ህወሃት ኦሮሞን እና አማራውን ለማጣላት ደፋ ቀና እያለ ነው ‪- ግርማ ካሳ

Unity

በጎንደር ተቃዉሞ በተነሳ ጊዜ የሕወሃቱ ጌታቸው ረዳ በትግራይ ሰዎች ላይ ጥቃት ደረሰ በሚል በኢቢሲ ወጥቶ ሲናገር፣ የአማራው ክልል መንግስት ቃል አቀባይ ግን ጌታቸው ረዳ የተናጋረዉን በማጣጣል በማንም የተለየ ብሄረሰብ ላይ ጥቃት ተነጥሎ እንዳልደረሰ መናገራቸው ይታወቃል።

በሕወሃቶች ጠብ ጫሪነት በተፈጠረው ቀዉስ፣ ወደ አላስፈላጊ ሁኔታ በመኬዱ፣ በንብረት ላይ ጥፋት እንደደረሰ ያልካዱት የአማራው ክልል ቃል አቀባይ አቶ ንጉሱ ፣ በወቅቱ ለሕዝብ ግልጽ ይሆን ዘንድ ፣ ነገሩ አስፈላጊ ባይሆንም፣ በንብረታቸው ላይ ጉዳት ከደረሰባቸው ወገኖች መካከል የትግራይ ተወላጆች ወደ 30% ብቻ እንደሆኑ ነበር የገለጹት።

ሆኖም ግን የሕወሃቱ ቃል አቀባይ ሆን ብለው ከ70% በላይ ጉዳት የደረሰባቸውን ሳይጠቅሱ በትግራይ ተወላጆች ላይ ብቻ ጥቃት እንደደረሰ መናገራቸው ከአንድ የመንግስት ቃል አቀባይ ነኝ ከሚል የማይጠበቅና አሳፋሪ ከመሆኑም ባሻገር፣ ሕወሃቶች ለስልጣናቸው ሲሉ ህዝብን ከሕዝብ ማጋጨቱንና በኢትዮጵያዉያን መካከል የዘር ጥላቻን ማሳደግ እንደ ስትራቴጂ አድርገው እየተጠቀሙበት እንደሆነም አመላካች ነው።

በዚህም መሰረት ነው ዛሬ በባህር ዳር ከተማ በተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የባህር ዳር ህዝብ በይፋ አጋርነቱን ለመብትና ለነጻነት እየተዋደቀ ላለው የኦሮሞ ህዝብ እየገለጸ፣ የነ በቀለ ገርባን ፎቶ ይዞ “በቀለ ገርባ መሪያችን እንጅ ሽብርተኛ አይደለም” ፣ “የኦሮሞ ወገኖቻችን ደም የኛም ደም ነው” ብሎ ከፍ አድርጎ ድምጹን እያሰማ ባለበት፣ በተመሳሳይ ሁኔታ በኦሮሚያ ዋና ከተማ በሆነችው የአዳም ከተማ ተቃዉሞ ለማሰማት የወጡ ኦሮሞዎች እነ አንዱዋለም አራጌን፣ እነ እስክንድር ነጋ ይፈቱ በማለት፣ በጎንደር እየደረሰ ያለዉን ግደያ በመቃወም፣ “አማራ የኛ ነው” እያሉ ድምጻቸውን በማሰማት ሕወሃት በኦሮሞው እና በሌላው ማህበረሰብ ላይ የዘረጋው የመከፋፈል ግድግድ መደርመስ መጀመሩንባሳዩበት ሁኔታ ሕወሃት የተለመደዉን አሳፋሪ ጨዋታ ለመጫወት እየሞከረ ነው።በሚቆጣጠረው ሜዲያ የኦሮሞውን እና የአማራውን ማህበረሰብ ለማጋጨት ደፋ ቀና እያለ ነው።

የሕወሃት ደህንነት የደህንነት ሃይሎች ባህርዳር የሚገኘውን የኦሮምያ አለማቀፍ ባንክ ላይ ጥቃት በማድረግ፣ በአማራና በኦሮሞ መካከል ግጭት ለመፍጠር ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ሥራ ከሰሩ በኋላ፣ ኢቢሲ ማምሻዉን ካልጠፋ ዜና፣ የጥፋት ሃይሎች በኦሮሞ ህዝብ ላይ በባህር ዳር ጥቃት ፈጸሙ የሚል አይነት ዜና እያናፈሰ እንደሆነ እየተሰማ ነው።

አብዛኛው የኦሮሚያ አካባቢዎች፣ ድፍን የሰሜን እና የደቡብ ጎንደር ዞኖች፣ ዛሬ ደግሞ ደግሞ ጎጃም የሕወሃት አገዛዝ አንገፈገፈን ብሎ በተነቃነቀበት ሁኔታ መቀሌና አዲስ አበባ የተቀመጡ አክራሪና ጥጋበኛ የህወሃት አመርሮች ግን አሁንም የሕዝብን ጥያቄ ከማክበር ይልቅ በሚቆጣጠሩት ሜዲያ በሕዝብ ላይ መሳለቃቸው ሰዎቹ ዉድቀታቸውን እያፋጠኑ መሆኑን አመላካች ነው።

በኦሮሚያ በሌሎች ወገኖች ላይ “አማራ ናችሁ” በሚል ለሃያ አምስት አመታት ጥቃት እንዲፈጸም ሲያደርጉ የነበሩት፣ ለኦህዴድ መመሪያ በመስጠት ሕወሃቶች ነበሩ። በዚህ በኩል የዘር ማጽዳት ወንጀል እንዲፈጸም እየገፋፉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ “ኦሮሞ ሊጨርስህ ነው፣ እኛ ነን ያለንህ” በማለት ኦሮሞ ያልሆነው የኦሮሚያ ነዋሪ ፈርቶ ወደእ ነርሱ እንዲጠጋ ሲያስፈራሩት ኖረዋል። (ለዚህ በማያጠራትር ሁኔታም የአክራሪው ኦነግ ከሕወሃት ጋር ስልጣን ጨብጦ የነበረ ጊዜ የፈጸማቸዉን የጭካኔ ተግባራቶች ህወሃትን ረድተዉታል)

ለኦሮሞዎች ደግሞ የአናሌ ሃዉልት አይነት እንዲሰራ በማድረግ ፣ ኦሮሞው በአማራው ላይ ጥላቻው እንዲጠነክር በመስራት፣ “አማራው ቋንቋህን ሊያጠፋ ነው፤ የድሮውን የነፍጠኛ ስርዓት መልሶ ሊያመጣብህ ነው..እኛ ነን ከአማራው የምንጠብቅህ ” እያሉ፣ ከሌላው ማህበረሰብ ጋር እንዳይግባባ አማርኛ እንዳይማርና እንዳያቅቅ እያደረጉ በከፋፍለህ ግዛ ታክቲክ ለ25 አመታት በስልጣን ላይ ቆይተዋል።

ሆኖም ግን ይህን ጨዋታ ኦሮሞው ሆነ ሌላው ማህበረሰብ ጠንቅቆ ገብቶታል። ከዚህ በኋላም የሚሰራ አይደለም።