“ነብይ በአገሩ አይከበርም” … እዉነት!?
ማስተዋል አዳነ
ጊዜዉ በአገራችን ክረምት ሊገባ ጥቂት ጊዜያት የቀሩበት ወቅት ነበር፤ የአሁኑ ክረምት። ወደአገር ቤት ለመሄድ የወሰንኩት ቤተሰብ፣ ጓደኛና ዘመድ ለመጠየቅና በአጠቃላይ የአገራችን የኑሮ ሁኔታ በጣም ስለናፈቀኝ፤ ይህንን ደግሞ ከተወሰነ አመት የትምህርት ቆይታ በኋላ ተመልሼ ማየት አለብኝ የሚል ዉሳኔ ላይ ስለደረስኩ ነበር። ተማሪ ስለሆንኩና የእረፍት ጊዜዬንም በዚሁ አጋጣሚዉን መጠቀሙ ጥሩ አማራጭ ስለሆነ ከፍራንክፈርት ወደአዲስ አበባ ትኬት ቆርጬ ግንቦት መጨረሻ ላይ ወደአገር ቤት ለመሄድ ተሰናዳሁ። የበረራ ቀን ሰኞ ነበር። የአዉሮፕላኑ አስተናጋጆች በጥሩ ሁኔታ አስተናግደዉን ወደዉስጥ ገባን። እንደጀርመን ሰአት አቆጣጠር ከቀኑ 11 30 አካባቢ ይሆናል። ሉፍታንዛ በጣም የሚደላ አየር መንገድ ነዉ። ከመሬት ዉስጥ ተተኩሶ ወደሰማይ ቀርቦ በጉም ዉስጥ ይከንፍ ጀመር። አዉሮፓን አቋርጠን እስከምንወጣ ድረስ በጉም የተዥጎረጎረዉ አረንጓዴ ለምለም መልክአምድር አልፎ አልፎ በደመና መካከል በአዉሮፕላኑ መስኮት ይታያል። አንዳንዴም አነስተኛ ሃይቆች በየአካባቢዉ ይታያሉ። ምናልባትም ሰዉ ሰራሽ ሃይቆች ይሆኑ? አዎ ይመስለኛል። አገራችንስ መቼ ይሆን እንዲህ አይነት ሰዉ ሰራሽ ሃይቆችን ገንብታ ወደጎረቤት አገሮች ለም አፈር እየጠረገ የሚወስደዉን ዉሃ ገድባ ለረሷ ፍጆታ በማዋል የእለት ጉርሷን የምታሟላዉ? እያልኩ ራሴን መጠየቅ ያዝኩ።
በጉዞ ወቅትም ማንም ኢትዮጵያዊ በቅንነት የሚያስበዉ ሃሳብ በአእምሮዬ ዉስጥ ይመላለሳል፤ ሁሉም ተባብሮ ቢሰራ፣ ዉጭ ያለዉ ዳያስፖራ ኢትዮጵያዊ ገንዘቡን፣ እዉቀቱንና ልምዱን ይዞ በመምጣት እንደየእዉቀቱና ችሎታዉ ቢሰማራና አገር ዉስጥ ካለዉ ሃይል ጋር ቢቀናጅ ከድህነት የማንወጣበት ምንም ምክንያት የለም በማለት በእርግጠኝነት አሰብኩ። ግን ግን እኮ ይህም መንግስት በተደጋጋሚ ጥሪ እያደረገ አይደል? ጥረት ይሏል ይህ ነዉ። ይሁን እንጂ ለምንስ እስካሁን ሳይሳካ ቀረ? ዉድ የሆነዉ መሬታችንስ ለምን ለዉጭ አገር ባለሃብቶች ወይም የመንግስት ባለስልጣናት ሽርካዎች በዘፈቀደ እንደቅርጫ ስጋ ይከፋፈላል እየተባለ ይወራል? የችግሩን ምንጭስ ምን ይሆን እያልኩ እያሰላሰልኩ የተዘበራረቀ ሃሳብ አሁንም አሁንም በአእምሮዬ ይጉላላል። በዋናነት ግን መንግስት ሁኔታዎችን ሳያስተካክል የተናጠል እናልማ ጥሪ ማቅረቡ ተቀባይነት የሌለዉ ፍሬ አልባ ሃሳብ እንደሆነ ገባኝ። የሚገርመዉ እኮ ነጻነት በሌለበት አገር፤ መንግስት ከህግ አግባብ ዉጪ እንደፈለገ እርምጃ በሚወስድበት አገር ዜጎች ተሸማቀዉ በሚኖሩበት አገር፤ ለኢትዮጵያዉያን ዳያስፖራ “አገር እናልማ” ጥሪ ምንድን ነዉ? ምንድነዉ የሚለማዉስ? መንገድና ህንጻ ብቻ ነዉ? ተቃዋሚዎችን በሆነ ባልሆነ ሰበብ እየፈጠረ አንዳንዶችን የፈንጅ ወረዳ የረገጡ፣ ሌሎችን ደግሞ የልማት ጸር፣ የቀሩትን ደግሞ የጥፋት ሃይሎች የሚል ታርጋ በመለጠፍ ራስ ራሳቸዉን በመምታት ከትግል ሜዳ ዘወር የሚያደርግ መንግስት እንዴት ነዉ ለሰዉ ልጅ ሁለንተናዊ እድገት፣ ሰላምና ብልጽግና አስፈላጊ ምሰሶ የሆኑትን እሴቶችን ሁሉ በመተዉ በመንገድና በህንጻ ልማት ላይ ብቻ እናተኩር በማለት ለዳያስፖራ ኢትዮጵያዉያን ጥሪ እያስተላለፈ ያለዉ? ገንዘብና እድገት መንግስት ከዜጎች ፈልጎ፤ ግን ደግሞ ስለነጻነትና ዲሞክራሲ ጥያቄ አታንሱ በማለት ነፍጎ ኢትዮጵያዊያን በሁሉም አቅጣጫ እንዳይሳተፉ መከልከል ምን ማለት ነዉ? ምን አይነት እድገትስ ነዉ የሚታሰበዉ? እድገት ማለት ሁለንተናዊ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እሴቶች በአንድ ላይ ተጣምረዉ የሚመጣ ለዉጥ እንጂ የአንድ የኢኮኖሚ እድገት ብቻ አለመሆኑን ብዙ ምሁራን ስለተነተኑት እዚህ ማብራራት አስፈላጊ አይመስለኝም። የገዢዉ ፓርቲ አባላትና ተቀጽላዎቹ እንደፈለጉ የአገሪቱን ገንዘብና ሃብት በሚዘርፉበት አገር፣ ህግና ስርአት የሆኑት በራሱ በህወሃት ኢህአዴግ ግንባር የተጻፉዉ ህገመንግስትና በተዋረድ ያሉ የአገሪቱ ህጎች ተሸርሽረዉ የገዢዉ ፓርቲ አባላት ብቻ ህግ በሆኑበት አገር፣ መንግስት አላማዉን የሚያስፈጽሙለት ካድሬዎች በየቤተክርስቲያናቱና በየመስጊዱ እንኳን ሳይቀር ባሰማራበት አገር ማን ማንን አምኖ ዉጭ አገር ስንት ጥሮ ግሮ ያፈራዉን ገንዘብ ለቀን ጅብ ይሰጣል? በብሄራዊ ባንክ ሳይቀር ባሌስትራ ወርቅ አስመስለዉ የሚያስቀምጡት ከህወሃት ኢህአዴግ የተጠጉ ባለጊዜዎች አይደሉም እንዴ? በአረመኔነቱ ስሙ በተደጋጋሚ የሚነሳዉ ደርግስ እንዲህ አይነት ድርጊት ፈጽሞ ይሆን? ይህንን የመሳሰሉ ሃሳቦች በአዕምሮዬ ይጉላላሉ።
አዉሮፕላኑም በረራዉን ቀጥሏል፤ ሜዲትራኒያን ባህርን አቋርጦ ወደ አፍሪካ አህጉር እየገባ ነዉ፤። እኛ ያልታደልን ሆነን ነዉ እንጂ አገራችን ኢትዮጵያ ከተወሰኑ የአፍሪካ አገሮች የተሻለ አየር ንብረት ያላት አገር ትመሰለኛለች። ይህንንም በደንብ የተገነዘብኩት የግብጽንና የሱዳንን የአየር ክልል ዉስጥ ሰንገባ ነዉ። በተለይም በግብጽ ደረቅ ምድረበዳ መሬት የሚበዛ መሆኑን በአየር ላይ ሆኖ ያየ ማንም ሰዉ በደንብ ይረዳል። በእዉነት ይህንን አገር ይዘዉ ከእኛ በእጥፍ በተሻለ የኑሮ ደረጃ ያሉ ለመሆናቸዉ እጅግ በጣም ይገርማል። ሆኖም አዉሮፕላኑ ወደአዲስአበባ ጉዞዉን ባቀና ቁጥር አልፎ አልፎ የተፈጥሮ ይሁን ሰዉ ሰራሽ ደኖች አለፍ አለፍ ብለዉ መታየታቸዉ አልቀረም። ከፊት ለፊቴ ያለዉን የአዉሮፕላኑ ርቀት አመልካች ቴሌቪዥን ስክሪን ሳይ ሱዳንን አልፈን እንዲያዉም ወደአገራችን ድንበር እየተጠጋን መሆናችንን አወቅሁ። ለእርሻ እጅግ ምቹ የሆነ ሰፋፊ መሬት ተንጣሎ ይታያል። የቴሌቪዥን ስከሪኑን ቀና ብዬ አየሁ። ስክሪኑ ኢትዮጵያ ዉስጥ እየገባን መሆኑን ያመላክታል። በመሆኑ ይህንን ለም የእርሻ መሬት የኢትዮጵያ መንግስት ለሱዳን በስምምነታቸዉ መሰረት ቆርሶ የሰጠዉ ገጸበረከት መሆን አለበት ብዬ አሰብኩ። መቼስ ይህ መንግስት በገዛ ዜጎቹ ላይ ምን ያክል አረመኔያዊ ተግባር የሚፈጽም መሆኑን ግፉን የቀመሰዉ ኢትዮጵያዊ ያዉቀዋል። በተለያየ ጊዜ በህወሃት ኢህአዴግ ድጋፍ በሱዳን የጸጥታ ሃይሎች ተወስደዉ የተገረፉና ደብዛቸዉ የጠፉ ሰዎችን ቤት ይቁጠራቸዉ። ዳያስፖራ ኢትዮጵያዊያን ባለመሰልቸት ኢትዮጵያ አንድነቷና ዳር ድንበሯ ተከብሮ ለዘላለም እንድትኖር ብርቱ ጥረት አድርገዋል፤ አሁንም እያደረጉ ይገኛሉ። እኛስ ይህንን የህወሃት ኢህአዴግ መሬት ቆርሶ የመስጠት ሴራ በዳያስፖራ ኢትዮጵያዊያን የተቀናጀ የማጋለጥ ስራ አወቅነዉ እንጂ ማን ይነግረን ነበር? ምስጋና ለአሜሪካ፣ ለጀርመንና ለተቃዋሚ ሬዲዮ ጣቢያዎችና ድህረገጾች! የድንበሩን መቆረስ ጉዳይ እነሱ አይደሉም እንዴ በአለም ዙሪያ ለሚኖረዉ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ቃለመጠይቅ በማድረግና የዜና መጽሄት በማዘጋጀት ያሰራጩት? ይህ ለም መሬት ለሱዳን መሰጠት በመቃወም ሰላማዊ ሰልፎች በማቀናበርና ጋዜጣዊ መግለጫዎች በመስጠት በዉጭ ያለዉ ኢትዮጵያዊ የከፈለዉን መስዋትነት ዜጎችን እጅግ በጣም የሚያኮራ ድርጊት መሆኑን እነአቶ መለስም ቢሆኑ የሚክዱ አይመስለኝም። ታዲያ እንዴት ነዉ ዳያስፖራ ኢትዮጵያዊያንን በልማት ብቻ ተሳታፊ ሁኑ እየተባለ ያለዉ? እንኳንስ አገር ቤት ገብቶ በዉጭ አገርም ቢሆን ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊ ነዉ፤ ስለኢትዮጵያ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያገባዋል።
*************************************************************************
በአገር ቤት ቆይታዬ በተለያየዩ ቦታዎች ተዘዋዉሬያለሁ፤ ናዝሬት፣ አዋሳ፣ ጂማ፣ ደብረማርቆስና ባህርዳር የመሳሰሉትን ከተሞች ለመጎብኘት ችያለሁ። በዚህ የጉብኝት ወቅት ግን በአጋጣሚ ከአንዳንድ ሰዎች ጋር በአዉቶቡስ ዉስጥ፣ ሻይ ቤት፣ ወይም በአጋጣሚ ዘመድ ጓደኛ ቤት ሁሉንም ማህበራዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን የዳሰሱ ወሬዎች ለማዉራት ችያለሁ። ስለህዝቡ የኑሮ ሁኔታ፣ ተመዘገበ ሰለሚባለዉ የኢኮኖሚ እድገት፣ ስለሚፈጸመዉ አድሎና ዘረኝነት፣ ስለተቃዋሚ ፓርቲዎች የወደፊት እጣ ፋንታና በአጠቃላይ ስለወደፊቷ ኢትዮጵያ በሰፊዉ አዉርተናል። ለማዉራት እድል የገጠሙኝ አብዛኞቹ ሰዎች ፍርሃት ይታይባቸዋል። ስለመንግስት የሚወራ ማንኛዉም ጉዳይ ፖለቲካ በመሆኑ “የፈንጅ ወረዳ” ለመግባት ወይም “ቀይ መስመር ለመርገጥ” ጊዜ ይወስድባቸዋል። ለአንዳንዶቹ ፖለቲካ ማዉራት ነዉር (taboo) ነዉ። ለሌሎቹ ደግሞ ስለመንግስት ማዉራት ለአደጋ ይዳርጋል። አንዳንዶቹ የእኔን ማንነት በመጀመሪያ ማወቅ ይፈልጋሉ ምክንያቱም በየሰፈሩ የበግ ለምድ ለብሰዉ ለቁጥር የሚታክቱ የህወሃት ኢህአዴግ ሰላዮች ስለተሰማሩና እኔም ከእነሱ ዉስጥ አንዱ ልሆን እንደምችል በመገመታቸዉ ነበር። እንዲያዉም ሰዎቹ የሚፈሩት ከዚያ ባለፈ የሚመጣዉን አደጋ ነዉ፣ ሁሉም እንደሚሉት ከሆነ በየትኛዉም ሰአት ሊታሰሩ ሊገረፉ ወይም በአንዱ ማጎሪያ ደብዛቸዉን ሊጠፏቸዉ ስለሚችል ከፖለቲካ ዉይይት ራሳቸዉን መቆጠብን መርጠዋል።
ጅማን በስሙ ብቻ እንጂ አገሩን አላዉቀዉም ነበር። ወደዚያዉ ባቀናሁ ሰሞን በጅማ ዩንቨርስቲ የሚመረቅ አንድ ዘመድ ስለነበረኝና አካባቢዉንም አይቼ ሰለማላዉቅ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ በማለት ጉዞዬን ለመጀመር ተሰናዳሁ። ከአዲስ አበባ አዉቶቡስ መናኸሪያ የጅማ አዉቶብሶች ትኬት ቆርጠዉ ስለጨረሱ በአጋሮ አዉቶቡስ የመጨረሻ መቀመጫ በማግኘቴ ትኬት ቆረጥኩ። መቀመጫ ያገኘሁት ከመጨረሻ ስድስት ከሚይዘዉ ወንበር ላይ ነበር። በቀኝ በኩል ሁለት የቆዳ ጃኬት የለበሱ ወንዶች በአንድ ጎን (በኋላ እንደነገሩኝ የአንድ መስሪያ ቤት የስራ ባልደርቦች ናቸዉ) በሌላ ጎን በግራ በኩል ደግሞ አጋሮ ድረስ የምትሄድ አንድ ወጣትና ሁለት አዛዉንት ሴቶች ሆነን ቁጭ አልን። ሆኖም ከሁዋላ 6 የሚይዘዉ መቀመጫ አምስቱ ስለያዙት በረዳቱ “ከኋላ 6” ትዕዛዝ ከተንሸራሸሩ በሁዋላ ለእኔ ያለመደገፊያ ጥቂት ቦታ ለቀቁልኝ። አዉቶቡሱ መጓዝ እንደጀመረ በኦሮምኛ ብቻ ያወሩ ከነበሩት ወንዶች አንዱ
“ይህ ላፕቶፕ ነዉ እንዴ?” ብሎ በአማርኛ ጠየቀኝ ማስቀመጫ ቦታ በማጣት በእጄ የያዝኩትን ላፕቶፕ እያየ።
“አዎ” የሚል መልስ መለስኩለት።
“ምን እኮ….ማንም ሰዉ ሊኖረዉ የሚገባዉ ግን በጣም ዉድ የሆነ አቃ ነዉ።” በማለት ጨዋታዉን ቀጠለ።
ከጎኑ የተቀመጠዉ ሰዉ ግን ምንም ሳይናገር ለረጅም ጊዜ የምናወራዉን ያዳምጥ ነበር። በጨዋታ መካከል ላፕቶፑን ለምን አገልግሎት እንደገዛሁት ወይም የትኛዉ መስሪያቤት እንደሰጠኝ ጠየቀኝ። ተማሪ እንደሆንኩና አዉሮፓ አገር ለጊዜዉ እንደምኖር ስነግረዉ መንግስት ስላከናወነዉ ልማት ምን አስተያየት እንዳለኝ በተደጋጋሚ ይጠይቀኝ ጀመር። በመጀመሪያ ያነሳዉ በመንገድ ግንባታ ምን ያክል ጥሩ ደረጃ ላይ እንደሆንን ነበር። በዝምታ ያዳምጠን የነበረዉ ሰዉ ባሰበት። እኔም የተሰሩትን ነገሮች አመስግኜ ያልተሰሩት ብዙ ነገሮች እንዳሉ ስነግራቸዉ ዳያስፖራ ኢትዮጵያዉያን (እኔንም ዳያስፖራ ኢትዮጵያዊያን ጋር በመደመር) ሁሉ ለአገራችን ልማትና ብልጽግናን መመኘት ሳይሆን ዉድቀቷንና ድህነቷን ሁሌ የሚመኙ መሆናቸዉን ሳያመነቱ ሁለቱም እየተቀባበሉ ተረኩልኝ። እንዲያዉም በአገር ዉስጥ ያሉ ተቃዋሚ ነኝ ባይ ፓርቲዎች ከዉጭ አገር ካሉት ኢትዮጵያዉያን ጋር ተመሳጥረዉ የአገሪቷን ሃብት ለምዕራብያዊን አገሮች በተለይም ለአሜሪካ ለመሸጥ በዝግጅት ላይ እንዳሉ ሆኖም ግን በኢህአዴግ ፓርቲና በአቶ መለስ ያላሰለሰ ቆራጥ አመራር አገሪቷ ከአደጋ እንደዳነች፤ ለዚህም ምሳሌ ሊሆን የሚችለዉ 1997 ምርጫ ማግስት ተሞክሮ የከሸፈዉ ውስጥ ዉስጡን በምዕራባዉያን አገሮችና በምርጫ ታዛቢዎች ጭምር ሳይቀር ሲደገፍ የነበረዉ የቀለም አብዮት ነዉ በማለት ጉዳዩን ለእኔ ለማስረዳት ሞከሩ። ስለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የአመራር ችሎታ ደግሞ ከየትኛዉም የአለም መሪ ሁሉ የሚሻሉ አስተዋይና ብልህ መሪ እንደሆኑ ያለምንም ሃፍረት ማዉራት ጀመሩ። እንዲያዉም “ነብይ በአገሩ አይከበርም” በማለት ይሁዳዊያን እየሱስ ክርስቶስን እንዴት ያጥላሉ እንደነበርና ይህም ትንቢት በእኛ አገር ታሪክ ዉስጥ መተኪያ በሌለዉ መሪ በአቶ መለስ ዜናዊ ላይ እየደረሰ እንደሆነ እኔም እነሱም በማናዉቀዉ የፖለቲካ ይሁን የሃይማኖት ትንታኔ ሊጠምቁኝ ሞከሩ። እንዲያዉም እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ለኢትዮጵያ የሚያስብ ቆራጥ መሪ (ቆራጥ የምትለዋ ቃል ከጓድ መንግስቱ የተወሰደች መሰለኝ) በአገሪቱም ይሁን በዉጭ አገር እንደሌለ፤ አገራችን ኢትዮጵያም ካለእሳቸዉ ዉጭ ሌላ አርቆ አሳቢ መሪ በታሪኳ አግኝታ እንደማታዉቅ ወደፊትም እንዲህ ራዕይ ያለዉ መሪ እንደማታገኝ በዝርዝር ለማሰረዳት ሞከሩ። የኢህአዴግ አባላት ከልባቸዉ ይሁን ከአንገት በላይ አቶ መለስን ምን ያክል እንደሚያመልኩ በእርግጠኝነት የተረዳሁት ያኔ ከእነሱ ጋር ካደረግኩት ዉይይት በኋላ ነበር።
ለተወሰነ ጊዜ ካዳመጥኳቸዉ በኋላ ሌላ ጥያቄ አስከተልኩ። “ለመሆኑ እዚህ አገር የፖለቲካ ነጻነት አለ ወይ?” ብዬ ስጠይቅ መልሳቸዉ ሁለቱም አንድ አይነት ነዉ፤ ባለማመንታት “አዎ” የሚል። ስለፖለቲካ እስረኞች (ለምሳሌ ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ)፣ ስለ 1997 እና 2002 ምርጫዎች፡ ስለፍትህ መጓደልና የሚዲያ ነጻነት አወራን። እንደእነሱ ገለጻ ከሆነ ሁለቱም ምርጫዎች “እንከን የለሽ” ነበሩ። በተለይ ደግሞ የ2002 ምርጫ ዉጤት ህዝቡ ከ1997 ከፈጸመዉ “ስህተት” በመማር ለኢህአዴግ የሰጠዉ የምራኝ ይሁንታ ነዉ። በጣም የገረመኝ ነገር ቢኖር ከላይ እስከታች ድረስ ያሉት ሁሉም የኢህአዴግ አባላት ኢትዮጵያ ዉስጥ የተፈጸመ ነገር ሁሉ የኢህአዴግ እጅ እንደሌለበት መካዳቸዉ ነዉ። ለምሳሌ በ1997 ምርጫ ማግስት በገፍ ለተገደሉና ደብዛቸዉ ለጠፉ ሰዎች ተጠያቂዉ ማን ነዉ በማለት ለጠየቅሁት ጥያቄ በጣም የሚዘገንን መልስ ነዉ የሰጡት። ሁለቱም ካድሬዎች “ተጠያቂዎቹ ሟቾቹ ናቸዉ! ኢህአዴግ ከሰዉ በላዉ ደርግ ነጻ ባወጣዉ አገር ለምንስ ነጻ አዉጪዉን ተቃዉመዉ ሰላማዊ ሰልፍ ይወጣሉ?” በሚል ጥያቄዬን በጥያቄ መለሱት። መንግስት የለም በሚያሰኝ ሁኔታ በወለጋ በኦሮሞና በአማራ እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የተፈጸሙትን ጭፍጨፋዎች ማን እንደፈጸማቸዉ ስጠይቃቸዉ ምናልባትም አንዳንድ “አክራሪዎች” በሴራዉ ሊኖሩበት ይችላሉ የሚል መልስ ሰጥተዉኛል። የህወኋት ኢህአዴግ እጅ እንዳለበት ማመን ግን አልፈለጉም። በሌላ አባባል ይህንን ሁሉ የዘር መከፋፈል ኢህአዴግ የሚከተለዉ የዘረኝነት ፖሊሲ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል በለስላሳ ቃላት ስጠቁማቸዉ ሁለቱም ዝምታን መረጡ። ከዉይይታችን እንደተረዳሁት የኢህአዴግ አባላት እርስ በእርስ እጅግ በጣም ይፈራራሉ ወይም የፖለቲካ ካቲካላቸዉ ዉሸት ብቻ የሚያስወራቸዉ ይመስለኛል።
አዉቶቡሱም መንገዱን ተያይዞታል፤ እኛም ወሬያችንን ቀጥለናል። የጉራጌ ዞን ዋና ከተማ ወልቂጤ እንደደረስን ለመንገድ የሚሆን ጫት መግዛት ነበረባቸዉ። ትንሽ እንደተጓዝን እኔም ከጫት ድግስ እንድቋደስ ጋበዙኝ። እንደማልቅም ነግሬያቸዉ እንደገና ወሬያችንን ስጀምር ከሁለቱ አንደኛዉ ሻንጣዉንና በእጅ የሚያዝ እቃ ማሰናዳት ጀመረ። “ለትራንስፖርት የከፈለዉ እስከአጋሮ፣ የሚወርደዉ ደግሞ እዚህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” ብዬ ስጠይቅ ለሁለት ሳምንት የኦህዴድ ፖለቲካ ስልጠና እንደሚሳተፍና ስብሰባዉም በጦላይ (ስሙን የረሳሁት መሰለኝ) እንደሚካሄድ ተነገረኝ። በተገንጣይ መንገድ ላይ አዉቶቡሱን አሰቆሞ ለኔም መልካም ተመኝቶልኝ ወረደ። ወሬዬን በመቀጠል ቀደም ብሎ በደንብ ሲያወራኝ የነበረዉን ወጣት የህወሃት ኦህዴድ ካድሬ በአባልነቱ ምን ያክል እንደሚያምንበት ጠየቅሁት፤ በአጠገባችን ያሉትን ሰዎች በደንብ ካስተዋለ በኋላ “እኔ አምኜበት ሳይሆን የእንጀራ ጉዳይ ሆኖብኝ ነዉ” የሚል አስገራሚና ያልጠበቅሁት መልስ በለሆሳስ ነገረኝ። እኔም በጣም ገረመኝ። ወጣቱ ካድሬ እንደነገረኝ ከሆነ ከአዋሳ ዩንቨርስቲ ግብርና ኮሌጅ በቅርብ ጊዜ ተመርቆ እጅግ ሩቅ ገጠር እንዲሰራ ይመደባል። አንድ አመት ሰርቶ ኑሮ አልስተካከል ሲለዉ በፈቃደኝነት የኦህዴድ አባል በመሆኑ ወደ ተሻለ ከተማ ያስጠጉታል። እሱ እንደነገረኝ ወደ ተሻለ ከተማ ያመጡት ምክንያት ማንኛዉንም ፈጽም የተባለዉን ነገር ሁሉ በፍጹም ታማኝነት ስለሚያከናዉንና ለዚህ ዉለታ ከዉሎአበልም ከደመወዝም ዳጎስ ያለ ንዋይ እንደሚሰጡት አጫወተኝ።
ጨዋታችን ደራ፤ ጫቱንም በዉሃ ማወራረድ ጀመረ። በእኔ በኩል ያለዉን ጉንጭ ጥቅጥቅ አድርጎ ወጥሮታል። አሁን በደንብ የልቡን ማዉራት ጀመረ። እንደካድሬዉ አባባል ሁኔታዎቹ ከተቀየሩ በዚህ “ዘረኛ መንግስት” ላይ መሳሪያ የሚያነሳ የመጀመሪያ ኢትየጵያዊ ቢኖር እሱ ራሱ እንደሚሆን በአጠገባችን ማንም ሰዉ እንደማያዳምጠን አማትሮ ካየ በኋላ ሳይደብቅ ነገረኝ። ቀደም ብዬ በሶስትዮሽ ዉይይት እኔ ያነሳኋቸዉ ነገሮች ሁሉ እዉነት እንደሆኑና የአኔን ሃሳብ እንደሚጋራ ነገር ግን ከባልደርባዉ ፊት ካመነ ነገ ከነገ ወዲያ ወደ ግምገማ በሚቀርቡበት ጊዜ ችግን እንደሚፈጥርበት፤ በአቋሙ እንደሚያስገመግመዉ ይህ ደግሞ ህይወቱን አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን በደንብ ስለተረዳ በመሆኑ እንደዋሸኝ ለጋ ጫት እየቀነጠበ በሃዘኔታ አጫወተኝ። ስለዋሸኝም ከልቤ ይቅርታ እንዳደርግለት ለመነኝ። በመቀጠልም ባልደርባዉም ጭምር የኦህዴድ አባል የሆነዉ ለጊዜዉ ለእንጀራዉ ብሎ እንጂ በምንም መልኩ አምኖበት እንዳልሆነ በግልጽ አስረዳኝ። ሆኖም ደጋግሞ የነገረኝ ነገር ቢኖር ማንኛዉንም የህወሃት የበላይነትን የሚገረስስ ሃይል ካገኘ በቅርቡ እንደሚቀላቀል ነዉ። የኢህአዴግ ቤት ዉስጡ ምስጥ የበላዉ እንጨት መሆኑን በተደጋጋሚ ገለጸልኝ። ድርጅቱን ለመጣልም ብዙ ሃይል ሳይሆን ጥቂት ግን በአግባቡ የተደራጀ ሁሉንም ኢትዮጵያዉያንን የሚወክልና በሁሉም አካባቢዎች ድጋፍ ያለዉ ድርጅት አስፈላጊ እንደሆነ በዝርዝር አስረዳኝ። የዳያስፖራና በአገር ዉስጥ ነፍጥ አንስተዉ የሚታገሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ይህንን ማቀናጀት የአለመቻላቸዉ ጉዳይ በጣም እንደሚያሳዝነዉ በቁጭት አወጋኝ። እንደእሱ እምነት ከሆነ ህወሃት ኢህአዴግ በምንም መልኩ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ስልጣን አይለቅም! እናም በኢህአዴግ ዘመን በምርጫ መሳተፉ ትርፉ በሰላም የሚኖረዉን ህዝብ ማስገደል ማሳሰርና ደብዛ ማስጠፋት ብቻ ነዉ አለኝ። በመሆኑም መንግስት፣ ፓርቲና የሃይማኖት ድርጅቶች በአንድ ሰፈር ልጆች በሚመሩበት አገር በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ አገር ቤት ያሉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶቸና ግለሰቦች ኢህአዴግን በምርጫ ለማሸነፍ አፋቸዉን ሞልተዉ ሲናገሩ ሲሰማ ሁሌ እንደሚገርመዉና በምንም መልኩ የማይታሰብ ድርጊት እየሞከሩ መሆኑን ገለጸልኝ። በመቀጠልም አብዛኛዉ የኦህዴድ አባል የህወሃት ኢህአዴግ አባል የሆነበት ምክንያት ከራሱ ጀምሮ ከርሱን ለመሙላት እንጂ አይዲዮሎጂዉ አማልሎት አይደለም።
*************************************************************************
ይኸዉ በአባጅፋር ዋና ከተማ ሶስት ቀን አሳልፌ ወደአዲስ አበባ በሚኒባስ ልመለስ ከሾፌሩ በስተኋላ 2 ረድፍ ርቄ በመስኮት በኩል ቁጭ ብያለሁ። ከመናኸሪያ ሳንወጣ አንድ በ30ዎቹ መጀመሪያ የእድሜ ክልል ዉስጥ ያለ ወጣት አጠገቤ ተቀምጦ በእኔ በኩል አሻግሮ በመስኮት ከቆመች ወጣት ሴት ጋር ያወራል። ኦሮምኛ በትንሹ ስለምችል የሚባባሉት ይገባኛል። ፍቅረኞች ናቸዉ። በፍቅረኞች መካከል የሚደረግ ወሬ ቢያዳምጡት አይጠገብም። የመለያያቸዉን እያወሩ ስለነበረ ብዙ ርዕስ አንስተዋል። ከአይናቸዉ ዉስጥም የሰቀቀንና ናፍቆት ነበልባል ይነበባል። ሚኒባሱ ቀስ ብሎ መንቀሳቀስ ሲጀምር ፍቅረኛዋም አፍቃሪዋን ከጫነችዉ ሚኒባስ ጎን ጎን ተከትላ አብራን ተንቀሳቀሰች። ሁኔታቸዉ እየገረመኝ ነበር። እሱም ቢሆን አይኑን ከእሷ አልነቀለም፤ እሷም ፍቅረኛዋን ከጫነዉ መኪና ጋር ዉድድር የምትገጥም ትመስላለች። ነገር ግን መኪናዉ ጉልበቱን ጨምሮ ወደፊት በፍጥነት በረረ። ወጣቱም ለመጨረሻ ጊዜ ዉድ ፍቅረኛዉን ለማየት አንገቱን ጠመዘዘ፤ አይ ብዙ ርቀናል!
ትንሽ እንደሄድን ይህ ወጣት ሰዉ ተደላድሎ ሲቀመጥ ያልጠበቅሁትን ነገር በጎን በኩል ገፋ አረገኝ! ከለበሰዉ ጃኬት ዉስጥ በግራ በኩል ያነገተዉ ሽጉጥ መሆኑን ተረዳሁ። ምንም መልስ አልሰጠሁትም፤ እሱም እኔን ገርመም እያደረገ ከማየት የቦዘነበት ጊዜ የለም። ጸጉረ ልዉጥ መሆኔን ተገንዝቧል። በእዉነቱም የህወሃት ኢህአዴግ ነገር ስለማይታመን በእኔ ላይ እርምጃ ሊወስድብኝ የመጣ የደህንነት አባል መሰለኝ። በዚሁ ቅጽበት ደግሞ ብዙ ሃሳቦች በአእምሮዬ መመላለስ ያዙ። በአንድ በኩል ከአራት ቀን በፊት ከአዲስ አበባ ወደጅማ ስሄድ ያገኘኋቸዉ ካድሬዎች እርምጃ እንዲወስድብኝ የላኩት መሰለኝ። በሌላ በኩል ደግሞ በአጋጣሚ የተሳፈረ የደህንነት አባል ሊሆን ይችላል ብዬ ራሴን ለማረጋጋት ሞከርኩ! ታዲያ ባለጊዜ ካልሆነ በቀር ማን በጠራራ ጸሃይ ሽጉጥ ይይዛል? ለምንስ እኔ እንዳዉቅ አደረገ? በሰላም አገር ለምንስ ሽጉጥ መያዝ ያስፈልጋል? በዚህ ሃሳብ ባህር ዉስጥ ሰምጬ ባለሁበት ሰአት ሚኒባሱ ስለሚሞቅ በትንሹ መስኮት እንድከፍትለት ጠየቀኝ። እኔም ራሴ ሞቆኝ ስለነበር በደስታ የምከፍትለት መሆኑን፣ ለጤናችንም ቢሆን ንጹህ አየር እንደሚያስፈልገን እያወራን እያለን ስማችንንና የምንሰራበትን መስሪያቤት ተለዋወጥን። እኔ ለጊዜዉ ባላምነዉም የፍቅር ጓደኛዉን ሊያስመርቅ የመጣ የጉምሩክ ሰራተኛ መሆኑን አስረዳኝ። አሁን ግን ሴት ጓደኛዉ አንዳንድ ፎርማሊቲዎችን ጨርሳ መምጣት ስለሚኖርባት እስከዚያዉ ድረስ እሱ በመስሪያቤቱ በጣም አስፈላጊ ሰዉ በመሆኑ ቶሎ መሄድ እንዳለበት ነገረኝ። ከጅማ እስከአዲስ አበባ ድረስ በሚኒባስ ታሪፍ የሚከፈለዉን የሁለታችንንም ትራንስፖርት ሂሳብ ከኪሱ ከ 300 ብር አዉጥቶ ለረዳቱ ሰጠ። እኔ የምዕራብያዉያንን የኑሮ ስልት ስለቀመስኩ የራሴን ለመክፈል ብከራከርም እሱ እንደሆነ ኢትዮጵያዊ ሩህሩህነት ስላለበት የሁለታችንንም እከፍላለሁ ብሎ አሻፈረኝ አለ። የምረቃ ሰሞን ስለነበረ የሚኒባሱ ሂሳብ በመቶ አምሳ ታሪፍ ጭማሪ ነበረዉ። ከዚያም ብዙ ነገር አልተነጋገርንም። እኔ እንደፈራሁት ነዉ፤ አላመንኩትም። እሱም ቦታዉ ስላልተመቸዉ ይመስለኛል ዝም ብሏል።
መኪናዋ በሙቀት ስላአደባየችን ላብ በሰዉነታችን ይንጠፋጠፋል፤ ተሳፋሪዎች አብዛኞቹ ነጋዴዎች ይመስሉኛል። የ “ጀበና” በሚል ቅጽል በ 130 ብር ጫት ተገዛ። በዚህ አጠቃቀም ቃሉ ለእኔ አዲስ ስለነበር ማብራሪያ ጠየቅሁ። “ሰዎች ገንዘብ አዋጥተዉ ጫት ይገዙና በኋላ በእኩል መጠን ለባለድርሻዎቹ የሚከፋፈል” መሆኑን ሹክ አለኝ። ጊቤ ወንዝን አቋርጠን የምሳ ሰአት ደረሰ ተባለና አንድ ሰሟን ከረሳኋት ከተማ ሹፌሩ መኪናዉን አቆመልን። ባለሽጉጡ ወጣት አብረን እንድንበላና እንድንጠጣ ጋበዘኝ። ግበዣዉን መቀበል ነበረብኝ፤ እንደግዴታም አይነት መሰለኝ። ሆኖም አሁን ይበልጥ ጥርጣሬ ገባኝ። “ይህ ሰዉ እያታለለኝ ነዉ እንጂ ደህንነት መሆን አለበት” በማለት ለሚመጣዉ ሁሉ ራሴን አዘጋጀሁ። ሁለት ጥብስ ካዘዝን በኋላ አስተናጋጁ ሁሌ እንደዳዊት የሚደግመዉን ሃረግ “የሚጠጣ ነገር ምን ይምጣ?” በማለት ጠየቀን። እኔ ዉሃ አዘዝኩ፤ አዲሱ በሚኒባስ የተዋወቅሁት ጓደኛዬ ግን የኔን ምርጫ ተቃወመ። “ለሁለታችንም ድራፍት አምጣልን!” አለዉ። እኔም የራሴን ተቃዉሞ አሰማሁ። መድሃኒት እየዋጥኩ ስለሆነ አልኮል ይዘት ያለዉ ነገር እንደማልጠጣ በአንድ ሁለት ኡኡታ ሳል መረጃ አስደግፌ አስረዳሁት። ተስማማን። እኔም ከዉሃዉ አዲሱ ጓደኛዬ ደግሞ ከድራፍቱ አንድ ሁለት አልንለት።
በመቀጠል ስራዉ እንዴት እንደሆነ ጠየቅሁት። ወጣቱ መልከመልካም ነዉ። ፈገግ ብሎ፣ “ስራ? እኔ እኮ ለደሞዝ አይደለም የምሰራዉ! አንዳንዴ እንዲያዉም ወሩ አልፎ ደሞዜን ሳልወስድ እቀርና ሂሳብ ክፍሎቹ ለማወራረድ እንዲመቻቸዉ ስልክ ደዉለዉ እንድወስድ ይለምኑኛል” አለኝ። ልመና? ወይ ጉድ! ለምን ደሞዙን በጊዜዉ እንደማይወስድ ስጠይቀዉ በመንግስት የሚከፈለዉ ደሞዝ ከሶስት ቀን ወጪዉ በላይ ሊሆን እንደማይችልና ይህንን ደግሞ አስታዉሶ መዉሰድ ሌላ ከባድ ፈተና እንደሆነበት በዝርዝር አጫወተኝ። ከዚያም ዙሪያዉን አማተረ፤ ገበታዉ ሳይነሳ የምኖርበት አገር መታወቂያ እንዳሳየዉ ጠየቀኝ። በድንጋጤ ክዉ አልኩ፤ ሆኖም የነበረኝ መታወቂያ ፓስፖርት ብቻ ስለነበር ከላፕቶፕ ቦርሳዬ አዉጥቼ አሳየሁት። ቀጥሎም “እኔ አሁን የቸገረኝ ነገር እንዴት ከዚህ መስሪያ ቤት ለቅቄ እንደምወጣ መላ ማጣቴ ነዉ” አለኝ። ከስራዉ በቀን በአስር ሺ የሚቆጠር ብር በጉቦና በድርድር መልክ አንደሚያኝ፤ በጣም በቂ ሃብት እንዳለዉ ሆኖም ያከማቸዉን ገንዘብ በሌሎች ዘመዶቹ ስም አዛዉሮ የጊዜን አመቺነት እየጠበቀ እንደሚገኝ አጋጣሚዉን ካገኘ ደግሞ አገር ጥሎ ሊጠፋ እንዳሰበ በዝርዝር አጫወተኝ። መታወቂያ የጠየቀኝ እሱ ተጠራጥሮኝ ኖሯል፤ ያመነኝ ፓስፖርቴንና በላዩ ላይ የተመታዉን ቪዛ ካየ በሁዋላ ነዉ። ከጊዜዉ አንጻር እዚህ ቦታ ላይ ከተነጋገርነዉ በላይ ማዉራት ስላልቻልን ወደመኪናችን ከመመለሳችን በፊት የተመገብንበት ሂሳብ መከፈል ነበረበት። አሁን እኔ እከፍላለሁ ብዬ መቶ ብር ሳወጣ እጄን ለመታጠብ በሄድኩበት ጊዜ አስተናጋጁ ጓደኛዬ እንደከፈለዉ አስረዳኝ። እጁን ታጥቦ ሲመጣ ለምን እኔ መክፈል ሲገባኝ እሱ እንደከፈለ ስጠይቀዉ “አንተ ገና ብዙ የምትረዳኝ ነገር አለ!” ነበር መልሱ። ምን ይሆን የምረዳዉ በማለት ዝም አልኩ።
መኪናችን ይዛን ወደአዲስ አበባ በረረች። የየግል ጉዳያችንን እያወራን አዲስ አበባ እንደደረስን ወደናዝሬት እሄዳለሁ አለኝ። እኔም ወደናዝሬት እየሄድኩ ስለነበር አብረን መሄድ እንዳለብን ተስማማን። ሆኖም አዲስ አበባ እንደደረስን ደክሞን ስለነበር ትኩስ ሻይ ቡና ፉት እያልን አብረን ለአንድ ሰአት ያክል አወራን። በእዚህ ጽሁፍ መግለጽ የማልችለዉን ብዙ የመስሪያ ቤቱን ምስጢር በዝርዝር አወራኝ። በተወሰኑ ነገሮች እንዳላመንኩት ሲገባዉ መታወቂያዉን አዉጥቶ አሳየኝ። የኢህአዴግ አባል ነዉ። ስልጣኑን መከታ በማድረግ ዘመድ አዝማድ በራሱ መስሪያ ቤት እንዳስቀጠረ የጀግንነት ታሪኩን አወጋልኝ። በእርግጥም የጉምሩክ ሰራተኛ ወሳኝ ከሆነ ቦታ የተቀመጠ ሰዉ። ሰዉየዉ በአሁኑ ጊዜ ያፈራዉን ንብረት በዝርዝር ቆጠረልኝ። የትየለሌ ነዉ። ከ 10 የማያንሱ የድርጅትና የመኖሪያ ቤቶች በአዲስ አበባ፣ ደብረዘይት፣ ሞጆና ናዝሬት፤ የተለያዩ ኤሮትራከር የጭነት መኪናዎች መለስተኛ አዉቶቡሶች አይሱዙ ኤፍ ኤስ አርና የድንጋይ መጫኛ ገልባጭ መኪኖዎች (ሁሉም ንብረቶች በቤተሰብ ስም የተገዙ) በባንክ በቤተሰብ ስም የተቀመጠ ጥሬ ገንዘብ ወዘተ አንድ በአንድ ተረከልኝ። ሆኖም በራሱ ስም ከ 3ሺ ብር ያልበለጠ ገንዘብ በባንክ እንዳለሁ አስረድቶኝ “አህያ ቢራገጥ ጥርስ አይሳበርም” አለኝ የዘመድን አንጀት አለመለያያት ሲያብረራልኝ። ከቤተሰብ ጋር ጸብ እንኳን ቢፈጠር እነሱ የሚወስዱት ትንሽ ገንዘብ ብቻ እንደሆነና እንደማይጨክኑበት አብራራልኝ። ቀጥሎም አንዳንድ ጊዜ በቀን 10ሺ ብር ድረስ በጎቦ መልክ እንደሚያገኝና የአገራችን የሙስና ቅሌት ምን እንሚመስል በራሱ ምሳሌ አስረዳኝ። ይህንን ሁሉ ገንዘብ እንዴት በጉቦ መልክ ሊቀበል እንደቻለ ስጠይቀዉ ሁሉም የሚዘርፍበት አገር ስለሆነ እሱም ሌሎችን ዘራፊዎችን መመሳሰል እንዳለበት አለበለዚያ ግን ወይ ሊያስሩት አለበለዚያ ባላሰበዉ መንገድ ሊያስወግዱት እንደሚችሉ በተደጋጋሚ እንደተነገረዉ ተረከልኝ። ሆኖም በዚያን ጊዜ ያልተሟላለት አንድ ችግር ነበረበት፤ አገር ጥሎ መዉጣት እንዴት እንደሚቻል አለማወቁ። ለዚህ ደግሞ መንገዱን እኔ እንድነግረዉ ወይም ወደአዉሮፓ እንዲወጣ እኔ እንድጋብዘዉ ለዚህም ወረታዉን በማንኛዉም ጊዜ ሊከፍለኝ እንደሚችል (ካለዉ አጠቃላይ ንብረት አንድ ሁለት ቤት ከፈለግሁበት ቦታ በስሜ ሊያዛዉርልኝ) በራስ በመተማመን መንፈስ አጫወተኝ። እኔም በዉስጤ እስቅ ጀመር፤ ሞኝነቱም አሳዘነኝ። ስልክ ተለዋወጥን።
በአጋጣሚ የተገናኘን ሰዎች ናዝሬት ድረስ በአንድ ወንበር ላይ ተሳፈርን። በጨዋታችን መካከል እኔና ዉጭ አገር ያለዉ ዳያስፖራ መሰሎቼ ስለሁኔታዉ ሳንገነዘብ ዝም ብለን ከመለፍለፍ ዉጪ ይህ መንግስት ምን እንደሚሰራ በእርግጠኝነት እንደማናዉቅ በዝርዝር አጫወተኝ። የስርአቱ ዋናዉ አንቀሳቃሽ መሳሪያ ህዝብ ሳይሆን ገንዘብ ብቻ እንደሆነ አስረግጦ ነገረኝ። “ገንዘብ ካለህ ማንንም ሰዉ እንደባሪያ ትገዛዋለህ። የፈለከዉን ነገር ታሰራዋለህ። ገንዘብ ካለህ ሰዉ ታስገድላለህ! የሚነካህ የለም ምክንያቱም በየደረጃዉ ጉቦ ትሰጥና ዳኞቹንም ሆነ መርማሪ ፖሊሶችን ዝም ማሰኘት ብቻ ሳይሆን መረጃዉንም ደብዛዉን ታስጠፋዋለህ። የኢህአዴግ አባላትም ገንዘብ ስለሚከፈላቸዉ ምንም ነገር አድርጉ ብትላቸዉ ከማድረግ ወደኋላ አይሉም። ለዚህ እኮ ነዉ የህወሃት አባላት በሙሉ ወደቢዝነስ አለም የገቡት! ማንንም ሰዉ በፈለጉበት ጊዜ መግዛት ይችላሉ” ነበር ያለዉ። በተዘዋዋሪ እኔንም እሱ ወደዉጭ አገር እንዲወጣ ቢዝነስ ዉስጥ አስገባኝ ማለት አይደል? የኢህአዴግ ሰዎች የሚያስቡት እንዲህ ሆኗል፤ ማንኛዉንም ሰዉ በገንዘብ መግዛት ይቻላል።
ናዝሬት በመድረሳችን መለያየት ነበረብን። ሁኔታዎቹንም በጥሞና እንድንነጋገር ለችግሩ መፍትሄ እንድንፈልግ ከአደራ ጋር አብይ ቀጠሮ ሰጠኝ። ዉሃ የመሰለ የቤት መኪና አቅርቦም ወደምሄድበት ላድርስህ አለኝ። ሆኖም ላደረገልኝ ሁሉ አመስግኜ የላድርስህ ግብዣ ሳልቀበል ቀረሁ። ከዚያ ቀን በኋላ ከ20 ጊዜ በላይ በተደጋጋሚ ደዉሎ እንድንገናኝ መፍትሄዉንም እንድነግረዉ ይጠይቀኝ ነበር። ነገር ግን በሆነ ባልሆነ አስባብ ግብዣዉን ሳልቀበል ወደባህርዳር ጉዞዬን ቀጠልኩ። ወደባህርዳር ስሄድ በአዉቶቡስ ዉስጥ የገጠሙኝም የኢህአዴግ ብአዴን ሰዎች ነበሩ።
*************************************************************************
ክፍል ሁለት ይቀጥላል!