ከታሪክ አሻራ ከሲፖራ እስከ ብርቱካን ሚደቅሳ – ከሄኖክ ታፈሰ

የኢትዮጵያ ሴቶች በጀግንነት፤ በቆራጥ ተጋድሎ፤ በብርቱ ሰራተኛነት፤ በችግር ጊዜ መላ በመምታትና የቤተሰቡን መሰረታዊ ህይወት በመምራት፣ የረጅም ዘመን ልምድና ታሪክ አልቸው።
በዚህ ጉዳይ ቅዱስ መጽሃፍ ኢትዮጵያዊቷ ሲፖራ የባለቤቷን የታላቁን የእስራኤል መሪና ነብይ የሙሴን ህይወት ከሞት እንዴት ልታተርፍ እንደቻለች ያስረዳናል።
የሆነውም እንዲህ ነው ሙሴ ከቀይ ባህር በስተምእራብ ይገኝ በነበረው በምድያ ምድር በስደት ይኖር ነበር።በዚህም ስፍራ ሲፖራ የምትባል የኢትዮጵያ ተወላጅ ሴት አገባ።ዘጸአት ፪፡፳፩-፳፪ ሁለት ልጆችም ወለደች፣ የመጀመሪያውም ልጅ ጌርሸን ተባለ ትርጓሜውም በሌላ ምድር ምጻተኛ ነበርኩ ሲሆን ሁለተኛውንም አልዓዛር አለው ፍችውም የአባቴ አምላክ ረዳኝ ነው።በዚህም በሁለተኛው ልጅ መወለድ ጊዜም ሲፖራ ሙሴን ከሞት አዳነችው።
ሙሴ ለዚህ ህይወቱን ለማጣት ላደረሰው ነገር የተጋለጠው አንድ ታልቅ ስራ እረስቶ ነበር።በዚያን ጊዜ በቤተሰብ ውስጥ ወንድ ልጅ ከተወለደ እስከስምንተኛው ቀን ድረስ ይገረዛል።ይህም ህጻኑ ወደ እግዚአብሄር ቤት መቀላቀሉን ያመለክታል።
ሙሴ ይህን በአይሁዳውያን ዘንድ ሲፈጸም የኖረን ታላቅ ስርዓት ዘነጋ እግዚአብሄርም ተቆጣ ሊገድለውም ፈለገ።ዘጸአት ፬፡፳፬-፳፮ ይህንንም ሁኔታ ባለቤቱ ስፖራ በመረዳቷ በፍጥነትና በድፍረት ልጁን በስምንተኛው ቀን ማብቂያ ላይ ልትገርዝ ስለቻለች የእግዚያብሄርን ቁጣ አበረደች ፤ባሏንም ከሞት አዳነች፤ የእግዚአብሔርንም ትዕዛዝ እንደምታከብር አሳየች።
በዚያን ዘመን እስራኤላውያን በባርነት በፈርኦን እጅ የወደቁበት ጊዜ ነበር።ሙሴም ከስደት ተመልሶ እስራኤላውያንን እየመራ ከባርነት ነጻ እንዲያወጣ በእግዚአብሔር ታዘዘ ።ይህንንም ተግባር እያከናወነ እያለ ብልህና ተወዳጅ የሆነችው የሚስቱ ፍቅርና የሁለት ልጆቹ አጽናኝነት አስፈለገው።አማቱን ሲፖራንና ሁለቱን ልጆቹንም ወደ እርሱ አስመጣ።
በባርነት ለተወለዱትና በጠቅላላው ቢያንስ አንድ ሚልዮን ለሚሆነው ህዝብ መሪ የሆነው ሙሴ የሁሉንም ጉዳይ ይመለከትና ፍርድ ይሰጥ ነበር ይህም በመሆኑ ጥቃቅኑን ጉዳይ እንኳን መመልከት ነበረበት።
መጽሐፍ እንዲህ ይላል” ህዝቡ በሙሴ ፊት ቆመ ከማለዳ ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ”በዚህ ጊዜ ነበር ብልኋ ሚስቱ ስራ እንደሚበዛበት የተገነዘበቸው።አለችውም እውቀት ያላቸውን ስዎች ምረጥ የሺአለቆች የመቶ አለቆች እና የአስር አለቆች ሹም፣ ህዝቡንም ያስተዳድሩ ዘንድ፤ ይህም እቅድ በሙሴ ዘንድ ተቀባይነት አገኘ ።
ከዛን ጊዜ በኋላ ጥቃጥን ጉዳዮች ሙሴ ዘንድ አይደርሱም ነበር።ለህዝቡም ትልቅ በረከት ሆነ ።እንግዲህ ኢትዮጵያዊቷ ሲፖራ ስልጣን በተዋረድ የማከፋፈል ሃሳብን የጠቆመች ስትሆን ይቺ መልኳ ጥቁር (የቀለም ሴት) በመጽሃፍ ቅዱስ ታሪክ እየሱስ ብቻ የሚበልጠውን ነብይ ያገባች ናት። ይህ ታሪክ ብዙ ሽህ ዘመን ያለፈው ቢሆንም ኢትዮጵያውያን ሴቶች ምን ያህል ታማኞች ፣ብልሆችና ሃይማኖታቸውን አክባሪ፣ በውበትም የታደሉና የተመረጡ መሆናቸውን እንድረዳ ያደርጋል።
ከዛም በኋላ ንግስት ሳባ (ማክዳ) ስመ ገናና ግዛቷ የሰፋ የኢትዮጵያ ንግስት ሆና አገሯን ያስጠራች ናት ።ባዲሲቷ ኢትዮጵያም እቴጌ ተዋበች ከሞቀ ቤተመንግስት በመውጣት፣ ባለቤታቸው ደጃዝማች ካሳን በኋላ አጼቴዎድሮስን ተከትለው ከአውደ ውጊያ ቀጠና ሳይለዩ ስንቅ በማደራጀትና ሰራዊቱን በመቀለብ ንጉሰ ነገስቱንም በመንከባከብና በመርዳት በዘመቻ እንደባከኑ ኖረው ለባለቤታቸው አላማና ፍቅር ሲሉ ህይወታቸውን ሰውተዋል።
የአጼ ሚኒሊክ ባለቤትም እቴጌ ጣይቱ የህግና የአስተዳደር ስራ እየሰሩ እያማከሩና እየመሩ የንጉሱን መንግስት ቀጥ አድርገው በመያዝ ሚኒሊክ ሳይሆኑ ንግስቲቷ ናቸው አገሪቷን የሚመሩት እስከመባል የደረሱ ብልህ አሰዋይና ጀግና ሴት እንደነበሩ ታሪካቸውያስረዳል።
የኢትዮጵያ ሴቶች በጦር ሜዳ ውሎ ላይም ተሳታፊ እንደነበሩ እነ ሸዋረገድ ገድሌ በፋሽሽት ኢጣሊያ ጊዜ የፈጸሙት ጀብዱና የጀግንነት ውሎ ምስክር ነው።ዘመናዊ ትምህርት በመቅሰምና በመሰልጠንም የአስተዳደርና የፖለቲካን ስራም አጣጥመው በመስራት፣ የጎላ የስራ ድርሽ ያበረከቱት እነ ዶክተር ስንዱ ገብሩ፣ በሙዚቃና በስፖርቱም እነ ብዙነሽ በቀለና እነ ደራርቱ ቱሉ ምንግዜም ሲታወሱ የሚኖሩ ናቸው።
አሁንም በዚህ የሚሊኒየም ዘመን ብርቱካን ሚደቅሳ የኢትዮጵያን ህዝብ ከግፍ ስርአት ለማዳን ከተነሱ ሃይሎች ጋር በማበር ባሳየችው ቆራጥነት ለከፍተኛ ስቃይ በተደጋጋሚ ብትጋለጥም ከኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ምንግዜም ተቀምጦ የሚቀር አኩሪ ተግባር የፈጸመች ሴት ናት።
ብርቱካን ሚደቅሳ የህግ ባለሙያ በመሆን በዳኝነት ወምበር ተቀምጣ በነበረችበት ወቅት አለአንዳች ፍርሃትና ማወላወል የህግን የበላይነት ያስመሰከረች ከመሆኗም በላይ ለስው ልጅ እኩልነት ፣ለፍትህና ለዲሞክራሲ መብት መከበር፣ በቆራጥነት በመቆም የአላማ ጽናትዋን ያስመሰከርች ናት።
ባለፈው ሰአት የደረሰባትን እስራትና እንግልት የተመለከተ ሁሉ ምን ያህል በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የፍትህ መጓደል፣ ግፍና በደል እየተፈጸመበት እንዳለ የአለም ህብረተሰብ በግልጽ እንዲረዳ አስችላለች ። ከተጣለችበት የመከራ ጉሮኖ ልትወጣ መቻሏም እንደፍርሃትና መንበርከክ የሚቆጠር ሳይሆን ብልህነቷን የሚአመለክት ነው።
የዚህ ጽሁፍ ዋና አላማ ከመጽሃፍ ቅዱሷ ሲፖራ እስከ ክፍለ ዘመኗ ብርቱካን ሚደቅሳ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ጠንካሮች፣ አስተዋዮችና ብልሆች፣ የአላማ ጽናት ያላቸውና ለተነሱበት ተግባር አለፍርሃት የቆሙ መሆናቸውን ለመግለጽ ሲሆን ከጥንት ጀምሮ አኩሪ የታሪክ አሻራ እየተዉ እንደመጡም ለመግለጽ ነው።
በሌላ በኩልም ከላይ የጠቀስኳቸው ታዋቂ ሴቶችን በምሳሌነት አነሳኋቸው እንጂ ብዙ እናቶችና እህቶቻችን በተለያየ ዘመን ለሃገርና ለወገናቸው አስመስጋኝ ተግባር እየፈጸሙ ያለፉና ያሉም እንዳሉ አይዘነጋም።