ትውስታዬ በውጭ ጉዳይ ሚንስቴር – ክፍል 4
በክፍል ሦስት ጓደኛሞችን እየከፈሉ ወሬ እንዲሰጧቸው ጫና ሲፈጥሩባቸው ተርኬ አቁሜ ነበር አሁን ደግሞ ከዚያ ተከትሎ የተፈጸመውን እተርካለሁ።
ወደ ውጭ አገር መመደብን ተስፋ አድርጎ የቆየ በሙሉ የምደባው እድል እንዳታመልጠው ሲል “ጌቶቹ” መስማት የሚፈልጉትን ሁሉ “እውነት” ነው እያለ በመናገር ወንድምና እህቶቹን አሳልፎ ለመስጠት ልቡ ፈቀደ።በዚህ ሁኔታ ጓደኞቻቸውን አሳልፈው ከሰጡ በኋላ ያለቀሱ አሉ።የሳቁም አሉ። የጓደኞቻቸውን ዓይን ትኩር ብለው ለማየት የተሰቀቁም ነበሩ።ያለቀሱትም፤የሳቁትም፤በሃፍረት የተሸማቀቁትም ከማንም ጋር ወዳጅነትን አላተረፉም።አሁን ዜጎች ወንድሜ ወንድሜ መባባልን ትተው አንዱ አንዱን በሃሰት ለመክሰሰ የማያፍሩባት አገር ተፈጥራለች።ይህን የመሰለ የሞራል ዝቅጠት በኢትዮጵያችን ለመፈጠሩና ለማደጉ ዋነኛው ተዋኒያን ደግሞ ህወሃት የተባለው ዘረኛ ድርጅት ነው።ይህ እኔ ብቻ በሚል ብርቱ በሽታ የተለከፈ ዘረኛ ድርጅት አገራችንን ነድቶ እየከተተ ያለበትን የሞራል ውደቀት የሚያሳየን አንዱ ሰበዝ ዜጎች ለምናምንቴና ለከንቱ ጥቅሞች ሲሉ ለሃሰት መገዛታቸው ነው።አገርም ፈረሰ የሚባለው እንዲህ ለሚበላና ለሚጠጣ ብሎ ወንድም ወንድሙን፤ እህት እህቷን አሳልፈው መስጠት የጀመሩ ዕለት ነው።መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያን ማፍረስ እቅዱ ስለሆነ በሚሆነው ሁሉ ኮሪቼአለሁ ይላል።ሌሎች ግን ምን እየሆነ እንደሆነ እንዳያስቡ ርካሽ በሆነ ድሎት ሂሊናቸው ተይዟል።የክፉ መንግስትም መገለጫው የዜጎችን መልካም እሴቶች አዋርዶ ሲያበቃ መንገድ ሠራሁላችሁ እያለ ዜጎችን ማድረቁ ነው።
ህወሃቶች ወንጀል ብለው 42 ሠራተኞችን ከውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አባረው ጦም ሚያሳዳሩት፤ልጆቻቸውንም ድሃ አደግ የሚያደርጉበት ወንጀል ይሄውላችሁ፤
እነርሱ ወንጀል የሚሉት ቅንጅትን መደገፍን ነው።ህወሃቶች ወንጀል አድርገው የቆጠሩት የእነርሱን ከንቱ ፕሮፓጋንዳ አለማመንን ነው።ወንጀል ሁኖ የሚቆጠረው ተውኝ እንደሰው ላስብበት ማለትን ነው።ከተባረርነው መካከልም ጓደኛየ “የኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት በጠንካራ መሠረት ላይ ያልተጣለ ጤንነቱ እንደተጓደለ ህጻን ልጅ የሚውተረተር ነው” ብሏል ተብሎ ነው።ሌላው ደግሞ የተባረረበት ምክንያት “መለስ መላጣ” ብሎ ተሳድቧል ተብሎ ነው።እስኪ እግዜር ያሳያችሁ የመለስን መላጣነት ራሱ መለስ ይክደዋል ? እንግዲህ መለስ ዜናዊ “መላጣ ብሎ የሰደበህን ከሥራ አባረርነው” ብለው ቢነግሩት ምን ይላል ትሉ እንደሆነ እነሆኝ መልሱ።መለስማ ራሱን ሁሉን አዋቂ፤ ሁሉን አድራጊ ጣኦት አድርጎ ስለሳለው የተዘፈነለትን ቅንድቡን ከፍና ዝቅ አድርጎ ሲያበቃ ደግ አደረጋችሁ ይላል እንጂ ሌላ ምንም አይልም። መላጣ መሆኑ ግን እውነት እንጂ ውሸት አይደለም።በህወሃት ኢትዮጵያ ትንሿም ትልቁም እውነት ቦታ የላቸውም።ትልቁ እውነት የኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት በጠንካራ መሠረት ላይ አለመቆሙ ነው።ትንሹ እውነት ደግሞ መለስ ቅንድቡ የማያምር መላጣ ግለሰብ መሆኑ ነው።በውጭ ጉዳይ ውስጥ ትልቁንም ትንሹንም እውነት የተናገሩት ወንጀለኞች ሆነው በገዛ አገራቸው መጻተኛ ሆኑ።እንዲህ ዓይነት በደል በዜጎች ላይ ሲፈጸም እነሆ የመለስ ዜናዊን እድሜ አስቆጥሯል።እንግዲህ ዘመኑ ምናምነቴ በኢትዮጵያችን የሰለጠነበት ነው።ምናምንቴዎች በሰለጠኑ ግዜ ደግሞ ብዙ ነውር ነገሮች የተከበረውን ሥፍራ ይወርሳሉ።ነውረኞችም ፈራጆች በመሆናቸው ዜጎች ለስደት ይዳረጋሉ፤ አልሰደደም ያሉትም የመከራ እንጀራን ይበላሉ፤የመከራ ጽዋንም ይጎነጫሉ።
አሁን በየኢምባሲው የምናያቸው ዲፕሎማት ተብየዎች አብዛኛዎቹ ለህወሃቶች ወሬ በማቀበል ወገኖቻቸውን አሳልፈው የሰጡ ሞራለ ቢስ ግለሰቦች ናቸው።ለዚያ ነውር ተግባራቸው ሽልማት ይሆናቸው ዘንድ በየኢምባሲው ዲፕሎማት ተብለው ተሹመዋል።እነርሱም ካራባታቸውን ሸብ አድርገው ሰው መሃል ሲቆሙ ወንድምና እህቶቻቸውን አሳልፈው በመስጠታቸው የመጸጸትና የማፈር መልክ አያሳዩም።ብዙዎች ከኑሯቸው ልቀው ለማሰብ ፍላጎት ቢያጡም ጥቂቶች ደግሞ እዚያ ሁነው አገራቸው በነውረኞች እጅ በመውደቋ የሚቃጠሉ አሉ።በዚህ ዘመን ግዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል እንደሚባለው ስለሆነ የወገኖቻቸው መከራና ስቃይ የሚያሰቃያቸው ሆዳሞችን ተሸክመው ለመኖር የግዜው ፈቃድ ሆኗል።
የሚገርመው ነገር ደግሞ በስውር እየተጠሩ በወንድምና እህቶቻቸው ላይ መረጃ እንዲሰጡ የሚጠየቁ ግለሰቦች ስም ዝርዝር በሚስጥር ይያዛል ቢባልም በተለያየ መንገድ ማን በማን ላይ ምን እንደመሰከረ እንዲያውቅ ይደረጋል።እንዲህም በማድረግ በጓደኛሞች መካከል ጥላቻን ተከሉ።ህወሃቶች አገርን ለማፍረስ የሚጠቀሙት የታወቀው አንዱ ዜዴያቸው ይሄው ነው።ክፉ መንግስት እንዲህ በወንድማማቾች መካከል ጥላቻን እየዘራ ሥኳር ቀምሶ የማያውቅ ገበሬ ስኳር መቅመስ በመጀመሩ ልትደሰቱ ይገባል ይላል።እኛ ደስ የሚለን ሥኳር የሚቀምስ ገበሬ በመፈጠሩ ሳይሆን ማር እንደልቡ መብላት የሚችል ገበሬ ቢፈጠር ነበር።ማር ሊያፈራ የሚችለው ዛፍ በሙሉ በህወሃት አመራር ተመንጥሮ በማለቁ ገበሬው የለመደውንና ለጤናው መልካም የሆነውን ማር አጥቶ የሸንኮራ አገዳ ፍርፋሪ ፈለጋ ከከተሜው ጋር ለመሻማት በመሰማራቱ ሊያፍሩ ሲገባቸው ኮርተውና ተጀንነው በአደባባይ እየጮኹ ያደነቁሩናል ይሄንንም አልሰማም ያለውን ሁሉ ኮሚቴ እያቋቋሙ ይወቅሩታል።
ተሰውሮ የሰራተኛውን ማንነት ሲሰልል የከረመው ቡድን አጥንቶ 42 ሰራተኞችን መርጦ እንዲባረሩ አስወሰነ።እያንዳንዱ ተባራሪ ቅሬታ አለኝ ካለ ግን ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ተብሎ ለተቋቋመው ኮሚቴ ቅሬታ ማቅረብ ይችላል ሲባልም ተነገረ።የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ አባላት ተብለው የተሰየሙት የሚከተሉት ናቸው፤
አምባሰደር ሃሊማ መሃመድ(ኦሮሞ)
አምባሳደር ግርማ አማረ(አማራ)
አቶ ዋህደ በላይ(ትግሬ)
አምባሰደር አማን ሃሰን(ኦሮሞ)
አቶ ምንሊክ ዓለሙ(አማራ)
አቶ ዮሃንስ አብርሃ(ትግሬ)
ወ/ት ፍርዶሳ አብዱልቃድር(ትግሬ)
እነዚህ ግለሰቦች ቅሬታ ሰምተው ችግሩን ለመፍታት ለእውነት ለመቆም ሃሞት ያላቸው ግለሰቦች ናቸው ለማለት አይቻልም።እንዲያውም የመንግስትን ፖሊስ የተቃወመ ሁሉ መባረር አለበት ብለው የሚያምኑ ናቸው።ዋህደ በላይ የቆየ የትግሬ ነጻ አውጪ አባል ነው።ሁለቱ ወጣት ትግሬዎች ድርጅቱን ስለመቀላቀላቸው በግልጽ የሚታወቅ ነገር ባይኖርም የታሰሩበትን የጎሳ ሰንሰለት ግን ፈትው ነጻ ሰው ለመሆን የቻሉ አይደሉም።ሌሎቹ ግን ያው ሆዳም የሚባሉ ናቸው።ምኒልክ ዓለሙ ከዚያ በኋላ አምባሳደር ተብሎ ደቡብ አፊሪካ ላይ ተሹሟል።የሚፈልገውም እርሷን ሹመት ነበር አግኝቷታል።ሌሎቹ ግን ቀድመው አምባሰደር ተብለው የተሾሙ ሲሆኑ ህወሃቶች አማራውንና ኦሮሞውን ለማሰቃየት የሚጠቀሙባቸው ዱልዱም ብትሮች ናቸው።ሃሊማ መሃመድን ”ከዚህ ቀደም አምባሳደር ያልንሽ በስህተት ነበር ካሁን በኋላ ተራ ዲፕሎማት ሁነሽ ትኖሪያለሽ” ብለዋት ከአምባሳደርነት ወርዳ ተራ ዲፕሎማት ሁና እየኖረች ነው።ህወሃት የሚሾማቸው አብዛኞቹ አምባሳደሮች የተጣሉበት የሚበቅሉ አራሙቻዎች ናቸው።አምባሳደር ሲባሉ አብበው ፈክተው ይኖራሉ።ከዚያ ተነቅለው ተራ ዲፕሎማት ሁኑ ሲባሉም ለምን ሳይሉ አሁንም በጣሏቸው ቦታ አብበው ፈክተው ይኖራሉ።
እነዚህ ሰዎች የእኔን ጉዳይ አይተው እንዲፈርዱ ስለተሾሙ የተባረርኩበትን ደብዳቤ ይዤ ቅሬታየን ላሰማ ከፊታቸው ቆምኩ።ከዚያም ከሳሼ ማነው ብየ ስጠይቅ ሚስጢር ነው አይነገርም አሉኝ።እሽ ጥፋቴ ምንድ ነው አልኩ ? ጥፋትህ መንግስትን ትቃወማለህ።በመንግስትም ፖሊሲዎች ላይ እምነት የለህም።እንዲያውም የጠቅላይ ሚንስትሩን የአመራር ችሎታ ታናንቃለህ አሉኝ።ለምሳሌ ጠቅላይ ሚንስትሩ ባድመ ላይ ያሳዩትን አቋም አንቋሸሃል አሉኝ።ምን ማለት እንደሆነ አልገባ አለኝ።ዝም ብየ እንዲህ ዓይነት ወሬ ከየት እንዳገኙ ማሰብ ያዝኩ።በእድሜው አባቴ ለመሆን ዘመን ያለው የቢሮየ ተጋሪ ጋር እንዲህ ያለ ነገር መነጋገሬ ትዝ አለኝ።እንዴት እኔን የሚያህል ልጅ ወልዶ አሳድጎ ሲያበቃ እንዲህ ዓይነት ትኝሽ ነገር አምጥቶ እኔን ለማስባረር አጉልቶና አዳብሮ ለመጠቀም ልቡ ጠነከር እያልኩ ሳስብ ዘለግ ያለ ግዜ ወሰድኩ።በባድሜ ጉዳይ ስንነጋገር “በአመራሩ ችሎታ ላይ ጥርጣሬ አለህ እንዴ” ብሎ የጠየቀኝ ቢሮየን የሚጋራኝ የህወሃቱ አባል ነበር።በጣም ተገርሜ ሳበቃ እኔ በአመራሩ ላይ ጥርጣሬ የለኝም ስል ዋሸሁ።እነርሱም አላመኑኝም።በአመራሩ ብቃት ላይ ጥርጣሬ እንዳለህ በቂ መረጃ አለን።እንዲህ ዓይነት ጥርጣሬ ይዘህ ለመቀጠል አስቸጋሪ ስለሚሆን በዚህ ይብቃን አሉኝና አሰናበቱኝ።ከዚያም በገዛ አገሬ ይሄን ተናግረሃል ተብየ ከመባረሬ በላይ በሰብቅና የገዛ አገሩን ዜጎች በመሰለል ላይ የተመሰረት ደካማ መንግስት አገሪቷን እየገዛት መሆኑ ክፉኛ አሳዘነኝ።ከደርግ ያልተሻለ ክፉ ዘረኛና ዘራፊ ሥርዓት በአገሪቷ ላይ በመተከሉ ደርግን ለማስወገድ የተደረገው ትግል ፋይዳ ቢስ ትግል ሆነ።የብዙ ወጣቶች ሞትም ያው እንደተራ ሞት ሆነ እንጂ በሁላችን ዘንድ የሚያስዘክራቸው አልሆነም።
ከዚያም ወደ ቢሮየ መሄድ ወደ ሲኦል የመሄድን ያክል ተሰማኝ።ሰው ካራጁ ጋር እንዴት አብሮ ይቀመጣል ?ይህ ቢሮየን የሚጋራኝ ሰው መሳይ አውሬ ያን ሁሉ ሲለፈልፍ የነበረው ወሬ ከእኔ ለመልቀም መሆኑን አሁን ተከሰተልኝ።ያችን ትንጥየ ክርክር ወስዶ ሲነግራቸው ትንሽም ቅር አለመሰኘቱ ገረመኝ።ይህ ግለሰብ እኔን የሚያክል ልጅ አለው።እኔ እድሜየ ሃያ ሰባት ዓመት ሲሆነኝ እርሱ ከሃምሳ ዓመት በላይ ነበር።ከሃይማኖቱም ከእድሜውም ያላተማረ ክፍ ጨካኝ መሆኑን ሳስብ ሰይጣን ስጋ ለብሶ ቢሮየ ቁጭ ያለ መሰለኝ።ከሰይጣኑ በላይ ግን አገሪቷን የሚመሩት እንዲህ ዓይነት ምንምንቴ ሰዎች መሆናቸውን ሳስብ ከልቤ አለቀስኩ።
የህወሃትን እውነተኛ መልክ ዘረኝነቱን፤ሌብነቱን፤ሴሰኝነቱን፤አገር አጥፊነቱንና ስግብግብነቱን ብነግራቸው ኑሮ አገር ከድተሃል፤ዘርም አጥፍተሃል ብለው የሞት ፍርድ ሊፈርዱብኝ የቆሙ ኃይሎች መሆናቸው አሁን ዘግይቶ ተከሰተልኝ።የጠላትነት መገለጫው ይሄው ነው።እንዲህ ዓይነቶቹ ብድኖች ጠላቴ ካልሆኑ ሌላ ማን ጠላቴ ሊሆን ነው ስል ከራሴ ጋር ሙግት ያዝኩ።አሁን ይሄን ህወሃት የተባለውን ድርጅት ብጠላ ምኑጋ ነው ስህተት የሚሆነው ? እንደምንስ ሆኖ ልወደው ወይም ደግሞ ስሜት አልባ ልሆን እችላለሁ ? ዝም ብንል እንኳ ዘር ሃረጋችንን እየመዘዙ በጠላትነት ከሚያዩን ኃይሎች ጋር ምን ህብረት ሊኖረን ይችላል እያልኩና ከራሴ ጋር እየተሟገትኩ ወደ ቢሮየ አዘገምኩ።
ወደ ቢሮየ ገብቼ ይህን ምናምንቴ ግለሰብ እገድለው ዘንድም አሰብኩ።ሰውነቴ ሁሉ በበቀል ስሜት ተወጠረ።ይህ ሰው ተስፋየን ገድሎታል።ምኞቴንም አምክኖታል።የእኔን ህልም አምክኖ እርሱ እንዴት ነጹህ አየር እየተነፈሰ ይኖራል !? አይደረግም ስል ለራሴ ነገርኩት።እናም ይኖር ዘንድ አልፈቀድለትም ብየ ከቢሮየ ደርስኩ።ያ ክፉ ሰው ከቢሮየ የለም።ብቻየን ተቀምጬ ህወሃት በመሆንና ባለመሆን መካከል ያለውን ልዩነት ሳሰላስል ቆየሁ።እነዚህ ሰዎች ትግሬዎች ናቸው ወይስ ሌሎች ? እያልኩ ከራሴ ጋር ሙግት ያዝኩ ።እነዚህ ቡድኖች ትግሬን እንወክላለን ብለዋል ግን ለምን እንዲህ ያሰቃዩናል ? ለማንኛውም ድሮ እኛ የምናውቃቸው እነዚህያ ጠንካራ ሰራተኛ፤ግልጽ፤ውሸት የማያውቁ፤ሃይማኖተኛ እና አልፎ አልፎ ግልፈተኛ ናቸው የሚባሉት ትግሬዎች ዛሬ የሉም።በዚያ መልክ የምናውቃቸውን ትግሬዎች እወክላለሁ የሚል አንድ ቡድን እንዴት እንዲህ በገዛ አገሬ እንዳልኖር ይከለክለኛል እያልኩ በሃሳብ ባዘንኩ።ሂሊናየን የሚያሳርፍ መልስ ግን ላገኝ አልቻልኩም።
ከሳሹና መስካሪው በሚስጢር ተይዞ 42 ሠራተኞች ጥፋተኛ ተብለው እንዲባረሩ ተደርጎ ጦማቸውን ማደረ የጀመሩት የትግሬ ነጻ አውጪዎች ነን በሚሉ ሃይሎች ነው።የእነዚህ ተባራሪ ወገኖች እውነተኛው ጥፋታቸው እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ ፍላጎት ማሳየታቸው ብቻ ነበር።ሌላ ጥፋት ሌላ የስነምግባር ጉደለት የሌለባቸው ንጹሃን በእውቀታቸውም በስነ-ምግባራቸውም እንከን የማይወጣላቸው የአገሪቷ ልጆች ነበሩ።ግና ምን ያደርጋል ተባረሩ።በአገሪቷ ውስጥም ሰርተው እንዳይበሉ የሥራ መልቀቂያ እንዳያገኙ ተፈረደባቸው።
እኔም ጥፋተኛ ተብየ ከተባረርኩ በኋላ የሥራ ልምዴን የሚገልጥ ደብዳቤ እንዲሰጠኝ ስጠይቅ “በገዛ ፈቃዴ ሥራየን ለቅቄአለሁ” ብለህ አመልክትና እንጽፍልሃለን ብለው በበደል ላይ በደል ፈጸሙብኝ።መባረሬ በደል ነው።ካባረሩኝ በኋላ ሌላ ቦታ ሰርቼ እንዳልኖርበት ማድረግ ግን ከበደል በላይ ሁኖ ሮሮ ሆነብኝ።ለማን አቤት ይባላል ? ሁሉም ቦታ እነርሱ ናቸው።ከእነርሱ ጋርም ያሉ በርካታ ሆድ እንጂ ሂሊና የሌላቸው ብዙ ሌሎች ለምንም የማይሆኑ አሉ።ወዴት መሄድ እንዳለብኝ ግራ ግብት ብሎኝ ጸጥ ብየ እግሬ ወደ መራኝ ተጓዝኩና ከግቢው ወጣሁ።ብቻየን በሃሳብ እየናወዝኩ ባለበት ወቅት መለስ ተ/ማሪያም የተባለውን ከተባራሪዎቹ አንዱ የሆነውን የመሥሪያ ቤቱን ባልደረባ ከግቢው ውጪ አገኘሁት።
መለሰ ተ/ማሪያምና እኔ የአንድ ዓመት ምሩቃን ነን።እርሱ በስነ-ጽሁፍ ተመርቆ ውጭ ጉዳይ ፕሬስ መምሪያ ውስጥ ይሰራል።እኔና እርሱ የምንካፈለው የጋራ ነገር አለን።
ጠላ እየሸጡ ያስተማሩትን እናቱን ለመርዳትና ኑሯቸውን ለመቀየር ቤታቸውንም ለመሥራት ያለውን ምኞት ይዞ ውጭ ጉዳይ መሥራት ከጀመረ እነደ እኔ አራት ዓመት አልፎታል።እርሱም እንደ እኔ ራቱን ዳቦ በሙዝ እየጨረገደ ተመስገን ብሎ መኖርን ልማዱ ያደረገ ነበር።ሆኖም ግን ምኞቱን እውነት ሳያደርግ ከ42ቱ ተባራሪዎች መካከል አንዱ አደረጉት።እርሱም እንደ እኔ ነገሩ ሁሉ ግራ ገብቶታል።
አንተም እንደ እኔ የእሳት ራት ሆንክ ሲል ጠየቀኝ።
አዎን የእሳት ራት ሁኜያለሁ።
መለሰ ተ/ማሪያም ከእኔ በላይ ተስፋ ቆርጧል።”በዚህ ዓለም ከእነዚህ ሰዎች ጋር መኖር አያስፈልግም።እዝህ መሥሪያ ቤት በመሥራቴ ያተረፍኩት ፀፀት እንጂ ተስፋ አይደለም።ተስፋየ ሞቷል።ተስፋው የሞተ በሥጋው ቢኖርም ያው እንደሞተ ነው።እንድኖር ያደረገኝ አንድ ተስፋ ነበር።አሁን ያ ተስፋ ሙቷል።አልቋል።ተፈጽሟል።ከእነዚህ ሰዎች ጋር መኖርና መሥራት ሥቃይ ነው የሆነብኝ።ሁል ግዜ መሠቃየት ደግሞ ይታክታል” አለ በአሮጌ ጫማው የሚደፈጥጣትን አንዲት ትንሽ ጠጠር ወደ ታች ወደ ውስጥ ይበልጥ እየደፈቃት።
ምን ማለቱ እንደሆነ የገባኝ ከውጭ ጉዳይ ከተባረረ በኋላ አሰላ ሂዶ ከተወለደበት ከሚስኪን እናቱ ቤት ራሱን ሰቅሎ መሞቱን ከሰማሁ በኋላ ነው።
ይቀጥላል . . .