አራት የስፖርት ጋዜጠኞች የፖለቲካ ጥገኝነት ጠየቁ

በየዓመቱ የሚካሄደውን የዳይመንድ ሊግ የአትሌቲክስ ውድድር ለመዘገብ ወደ አሜሪካ እና ስዊድን አምርተው የነበሩት አራት ኢትዮጵያዊያን የስፖርት ጋዜጠኞች የፖለቲካ ጥገኝነት ጠየቁ። ጉዳያቸውንም የየአገራቱ መንግስታት እየተከታተሉት መሆኑን ተናግረዋል።
በአሜሪካ የፖለቲካ ጥገኝነት የጠየቁት ጋዜጠኞች የአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሃን ባልደረባ የነበረው አመሃ ፍሰሃ፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘጋቢ የነበረው ሊባኖስ ዮሃንስ እና የቀድሞው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የስፖርት ክፍል ባልደረባ የነበረው ሳምሶን ከተማ ናቸው። ሶስቱ ጋዜጠኞች ባለፈው መጋቢት ወር ላይ በአሜሪካ ዩጂን ተካሂዶ የነበረውን የዳይመንድ ሊግ ውድድር ለመዘገብ እንደሄዱ ያስታወሱት ጋዜጠኞቹ ወደ አገራቸው መመለስ እንደማይፈልጉ ለአሜሪካ መንግስት ማስታወቃቸውን ተናገረዋል። ምክንያታቸውን ሲያቀርቡም ፖለቲካዊ መሆኑን በመግለጽ ነው።
ሌላው በስዊድን የሚገኘው ደግሞ የቀድሞው የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የስፖርት ክፍል ባልደረባ የነበረው ጋዜጠኛ ቶማስ ሰብስቤ ነው። በተለይ ቶማስ ሰብስቤ እንደገለጸው “ጉዳዩን የስዊድን መንግስት እያየልኝ ነው። ለጊዜው በሆቴል ተቀምጫለሁ” ሲል የፖለቲካ ጥገኝነት መጠየቁን ተናግሯል።