አንዱዓለም አራጌ የግድያ ሙከራ እንደተደረገባቸው ለፍርድ ቤት አሳወቁ
(Reporter) — የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ አንዱዓለም አራጌ በተጠረጠሩበት የሽብር ወንጀል በታሰሩበት ማረሚያ ቤት፣ የካቲት 7 ቀን 2004 ዓ.ም በአንድ ዕድሜ ልክ በተፈረደበት ግለሰብ የግድያ ሙከራ እንደተደረገባቸው፣ ጉዳያቸውን በመመርመርና በማየት ላይ ለሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ ወንጀል ችሎት የካቲት 26 ቀን 2004 ዓ.ም ተናገሩ፡፡ ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪዎቹን ለየካቲት 26 ቀን 2004 ዓ.ም ቀጥሮ የነበረው፣ ቀደም ባሉት ችሎቶች በሽብር ወንጀል ክስ የመሠረተባቸውን የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ፣ የሰዎችና የሰነድ ማስረጃዎች ካዳመጠና ከመረመረመ በኋላ ‹‹ተከላከሉ›› በማለቱ፣ የተጠርጣሪዎቹን የመከላከያ ምስክሮች ለመስማት ነበር፡፡
በዕለቱ ተጠርጣሪዎቹ ከማረሚያ ቤት ወደ ፍርድ ቤት የቀረቡ ቢሆንም፣ ዓቃቤ ሕግ ያሰማቸው የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች ተገልብጠው ስላልደረሷቸው፣ ጠበቆቻቸውና ተጠርጣሪዎቹ በመቃወማቸው መከላከያ ምስክሮቹ ሳይሰሙ ቀርተዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ብይኑ ተገልብጦ ባይሰጣቸውም መዘጋጀት እንደነበረባቸው ቢገልጽም፣ ጠበቆቹ ‹‹ፍርድ ቤቱ ተገልብጦ እንዲሰጥ አዞ ስለነበር ስንጠብቅ ጊዜው አለፈብን፤› በማለታቸው ሌላ ቀጠሮ ከተሰጠ በኋላ አቶ አንዱዓለም ማስረዳታቸውን ቀጠሉ፡፡
አቶ አንዱዓለም ለፍርድ ቤቱ ጨምረው እንዳስረዱት፣ ድብደባው በተፈጸመባቸው ጊዜ ለፍርድ ቤት ሲያዘጋጁት የነበረ ሰነድ ተወስዶባቸዋል፤ ጤናቸውም እንደተዛባ ገልጸው፣ ከማረሚያ ቤት ውጭ ባለ የሕክምና ቦታ እንዲታከሙ እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡
በአቶ አንዱዓለም ላይ የደረሰውን ድብደባ በሚመለከት በሕግ አግባብ መጠየቅ እንደሚቻል ፍርድ ቤቱ አስረድቶ፣ ‹‹ሰነድ ተወስዶብኛል፣ ሕክምና ያስፈልገኛል፣ በማረሚያ ቤት በአግባቡ አልተያዝኩም፤›› የሚሉትን ጥያቄዎች በሚመለከት የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ፍርድ ቤት ቀርበው እንዲያስረዱ አዟል፡፡
ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ ካቀረቡት ውስጥ የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ናትናኤል መኮንና አቶ ክንፈ ሚካኤል አበበ (አበበ ቀስቶ) ሲሆኑ፣ አቶ አንዱዓለምን የድብደባ ጉዳት ያደረሰባቸው ታራሚ እነሱ ዘንድ ተዛውሮ መታሰሩን ጠቁመው፣ ለሕይወታቸው እንደሚያሰጋቸው አመልክተዋል፡፡
በማንኛውም ወቅት ችግር ሊያደርስባቸው እንደሚችል በመስጋት የሚተኙት በየተራ (ናትናኤል ሲተኛ፣ ክንፈ ሚካኤል ይጠብቃል) መሆኑን ለፍርድ ቤቱ ያስረዱት ተጠርጣሪዎቹ፣ በምግባቸውም ላይ መርዝ ጨምሮ ያጠፋናል የሚል ስጋት ስላላቸው እሱን ወይም እነሱን ማረሚያ ቤቱ ለብቻቸው እንዲያስራቸው ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡
ታራሚው (አቶ አንዱዓለምን ደበደበ የተባለው) በታሰሩበት ክፍል ውስጥ የተናገራቸውን ለፍርድ ቤቱ ክብር ስለማይመጥን መናገር እንደማይፈልጉ የገለጹት ተጠርጣሪዎቹ፣ ታራሚዎቹ ኢትዮጵያውያን ባይሆኑ ኖሮ ሊያስገድላቸው እንደነበር ለፍርድ ቤቱ መግለጻቸውን ጠበቃቸው ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡ ታራሚዎቹ የተናገሩትንና ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ምላሽ ለጋዜጠኞች የገለጹት የአቶ አንዱዓለም አራጌ፣ የአቶ ናትናኤል መኮንን፣ የአቶ እስክንድር ነጋና የአቶ ክንፈ ሚካኤል አበበ ጠበቃ፣ ጠበቃ ደርበው ተመስገን ናቸው፡፡
በዕለቱ የነበረውን ችሎት ለመታደም በልደታ ፍርድ ቤት የተገኙት የተጠርጣሪዎች ቤተሰቦች፣ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር፣ የአገር ውስጥና የውጭ ጋዜጠኞችና ሌሎች የችሎት ታዳሚዎች ቢሆኑም፣ የፍርድ ቤቱ ችሎት አስቻይ ፖሊሶች አምባሳደሩን፣ የውጭ አገር ጋዜጠኞችን፣ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳንና ጥቂት ሌሎች ታዳሚዎችን አስገብተው የአገር ውስጥ ጋዜጠኞችን በመከልከላቸው በችሎቱ ውስጥ ገብተው መዘገብ አልቻሉም፡፡ ችሎት አስቻይ ፖሊሶቹ እንደ ምክንያት የገለጹት፣ ‹‹ችሎቱ ጠባብ ስለሆነ ነው›› የሚል ቢሆንም፣ ሌላ ጊዜ እንደሚደረገው ሒደቱን በሰፊ የማስቻያ ቦታ እንዲሆን ማድረግ ወይም በታራሚዎች ከመሙላት ተጠርጣሪዎችን በየተራ ማስገባት ይቻል እንደነበር ጋዜጠኞቹ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ የዕለቱ ችሎት ከዝግ ችሎት ተለይቶ እንደማይታይም ጋዜጠኞቹ ተናግረዋል፡፡
በፀረ ሽብርተኝነት ተጠርጥረው ጥቅምት 30 ቀን 2004 ዓ.ም ክስ ከተመሠረተባቸው 24 ተጠርጣሪዎች መካከል፣ በአገር ውስጥ ሆነውና በማረሚያ ቤት ጉዳያቸውን በመከታተል ላይ ያሉት አንዱዓለም አራጌ፣ ናትናኤል መኮንን፣ ዮሐንስ ተረፈ፣ የሸዋስ ይሁንዓለም፣ ክንፈሚካኤል ደበበ፣ ምትኩ ዳምጤ፣ እስክንድር ነጋና አንዱዓለም አያሌው ናቸው፡፡