ምርጫ ቦርድ ሕገ ወጠ በሆነ መንገድ ገንዘብ እንዳከፋፈለ ተዘገበ !

አቡጊዳ – ነሐሴ 9 ቀን 2002 ዓ.ም

እራሱን ገለልተኛ አድርጎ የሚቆጠረዉ፣ ግን በብዙዎች የገዢዉ ፓርቲን ጥቅም የሚያስጠብቅ እንደሆነ የሚነገርለት፣ የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ከ2002 ምርጫ በፊት ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ገንዘብ ለድርጅቶች እንደሰጠ የሚዘግቡ ዘገባዎች በአዲስ አበባ እየተሰሙ ነዉ።

የሪፖርተር ጋዜጣ፣ የአየለ ጫሚሶ ቡድን ምክትል ሊቀመንበር የነበሩትንና እራሳቸዉን ከቡድኑ ያገለሉትን፣ አቶ ለገሰ ቢራታን በመጥቀስ፣ ሪፖርተር ጋዜጣ በእሁድ ነሐሴ 9 እትሙ፣ የምርጫ ቦርድ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ፣ ሁለት የፓርላማ መቀመጫ ብቻ ያለዉ የአየለ ጫሚሶ ቡድን ፣ ከአርባ በላይ መቀመጫ እንዳለዉ ተደረጎ፣ አንድ መቶ አርባ ሺህ ብር እንደተሰጠዉ ዘግቧል።

ከምርጫ ዘጠና ሰባት በኋላ የቅንጅትን ስም በአቶ አየለ ጫሚሶ ለሚመራዉ ቡድን እንዲሰጥ መደረጉ ይታወቃል። ይህ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ የቅንጅትን ስም የወሰደዉ ቡድን፣ በኢትዮጵያ ምድበለ ፓርቲ እንዳለ ለማሳየት ገዢዉ ፓርቲ የሚያደርገዉን የማታለል እንቅስቃሴ ይረዳ ዘንድ፣ እንደ አንድ ተቃዋሚ ተደርጎ በሸራተኑ የስነ ምግባር ፊርማ ሥነ ስርዓት ላይና በምርጫ ክርክሮች ላይ እንዲሳተፍ መደረጉ ይታወሳል።

እራሱን ቅንጅት ብሎ የሚጠራዉ የአየለ ጫሚሶ ቡድን፣ እንደ አንድ ትልቅ የዴሞክራሲ ስኬት ሲወራለት የነበረዉና የሥነ ምግባሩ ስምምነት የወለደዉ የፓርቲዎች ምክር ቤት ሙሉ አባል ሲሆን፣ የቡድኑ አባላት ለገዢው ፓርቲ ያሳዩት ታማኝነትና ዉለታ ሳይከፈላቸዉ በባዶ እንዲቀሩ መደረጉ የ99.6% የምርጫ ዉጤት በግልጽ አሳይቷል።