እሪ በይ ሀገሬ! – ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
ስማ ወገኔ! ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ከዚህ በላይ ክፉ ቀን የለም!! ቀን ሳለ የጨላለመብን፣ የህይወት ጣዕም ጠፍቶብን ምሬትና ሐዘን ሲፈራረቁቡን፣ በገዛ ምድራችን ባሮች በስደትም ባሮች፣ በገዛ ምድራችን ምጻተኞች በእንግድነት የሰፈርንባት ምድርም እንዲሁ ስደተኞች፣ በገዛ ምድራችን ተገፍተን እና አልቅሰን በስደትም በኃሳብ ማቀን እስከመቼ ነው?
እንግዲህ እሪ በይ ሀገሬ! የሕዝብሽ የርሀቡ ጽናት፣
የልጆችሽ ጉስቁልናና ሰቆቃ፣
ባርነት – ዋይታና እሪታ።
እሪ በይ ሀገሬ! መሬትሽ ተቸብችቦ ልጆችሽ በስደት ሲንከራተቱ
በአንጻሩ በዕዳን በጉያሽ ሲርመሰመሱ።
እሪ በይ ሀገሬ! አንድ ሳለን የለያየን የፖለቲካ መሪዎችሽ የልብ ጥመት፣
ክፋትና እልከኝነት።
እሪ በይ ሀገሬ! የእናውቅላችኋለን ፖለቲከኞችሽ ክህደትና ዲስኩር – ሲጠብሰን፥
ራስ ወዳድነታቸው – መንገድ ላይ ሲያስቀረን፥
መራራነታቸው – ሰላማችንን ስያሳጣን፥
ጥላቻቸውና ንቀታቸው – ጾማችንን ስያሳድረን።
እሪ በይ ሀገሬ! የኃይማኖት መሪዎችሽ ድንቁርና – ከፈጣሪ ሲለያየን፥
ሌብነታቸው – እጃችን በአፋችን ስያስጭነን፥
አድርባይነታቸው – እንደ እሳት ሲፈጀን፥
ምንደኝነታቸውና ነፍሰ ገዳይነታቸው – ከሀገር ሲያስኮበልለን።
እሪ በይ ሀገሬ! ልጄ ስትዬ በታሪክ ያስተዋወቅሽን ፈላስፋው እነ ዘርዓ ያዕቆብ ታሪካቸው በሰማንባትና
በተመላለሱባት ምድር ኑሮአቸው ሲቀርባቸው ለቁራሽ ዳቦ ሲባል ወሬኞች፣ ሐሜተኞችና
አሉባልተኞች ከለባት ልጓማቸው ፈትተው ባልተገራ አንደበታቸውና ብዕራቸው ሲሳለቁብሽ፥
እሪ በይ ሀገሬ! ኢትዮጵያን ለኢትዮጵያውያን ይተዉልን ዘንድም እሪታሽን አስተጋቢልን።
እሪ በይ ሀገሬ! የማጸንሽ ፍሬዎች ከጣላቶሽ አብረው ሊያወድሙሽ ሲመክሩ፥ እሪ በይ ሀገሬ! ጩሆትሽን አሰሚ ቸሩ መድኃኔአለም አይቶ ቢራራልሽ፣
እሪ በይ ሀገሬ! እንግዲህ አምላክ አባ አይደለም ሰምቶና አይቶ ዝም አይልሽ!!
የሰው እርዳታ የማይሻ በወጀብም በአውሎ ነፋስም መንገድ ያለው መንገደ ብዙ እግዚአብሔር ይርዳን! ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል