት ከሰጠ፣ ያ ሰዉ ወዲያዉኑ እንደ ጠላት ነዉ የሚቆጠረዉ። «ወያኔ» ወይንም «ሆዳም» የሚል ስም ይለጠፍበታል። ትላንት ለትግሉ ጥሩ ያበረከተው፣ ትላንት የሰራዉ መልካም ሥራ ተረስቶ ዛሬ በአደባባይ ይብጠለጠላል።
አንድ ጊዜ ነዋሪነታቸዉ በኒዉዮርክ የሆነ፣ አቶ አባተ ካሳ የሚባሉ አንጋፋ ኢትዮጵያዊ በተለያዩ የአሜሪካ ከተሞች ሴሚናር ይሰጡ ነበር። በቺካጎ ያደረጉትን ሴሚናር ለመካፈል እድል አግኝቼ ነበር። በሴሚናሩ ከተማርኳቸዉና ከማስታወሳቸዉ ጠቃሚ ትምህርቶች መካከል ስለ «ስህተት» ያስተማሩት አንዱ ነበር። «ስህትት የማይሰሩ በሶስት ሊመደቡ ይችላሉ። እነርሱም የማይሰራ ሰዉ፣ የሞተ ሰዉ እና እግዚአብሄር ናቸዉ» ሲሉ ሌላዉ ስህተት እንደሚሰራ ነበር አቶ አባተ ያስረዱት።
የሚሰራ ሰዉ ሊሳሳት እንደሚችል ብዙ ጊዜ እንዘነጋለን። አንድ ሰዉ ስህተት ከሰራ «ሰዉ ነዉና መሳሳቱን እንደ ትልቅ ነገር መቁጠር የለብኝም። ለምን ወንድሜን አልመልሰዉም ? ለምን ቀስ ብዬ አላናግረዉም ? ድንገት ያልተገነዘበዉ ነገር ይኖራል ፤ ስህተት መሆኑን ካለኝ ልምድ አሳየዋለሁ። ሌላ ጊዜ ተመልሶ ድጋሚ እንዳይሳሳት እመክረዋለሁ» በሚል፣ ወንድማችንን ከስህተት ለማረምና ለማንሳት አንቸኩልም። ወዲያዉ በስሜት እንሞላና እራሳችንን ለንዴት፣ ለጥላቻ አሳልፈን እንሰጣለን።
ሌላዉ ያለብን ችግር በሌላዉ ጫማ ላይ ሆነን ነገሮችን ለማየት አለመሞከራችን ነዉ። ኢትዮጵያዊ ወገናችን ላይ ክስ ስናቀርብ፣ እኔ በርሱ ቦታ ብሆንስ ብለን አንጠይቅም። አንድ ሰዉ ከኔ አስተሳሰብ የተለየ ነገር ከተናገረ «ለምንድን ነዉ እንዲህ ያለዉ ? እስቲ እንዲሁ በጭፍን ፍርድ ከምሰጥ እርሱ ባለው መልኩ ነገሮችን ላማዛዝናቸዉ » አንልም። ለፍርድ፣ ለወገዛ እንቸኩላለን።
ይህ በዳያስፖራ ያለዉ ያለመቻቻል ፖለቲካ፣ አላወቅነዉ እንጂ በተዘዋዋሪ መንገድ እንቃወመዋለን የምንለዉን ገዢዉን የኢሕአዴግ ፓርቲን እየጠቀመ ያለ ፖለቲካ ነዉ። አንድ ሰዉ የበለጠ በሰደብነዉና ባወገዝነዉ ቁጥር፣ ከኛ እየራቀ ነዉ የሚመጣዉ። ብዙዎች፣ እኛ የዳያስፖራ ሰዎች ባለን ጽንፈኛና አክራሪ አቋም፣ የበለጠ እንዲያመሩ፣ ከትግሉ ሜዳ እንዲወጡ፣ ምናልባትም ወደ ኢሕአዴግ ካምፕ እንዲገቡ እየገፋፋናቸው ነዉ። የወዳጆችን ቁጥር እየቀነስን የሚቃወሙንን ቁጥር እያበዛን ነዉ። ይህ ደግሞ የሽንፈት ፖለቲካ ነዉ።
ወደ ፌዴሬሽኑ ጉዳይ ልመለስና ያለዉ ችግር በንግግር በዉይይት ይፈታ ነዉ የምለዉ። አለመስማማቶች፣ አለመግባባቶች አሉ። በርጋት በቅንነት ከተነጋገርን፣ እንኳን ይችን ቀላል ጉዳይ ቀርቶ ሌላ ከባድ ትልቅ ችግር መፍታት እንችላለን። «እገሌ ዉሸታም ነዉ … እገሌ ወያኔ ነዉ..እገሌ ገንዘብ በላ ..ወዘተረፈ» የሚል ትልቅን ሰዉ የማይመጠን አባባሎችን በጽሁፍና በድህረ ገጾች ባንወረወር ጥሩ ነዉ። ፌዴሬሽኑ የራሱ ሕገ ደንብ አለዉ። በደንቡም መሰረት ወሳኞቹ በተለያዩ ከተሞች ያሉ ቡድኖች የወከሏቸዉ የቦርድ አባላት ናቸዉ። የቦርድ አባላትም ለፌዴሬሽኑ ጥቅምና ሕልዉና ሲሉ ጠቃሚዉንና ኢትዮጵያዉያንን የሚያቀራርብ ዉሳኔ ይወስዳሉ የሚል እምነት አለኝ።
ብርቱካን ሚደቅሳ በዚህ በፌዴሬሽኑ ጉዳይ ምን እንደምታሰብ ብዙ አላውቅም። ነገር ግን እርሷ የመለያየትና የመወጋገዝ ምክንያት መሆን እንደማትፈልግ ግን መገመቱ አይከብድም። ማንም በባዶዉ ፣ በፍርደ ገምድልነት «ወያኔ፣ ሆዳም» ተብሎ እንዲሰደብ የምትፈልግ አይመስለኝም። አንድ ሰዉ «ወያኔ ነኝ» እንኳን ቢል በኢትዮጵያዊነቱ መከበር ይገባዋል ብላ የምታምን ሴት ናት። የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ፖለቲካ የፍቅር፣ የሰላም፣ የአንድነት፣ የጨዋነት፣ የመከባበር ፖለቲካ ነዉ። «ብርቱካን ሚደቅሳን እንወዳታለን፣ እናከብራታለን» የምንል ከሆነ እርሷ ለምትታገልለት፤ ለታሰረችለት የተከበረ አላማ መቆማችንን ማሳየት አለብን። በብርቱካን ስም ሌላዉን ኢትዮጵያዊ እየሰደብንና እያወገዝን ፣ ከኛ ጋር የማይስማማዉን ሁሉ «ወያኔ ነዉ» እያልን ለብርቱካን ሚደቅሳ ፍቅርንና አክብሮትን እገልጻለሁ ማለት ዉሸት ነዉ።
ዳያስፖራዉ ለኢትዮጵያ እንደ ወርቅ መዓድን ነዉ። በአንድ ላይ ከተሰባሰበ ትልቅ ሥራ ሊሰራ የሚችል አካል ነዉ። በአንድ ላይ እንዲሰባሰብ ደግሞ መቻቻል ይኖርበታል። ዴሞክራሲን የሰለጠነ ፖለቲካን መማር አለበት። ከአሜሪካ ቀመስ ጄሪ ስፒንገር አስተሳሰብ ወጥቶ ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን ማንገብ ይጠበቅበታል።