ውሸት፣ ማስመሰል፣ ማስፈራራትና ጭቆና የኢህአዴግ ዋነኛ ሥልጣን ላይ የመቆያ ስልቶች

ከኢትዮጲያ ፌዴራላዊ አንድነት መድረክ(መድረክ) የተሰጠ መግለጫ

ኢትዮጵያ ሀገራችን ረጅም የህላዌ ዘመንና የመንግሥትነት ታሪክ ካላቸው ጥቂት አገሮች አንዷ በመሆን ትታወቃለች፡፡ በሌላ ወገን መንግሥታት ወይንም ገዢዎች በህዝብ ላይ አሠቃቂ የጭቆናና የአፈና ሥርዓት በመዘርጋት ሕዝቡ ሁለንተናዊ ክብሩን ተገፎ የሚኖርባት አገር በመሆንም ትታወቃለች፡፡ ጭቆናውን እጅግ የከፋ የሚያደርገው ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ የነፃነቱ፣ የሀገሩ እና የመብቱ ባለቤት ለመሆን ካደረገው ረጅምና እልህ አስጨራሽ ትግል በኋላ ከእለት ወደ እለት እየከፋ በሚሄድ የጭቆና ሥርዓት ውስጥ እየሟቀቀ መገኘቱ ነው፡፡ በተለይም በአለንበት በ21ኛው ክፍለ ዘመን የነፃነትና የእኩልነት ጉዳይ የሁሉም ሰብአዊ መብቶች፣ ልማት ሁሉን አቀፍ እሴቶች ማዕከላዊ አጀንዳ በሆኑበት ሁኔታ ኢትዮጵያ ግን አሁን በአለም ላይ ከሚገኙ ለሰበአዊ ክብር፣ ለሀገር ሉዓላዊነትና እድገት ቁብ ከማይሰጡ ጥቂት አምባገነን መንግሥታት በአንደኛው መዳፍ ውስጥ ትገኛለች፡፡

የአለፉት 2ዐ አመታት መጀመሪያ ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በአንድ በኩል በደርግ አምባገነናዊ መንግሥት ከደረሰበት ሠፊ አፈና እፎይ ለማለት ከፍተኛ ጉጉት ያደረበት፣ በሌላ ወገን ደግሞ የኢህአዴግን የማያባራ የማማለያ ፕሮፓጋንዳ እውነት ይሆናል ብሎ በመገመት የነፃነት ንጋት በኢትዮጵያ ምድር ላይ ሲበራ ለማየትና የአለፉትን ክፉ ዓመታት ለመርሳት በዝግጅት ላይ ነበር፡፡ ይሁን እንጅ የሆነው ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው፡፡ ያለፉት ክፉ የጭቆና ዓመታት በሌላ የከፋ ጭቆናና ክፉ ዓመታት ተተኪ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለእፎይታ የዘጋጀውን ጎኑን ለትግል መልሶ ያዘጋጀባቸው አመታት ነበሩ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአለፉት 2ዐ ዓመታት አስፈላጊውን ሁሉ መስዋእትነት በመክፈል የነፃነቱ፣ የመብቱ እና የሀገሩ ባለቤት ለመሆን የሚያደርገውን የነፃነት ትግል ቀጥሏል፡፡

ኢህአዴግ ከሌሎች የኢትዮጵያን ሕዝብ ከጨቆኑ ሥርዓቶች ከሚለይባቸው ምክንያቶች አንዱ ማስመሰልን የተካነና ለዝንተ ዓለም ቢዋሽ ይሉኝታን ወይንም ሀፍረትን ያልፈጠረበት ስብሰብ መሆኑ ነው፡፡ ኢህአዴግ ዴሞክራሲን ሰብኮ ሶሻሊዝምን የሚያሰፍን፣ ነፃነትን ሰብኮ ጭቆናን የሚያጎናጽፍ፣ ልማትን በሃሳብ እየሳለ ድህነትን የሚያመርትና ስለሙስና መጥፋት እየዘመረ ከእግር እስከ አንገቱ ሙስና ውስጥ የተዘፈቀ መሆኑ ነው፡፡ ይኸንን መሠል አካሄዱ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የዓለም አቀፍ ማህበረሰብም ግራ ያጋባ ነበር፡፡ ነገር ግን ከ1997 ዓመተ ምህረት ምርጫ በኋላ እኩይ ተግባራቱን በቃላት ናዳ መሸፈን በማይችልበት ደረጃ ተጋልጧል፡፡ በተለይም በ2ዐዐ2 ዓም አካሄድኩት በሚለው የምርጫ ተውኔት ደግሞ ከመቸውም ጊዜ በከፋ ሁኔታ እርቃኑን የቀረበትና ኢህአዴግ የሚመራው መንግሥት የኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ የአለማቀፉ ማህበረሰብ ለመንግሥትነት የሚሰጡትን ክብር ሊያገኝ ያልቻ በአፈ-ሙዝ አስገዳጅነት የተጫነ ኃይል መሆኑን አረጋግጧል፡፡

ይኸን በመሠለ ሁኔታ እርቃኑን ቢቀርም የቅጥፈት አባዜው ግን በእጅጉ እንደተጠናወተው ይገኛል፡፡ ኢህአዴግ በኢኮኖሚ አደግን ተመነደግን እያለ በሚያዜምበት ሁኔታ የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን በየጓዳው የመኖር ያለመኖር ጭንቅ ውስጥ ወድቆ ይገኛል፡፡ ኢህአዴግ በኢኮኖሚ አድገናል በሚል ጉም ለማዘገን ሲጥር አንቱ የተባሉ አለማቀፍ የምርምር ተቋማት ግኝት የሚያወጡት መረጃ ግን ፈጽሞ የተለየ ነው፡፡ ኢህአዴግ ኢኮኖሚው አደገ ሲል የሚያነሳው መከራከሪያ የበጀት መጨመርን ነው፡፡ ጨመረ የሚባለው በጀትም ግን ከኢኮኖሚው ተረፈ- ምርት ከተገኘ እድገት ሳይሆን ከእርዳታ እና ብድር ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ የሀገሪቱን የገቢ እና ወጭ ንግድ ሁኔታን ስናይ በእጅጉ ያልተመጣጠነና የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የሀገር ኢኮኖሚ የሚባልበት ደረጃ ላይ የማይገኝ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ አገሪቷ በአለፈው የፈረንጆች ዓመት አቅሟን አሟጣ ልታገኘው የቻለችው የውጭ ምንዛሬ መጠን ከ1.4 ቢሊዮን ያልዘለለ ሆኖ እያለ፣ እንዲሁም ይኸኑ ተከትሎ የብር አቅም በአንድ ምሽት ወደ ወረቀትነት እየተቀየረ ባለበት፣ ግሽበቱ እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ በደረሰበትና በዚህም ሳቢያ የኢትዮጵያ ሕዝብ በኢኮኖሚ ድቀት በከፍተኛ ሁኔታ በተደቆሰበት ሁኔታ ኢኮኖሚው ሰማያትን አልፎ መስፈንጠረን ኢህአዴግ በተቆጣጠራቸው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ የኢትዮጵያ ሬዲዬ፣ ፍትህን አለማወቁን በሚያስመሰክርበት ፋና ሬዲዮና በአዲስ መዘመን ጋዜጣ እያደነቆረን ይገኛል፡፡ ይህ የሚያሳየው ኢህአዴግ ተደራጅቶ አገር መምራትና ወደ ተሻለ ጎዳና ማቅናት ቢያቅተው ተደራጅቶ መዋሸትን አንደ ወሳኝ የህዝቡን ኑሮ ህይወት ያለወጠ ከተውኔት አያልፍም፡፡ እድሜ ማራዘሚያ መድሀኒት አየተጠቀመበት መሆኑን ነው፡፡ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ሕዝብ ከሰባ ከመቶ በላዩ የንፁህ መጠን ውሀ እንኳን መጠቀም በማይችልበት ሁኔታ ይኸው የኢኮኖሚ መመንደግ ልፈፋው ቀጥሏል፡፡

በፖለቲካው ጎራም ቢሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ እጣ ፋንታው ከአብራኩ በወጡ አምባገነን ገዢዎች መረገጥ እስኪ መስል ድረስ አሁንም ለ2ዐ ዓመታት የኢትዮጵያ ሕዝብ በማያባራ የጭቆና ማዕበል ውስጥ እያለፈ ይገኛል፡፡ አሁን ደግሞ ያለፉት ዓመታትን የጭቆናና የድህነት መዝገብ በቅጡ ሳያወራርድ በቀጣዩቹ ዓመታት ይመዘገባል ስለሚለው የላም አለኝ በሰማይ እቅድ ወደ ተግባር የተለወጠ ያህል ቀን ከሌት የኢትዮጵያን ሕዝብ መደበቂያ እስኪያጣ ድረስ የፕሮፓጋንዳ እሩምታ እያወረደበት ይገኛል፡፡ ኢህአዴግ በመሪዎቹ አማካኝነት ይሰራው የነበረው ተውኔት በድራማ ብዛት መሬት ላይ ያለውን ላቅን የመለወጥ እንደማይቻል ገሀድ ወጥቷል፡፡ ኪነት ለአቢዬት በሚል መፈክር ደርግ የሀገሪቱን የኪነት ባለሙያዎች ለፖለቲካ መጠቀሚያ ያደረገውን ፈሊጥ በመከተል ኢህአዴግ ደግሞ አርቲስቱም አትሌቱም ለአቢዬታዊ ዴሞክራሲ አሁን ደግሞ በአዲስ ዓመት ዋዜማ እንዳየነው የኢትዮጵያን ሕዝብ ለማሳመን በሀገሪቷ ውስጥ አሉ የተባሉ ተዋናኞችን በመቅጠር ገና በጥዋት የጀመረውን ተውኔቱን ቀጥሏል፡፡ ኢህአዴግ ይኸን በመሠለው የአፈናና የማስመሰል ጎዳና ተጉዞ የት እንደደረሰ የ2ዐዐ2 ዓም ምርጫ ተብዮ ያንም ተከትሎ የመንግሥት ምስረታ ተብሎ እየተተወነ ባለው አሠልች፣ አሳፋሪ እና አይን ያወጣ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የሚደረግ መራራ ቀልድ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንገት ያስደፋ ለዓለም የነፃነትና የዴሞክራሲ ታሪክም በጥቁር መዝገብ ውስጥ ተከትበ የሚያልፍ እውነት ሆኖአል፡፡

ይኸን በመሠለ ሁኔታ ያለ ኢትዮጵያ ሕዝብ ይሁንታ ሥልጣን ላይ አይኑን በመጨው ታጥቦ የተፈናጠጠው ኢህአዴግ የአፈና ነጋሪቱን ከ97 ዓመተ ምህረት ምርጫ በኋላ እንዳደረገው አሁንም ማልዶ መጎሠም ጀምሯል፡፡ በ1997 ዓመተ ምህረት ምርጫ ወቅት የሚጠበቅባቸውን ሙያዊ እና ተቋማዊ ሚና የተወጡትን እንደ የሲቪል ማህበረሰብ እና ነፃ ፕሬስ ደብዛቸውን በማጥፋት የአፈና መዋቅሩን ለ2ዐዐ2 ዓም የምርጫ ተውኔት እንደዘረጋ በፀፀት እናስታውሳለን፡፡ አሁን ደግሞ ግባተ- መሪቱን ያፋጠነውን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ከዚህም በላይ ዝቅ አድርጎ ለመቅበርና ዝንተ ዓለም የኢትዮጵያን ህዝብ ረግጦ ለመግዛት በመጣደፍ ላይ ይገኛል፡፡

የአሁኑ የአፈና የክተት እወጃ አገራችን ውስጥ በሚገኙ ሀቀኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ መሆኑን በኢህአዴግ የአዲስ ራእይ መጽሔት ላይ በማያሻማ መልኩ ተቀምጧል፡፡ የኢህአዴግን ልእልና በሚያቀነቅኑ በስም የህዝብ፤ በተግባር ግን የኢህአዴግ አንጡራ ንብረቶች በሆኑት የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮም ጭምርም ነው፡፡ ከላይ ከፍ ሲል እንደተገለፀው በሁሉም መስፈርቶች አንፃር የኢትዮጵያን ሕዝብ ህገ-መንግሥታዊ እና ሰብአዊ መብቶች ሁሉ በመጣስ፣ በተደራጀ መልኩ ከማስመሰል አልፎ የህዝብን ድምጽ በጠርናፊና ተጠርናፊ ስልቱ በመንጠቅ የሚታወቀው ኢህአዴግ ራሱን የህገ መንግሥት ጠበቃ ሌሎችን ደግሞ ፀረ ህገ መንግሥት በማለት ሲፈርጅ እንደተለመደው ቅንጣት ሀፍረት አልገደበውም፡፡ በግልጽ ለማስቀመጥ ኢህአዴግ ሕገ-መንግሥቱን የሚያከብሩና የማያከብሩ ብሎ ለመለየት ያስቀመጠው ዋነኛው መስፈርት እሱ የሚያዜማቸውን ዜማዎች መልሰው የሚያስተጋቡ ሕገ መንግሥቱን የሚያከብሩ ተብለው ሲመደቡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያላቸውን ራእይ አንጠረው በማውጣት ከኢህአዴግ የተሻለ የሚሉትን አማራጭ ይዘው ሕዝብን ከጎናቸው ለማሰለፍ ለተፈፃሚነቱ የታገሉ በህዝብም ዘንድ ከበሬታ ያገኙትን ደግሞ ፀረ-ህገ መንግሥት በማለት ይፈርጃቸዋል፡፡ በዚህ በኢህአዴግ ንድፈ ሃሳብ መሠረት ትልቁ ጭንቅ ኢህአዴግ በየሰከንዱ ስለሚጥሰው ህገ መንግሥት አይደለም፡፡ ትልቁ ጭንቅ ተጠናክረው እና የህዝብን ዓመኔታ ይዘው የሚወጡ ተቃዋሚዎች ካሉ ኢህአዴግን ከሞቀው የሥልጣን ማማው እንዳይወርድ ነው፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ የሚያወጣቸው መግለጫዎችና ይኸኑ መጽሔት ተብዬ እንደተለመደው የኢትዮጵያን ሕዝብ ለማወናበጃ ሀቀኛ ተቃዋሚዎችን ደግሞ ከትግል ሜዳው ገፍትሮ ለማስወጣት የታሰበ እና ለዚሁ ዓላማም ከየትም የተቃረመ ጥራዝ ነጠቅ የፕሮፓጋንዳ ነው፡፡ በዚሁ በኢህአዴግ ግርድፍ ሀተታ መሠረት ኢህአዴግ ፀረ-ሕገ መንግሥት ሲል ፀረ-ኢህአዴግ ማለቱ ሲሆን፣ በኢህአዴግ አምባገነናዊ ስሌት ደግሞ ህገ መንግሥት ሲል ኢህአዴግ መሆኑን በማያሻማ መልክ አስቀምጦታል፡፡ ኢህአዴግ እነዚህ ፓርቲዎች ፀረ-ህገመንግሥት ከሆኑ እንዴት እንደታገሳቸው ቢያስረዳ ይቀለው ነበር፡፡ አሊያም ፈቃዳቸውን አስመልሶ ሌላ የሚታወቅበትን የቆረጣ ተግባሩን ለምን አልፈፀመም ምንአለ ፀረ-ህገመንግሥት ሲሆን ዝም ካለ ህገ መንግሥቱግ ባለማስጠበቁም ሊጠየቅ ይገባዋል፡፡

እንዲሁም ኢህአዴግ በዚሁ ጥራዝ ነጠቅ ትንቀናው ከተተካኪ አመራር አልፎ ስለተተካኪ ፓርቲዎችም ሊነግረን እየዳዳው ነው፡፡ ከ2ዐ ዓመታት በኋላ የደርግን ብሔራዊ ሸንጎ በኢትዮጵያ ምድረ ድጋሚ እንዲፈጠር በማድረግ ኢህአዴግ እንደተሳካለት የዚህ ሰሞኑ የመንግሥት ምሥረታ ተብዬ ፌዝ ገሀድ አውጥቶታል፡፡ በዚሁ ሂደት ኢህአዴግም በተግባር የኢሠፓ አልጋ ወራሽነቱን አስመስክሮ ሀገሪቷን ወደ አንድ ፓርቲ ፈላጭ ቆራጭነት ዘመን ይዟት ተሟል፡፡ በአመራር ደረጃም መተካካት እየተባለ በተደጋጋሚ ሲነገረን የባጀው በተግባር ግን ተራ በኢትዮጵያ ገዢዎች ዘንድ የተለመደው የሹም ሽር ከመሆኑም በላይ በመንበረ-ሥልጣኑ ላይ የተቆናጠጡትን የሥልጣን መሠረት ለማስፋትና ብሎም ቀጣይነቱን በአስተማማኝ መሠረት ላይ ለማረጋገጥ የተሰራ ቀመር ነው፡፡ ከዚህ የዘለለ አንዳች የዴሞክራሲ ሽታ የለውም የጉልቻ መለዋወጥ ከመሆን አልዘለለም፡፡ በደርግ ጊዜም የአንድ ፓርቲ ሥርዓት ብቻ ሳይሆን የአንድ ግለሠብ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ እንደነበር ለኢትዮጵያ ሕዝብ ማስረዳት ለቀባሪው ማርዳት ነው የሚሆነው፡፡

ኢህአዴግ የፓርቲዎች መተካካት በሚለው የቃርሚያ ፈሊጡም ከዚህ የዘለለ ሕልም የለውም፡፡ ኢህአዴግ ስለተተካኪ ፓርቲዎች ሲያወሳ የሚነግረን እርሱ ያነገበውን የአረጀ የአፈጀ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ የአፈና ሥርዓት ከኢህአዴግ ባልተለየ ሁኔታ የተጠመቁና ኢህአዴግ በጣቶቹ ቀርፆ የሚፈጥራቸው በሌላ ስም የሚጠሩ ኢህአዴጎች መሆናቸውን ያለማፈር ነግሮናል፡፡ ይህ በገሀድ የሚያሳየን አሁንም ኢህአዴግ ትርጉም አልባ ሀረጎችን በመምዘዝ የኢትዮጵያን ሕዝብ ግራ ለማጋባት ብሎ ለማዘናጋት ማቀዱን ነው፡፡ ከዚህ ውጭ በሀሳብም ሆነ በተግባር ኢህአዴግ ስለተተካኪ ፓርቲዎች የሚለፍፈውም ሆነ ስለተተኪ አመራር አብዝቶ ሲደሰኩር የነበረው የቀን ቅዥት መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ዋናው ኢህአዴግ እያስተላለፈ ያለው ጭብጥ የሠራተኛ ማህበራትን፣ የሲቪል ማህበረሰቦችን፣ የነፃ ፕሬስንና ሌሎችንም ህገ-መንግሥታዊ ተቋማት በራሱ አምሳል እንደተካቸው ሁሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በእኔ መልክና ቅርጽ ካልፈጠርኳችሁ ህልውና አይኖችሁም የሚል ነው፡፡

ሌላው ኢህአዴግ የግራ ማጋባትና የማስመሠል ዘመቻውን እውን ያደርጉልኛል ብሎ ከመዘዛቸው ሀረጎች አንዱ ‹አውራ ፓርቲ› የሚለው ነው ኢህአዴግ በራእይ መጽሔቱ ደጋግሞ ከጠቀሳቸው አገሮች መካከል ስዊድን፣ ጃፓን ጀርመንና አሜሪካ ይገኙባቸዋል፡፡ በተግባር ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዳይደራጁ ብሎም እንዳይኖሩ፣ ከተደራጁም እሱ በሚፈልገው እና በሚፈቅደው ልክ ብቻ ካልሆነ ህልውና እንዲኖራቸው እንደማይፈልግ እየነገረን ነው፡፡ በገሀድም ከኢህአዴግ ፈላጎት ውጭ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ከህገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱ ውጭ ናቸው ሲል ህገ- መንግሥትም ማለት ኢህአዴግ መሆኑን በማያሻማ መልኩ እየነገረን ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ሕዝብ እምነት፣ አስተሳሰብ እና ፍላጎት ውጭ እንዲሁም በዓለማቀፍ ማህበረሰብ እንግዳ በሆነ መልኩ እና መጠን ኢህአዴግም ራሱን በተደራጀ መንግድ ሕዝብ የሚያፍን፣ እራሱን ያወጣውን ህገ-መንግሥት ደጋግሞ በመጣስ እርባና ቢስ ያደረገና ምንም አይነት የህግ እና የሞራል መሠረት የሌለው ጨቋኝ ስብስብ ሆኖ ሳለ ከእነዚህ ዴሞክራሲያዊ አገሮችና ዴሞክራሲያዊ ፓርቲዎቻቸው ጋር እራሱን ለማሰለፍ መድከሙ ለምን ይሆን? ያው የተካነበትን የተውኔት ትይንት አሁንም ያዋጣኛል ብሎ አስባ ከሆነ አሁንም እንደልማዱ ተሳስቷል፡፡

ያለአቅሙ፣ ያለ ፍላጎቱ፣ ያለ እምነቱ እና ያለ ተፈጥሮው ከዴሞክራሲያዊ ፓርቲዎች እና አገሮች ጋር በስማበለው ራሱን ለማቆራኘት ለምን ፈለገ፤ ቢጤዎቹን እናማይነማር ፣ ኩባ፣ ኤርተራ እና ቻይናን ቢጠቅስ? በተግባር እንደሚያደርገው ስለ አነርሱ የዴሞክራሲ እና የሰብአዊ መብት አያያዝ ቢነግረን? የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ከስም ባለፈ ሞቶ በተቀበረበት፣ የዴሞክራሲ ምሶሶዎች ተሰባብረው ኢህአዴግ ወደ ፈለገው የሚያዘማቸው ሰንበሌጦች በሆኑበት ሁኔታ፣ የኢህአዴግ የ2ዐ ዓመት የአፈና፣ የድህነት ቅፍቀፋና ሰብአዊ ክብርን የማኮሰስ ጉዞው በሁሉም ዓለማቀፍ ገለልተኛ ተቋማትና ዴሞክራሲያዊ አገሮች ዘንድ የተወገዘና አይንህን ላፈር የተባለ ፓርቲ፣ እንዲሁም ገና ከጥዋት ጀምሮ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ሆድና ጀርባ ሆኖ የባጀ ፓርቲ በየትኛው ተግባሩ እና ሚዛናዊ መለኪያ ነው አውራ ፓርቲ ሊባል የሚችለው? ለመሆኑ በቅጡ ህግ ተግባር ላይ የሚውልበት ሥርዓት ቢኖር ኢህአዴግ እንደፓርቲስ መመዝገብ የሚችል አካል ነውን? ታሪኩና ሪኮርዶቹ የሚያሳዩት በተግባርም በአስተሳሰብም በየትኛውም ሚዛን ሲመዘን እጅግ ያነሰ እና የኮሰሰ ፓርቲ መሆኑን ነው፡፡ በኢህአዴግ ዘመን ክብሩን ያልተገፈፈ፣ ትርጉሙን እንዲስት ያልተደረገ ምን ነገር አለ? የኢህአዴግ የአውራ ፓርቲነት ተረት ተረት፡፡ የቃላት ትርጉማቸውን እንዲያጡ ከማድረግ ውጭ ሌላ ትርጉም የለውም

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሁሉም መስኮች ነፃነቱን በተገፈፈበት ሁኔታ ልማት ሊመጣ አይችልም፡፡ ልማት፣ ዴሞክራሲና ፍትሕ ከእውነተኛ ነፃነት ጋር በእጅጉ የተዛመዱ ጉዳዬች ናቸው፡፡ ነፃነት በሌለበት አገር እነዚህን ነገሮች ሁሉ አሰፈንኩ ማለት እንደተለመደው ከተራ ፌዝ አያልፍም፡፡ ነፃነት በሌለበት ልማት እውነ አይሆንም፡፡ አለ በቢባልም ዘለቄታ አይኖረውም፡፡ የኢህአዴግ መሪዎች በቅጡ የማይረዷቸውን ቃላት ለሕዝብ በመወርወር እስካሁንም ድህነትን እንጂ ለማትን ሊያመጡ አልቻሉም፡፡ አሁንም ሕዝብን ለማማላል ያስችለናል ብለው በግዴለሽነት የሚወረውሯው ቃት የኢህአዴግን ውሎ አድሮ ውድቀት አፍቃሪ ከማድረግ የዘለለ ፋይዳ የላቸውም፡፡ በኢትዮጵያ ድህነትን መዋጋት የሚቻለው የሕዝቡ ሁለንተናዊ ነፃነቱ ሲጠበቅ ነው፡፡ ከዚያ ውጭ በማስረጃ እና በተግባር ያልተደገፈ እቅድና አተገባበሩ የሠማይና የመሬት ያህል በተራራቀ ኢኮኖሚ ታች ያለው የግብርና ምርት ሳያድግና የህዝቡ የኑሮ ሁኔታ ከድጡ ወደ ማጡ ከእለት ወደ እለት በሚወርድበት ሁኔታ በምን አየነት ተጨባጭ የኢኮኖሚ ስለት እድገት እንደሚመዘገብ በተምራዊ ተውኔቱ ኢህአዴግ ብቻ ነው ሊያስረዳ የሚችለው፡