ለሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ ‹‹የማጽናኛ መዋጮ›› ሊበረክትላቸው ነው
- (ደጀ ሰላም፤ ኦገስት 18/2010፤ ነሐሴ 12/2002 ዓ.ም):- በቁጥር ከስድሳ የማያንሱ እና በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥር የሚገኙ የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤያት ጸሐፊዎች እና አንዳንድ የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎች ለአወዛጋቢው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ ‹‹የማጽናኛ መዋጮ›› ሊያበረክቱ ማቀዳቸው ተሰማ፡፡ የሀገረ ስብከቱ ምንጮች ለደጀ ሰላም ያደረሱት መረጃ እንደሚጠቁመው፣ ‹‹የማጽናኛውን መዋጮ›› ለማስፈጸም በዋናነት እየተንቀሳቀሱ የሚገኙት የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ጸሐፊዎች እና አንዳንድ አስተዳዳሪዎች ሲሆኑ ማጽናኛው የሚከናወነው ጸሐፊዎቹ ባሰባሰቡት የገንዘብ አስተዋፅኦ ነው፡፡
እንደ ምንጮቹ ገለጻ እስከ አሁን ድረስ ሥራ አስኪያጁ በግላዊ እና ማኅበራዊ ኑሯቸው ከደረሰባቸው የሞራል ጉዳት ለማጽናናት ታስቦ እየተደረገ ያለው የገንዘብ አስተዋፅኦ መጠኑ 30‚000 ብር ገደማ መድረሱ የተመለከተ ሲሆን ከነገ በስቲያ ዓርብ ለሥራ አስኪያጁ እንደሚበረክትላቸው ለመረዳት ተችሏል፡፡ ሱባኤውን ምክንያት በማድረግ በድሬዳዋ ሀገረ ስብከት የሚገኙት እና ሕመማቸው እንደጠናባቸው የሚሰማው ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ወደ አዲስ አበባ ከመመለሳቸው በፊት በጥድፊያ እንዲፈጸም ታስቦ የተደረገውን ይህንኑ ‹‹ገንዘባዊ ማጽናኛ›› በዋናነት የመሩት ፀጋዬ ግደይ (ከመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም – ግቢ ገብርኤል)፣ መልአከ ፀሐይ በቀለ (የፈረንሳይ ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ)፣ መምህር ሰሎሞን በቀለ (የደብረ ነጓድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ጸሐፊ)፣ መንግሥቱ (ከደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን) መሆናቸው ታውቋል፡፡ የገንዘብ አስተዋፅኦው ምንጭ ከየት እንደ ኾነ እንዲሁም የት እና በምን አኳኋን ለሥራ አስኪያጁ እንደሚበረከትላቸው ለጊዜው ለማረጋገጥ አልተቻለም፡፡ በቁጥራቸው ስድሳ ያህል ይሆናሉ የተባሉት የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ጸሐፊዎች በተጠቀሰው አኳኋን ተቆርቋሪነታቸውን ሊያሳዩ የበቁት ከሚበዙት የሀገረ ስብከቱ አድባራት እና ገዳማት አስተዳዳሪዎች በተቃራኒ ከሥራ አስኪያጁ ጋራ በመሠረቱት በጥቅም ላይ የተመሠረተ ልዩ ግንኙነት ምክንያት እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡ ይኸውም ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ የፀሐፊዎቹን ዘመድ አዝማድ እና ወዳጆች በተለያዩ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን በማስቀጠር እና አግባብነት የሌለው ዕድገት እና ዝውውር በመስጠት የሚገለጽ ሲሆን ፀሐፊዎቹ በበኩላቸው ደግሞ በዋናነት ለሥራ አስኪያጁ ውለታ በሚያበረክቱላቸው በዐሥር ሺሕ ብሮች የሚቆጠር እጅ መንሻ እና ሌሎች የዓይነት ስጦታዎች የሚፈጸም ነው፡፡ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጩ በመዋጮ ትዳር የመመሥረት፤ የሞባይል፣ የነዳጅ፣ የቤት ቁሳቁሶቻቸውን እና የዕለት ምግባቸውን ወጪዎች በደጅ ጠኚዎች መዋጮ የመሸፈን፣ ይህንንም በአጋፋሪዎቻቸው በኩል በማስፈጸም ገንዘብ የማጋበስ ልማድ ክፉኛ የተጠናወታቸው መሆኑ ይነገራል፡፡ ሥራ አስኪያጁ ከአጥቢያ ሰበካ ጉባኤያት ጸሐፊዎች ጋራ በመሠረቱት ልዩ የጥቅም ግንኙነት ሳቢያ የተማረሩ የአጥቢያዎቹ አስተዳዳሪዎች አቤቱታቸውን ፓትርያርኩ ዘንድ እስከ ማቅረብ ደርሰው እንደ ነበር እኒሁ የሀገረ ስብከቱ ምንጮች ያስረዳሉ፡፡ ለሥራ አስኪያጁ ‹‹የማጽናኛ መዋጮ›› ለማበርከት ሰበብ ሆኖ የተጠቀሰው ‹‹የሐውልቱ ሥር ቁማርተኞች›› በሚል ርእስ በስውሩ ጸሐፊ ‹ሊቀ ትጉሃን› ዘሪሁን ሙላቱ በቅርቡ ‹‹የተጦመረው›› አሸማቃቂ ጽሑፍ የሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጩን ግላዊ ሕይወት፣ ማኅበራዊ ግንኙነት እና የሥራ ተነሣሽነት በእጅጉ መጉዳቱ እንደ ሆነ ተገልጧል፡፡ ‹‹ነገረ ፋንታሁን›› በሚለው የጽሑፉ ክፍል(ገጽ 9 – 23) ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጩ በቀደመው ኑሯቸው – ‹‹ጨካኝ የደርግ ኀምሳ አለቃ›› አሁን ደግሞ ‹‹የኢሕአዴግ ዋናው ሰው እኔ ነኝ›› እያሉ በ‹ፖሊቲካ ጫዎታ› የሚያምታቱ፣ ‹‹በትዳር ሕይወታቸው ላይ ባደረሱት ከፍተኛ ደባ፣ ቅሌት እና የወሲብ መዘዝ ብዙዎችን ወደ መቃብር ያሳደዱ፣ የግል ጤንነታቸው የማያሳስባቸው እና በራሳቸው ተስፋ የቆረጡ››፣ በትምህርት ይዞታቸው ‹‹ሰነፍ›› ከመሆናቸው የተነሣ ‹‹3ኤፍ›› የሚል ቅጽል ስም የተሰጣቸው፣ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ባገኙት ነጻ የትምህርት ዕድል መሠረት ከፍተኛ ትምህርታቸውን በሚከታተሉበት ኦስትርያ/ቪዬና ‹‹ወደፊት የካቶሊክ ካህን ለመሆን በመሐላ የተፈጠሙ›› ይኹንና ‹‹የሚያወግዛቸው አጥተው፣ ቅዱስ ነኝ ብለው ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ጋራ የተሰለፉ››፣ በአስተዳደራቸው በገጠማቸው ‹‹የብቃት ግሽበት›› ሀገረ ስብከቱን እንደ ግል ግሮሰሪያቸው በመቁጠር በሥራ ፈላጊ ካህናት ላይ ጭከና እና አረመኔነት የተመላበት የሰብአዊ መብት ረገጣ እየፈጸሙ በሰብአዊ መብት ተሟጓቾች ዘንድ የቤተ ክርስቲያናችንን ገጽታ ያበላሹ – ‹‹መደዴ››፣ በሚልዮኖች የሚቆጠር የቤተ ክርስቲያንን ጥሬ ገንዘብ በዘረፋ በማካበት ብልጽግናን በአቋራጭ የተቆናጠጡ -‹‹ወቅታዊ ባለጸጋ››፣ የአቅም ግንባታ ጥረትዋን የሚያዳክሙ – ‹‹ሙሰኛ››፤ በአጠቃላይ ካለባቸው ከፍተኛ የሥነ ምግባር ግድፈት አኳያ በፍትሕ መንፈሳዊ እንደተደነገገው ከሐላፊነታቸው ተነሥተው እና ከክህነታቸው ተሽረው በሕግ መጠየቅ እንደሚገባቸው እና ይህም ‹‹ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን መታደግ›› መሆኑን ያሳስባል፡፡ በተያያዘ ዜና በትላንትናው ዕለት ተሲዓት በኋላ ከስውሩ ጸሐፊ አዲሱ ‹መጽሐፍ› ሥርጭት ጋራ በተገናኘ አክሊል ዳምጠው የተባለ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዝሙር ፒያሳ አካባቢ ለአጭር ጊዜ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ ‹‹በስሕተት ነው›› በሚል መለቀቁ ተሰምቷል፡፡ ይኸው ደቀ መዝሙር ቀደም ሲል ከግንቦት 1997ቱ ምርጫ መነሣሣት ጋራ በተያያዘ ከኮሌጁ ታግደው ከነበሩት እና ባለፈው ዓመት ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ በአስተዳደሩ ከተፈቀደላቸው ዐሥራ አንድ ደቀ መዛሙርት አንዱ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ በሌላ በኩል በዚሁ ‹መጽሐፍ› ከእነ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ እና በጋሻው ደሳለኝ ጋራ ‹‹ቅዱስ ፓትርያሪኩን ማስፈራሪያ እና የንግድ ምልክት ያደረጉ የዘመናችን አፍኒን እና ፊንሐስ›› የተባሉት ወይዘሮ እጅጋየሁ በየነ የማያባራ ራስ ምታት በሆነባቸው የቀድሞ ወዳጃቸው የአሁኑ ባላንጣቸው ሊቀ ትጉሃን ዘሪሁን ሙላቱ ጉዳይ ላይ ለመምከር የሱባኤውን መጠናቀቅ ሳይታገሡ ፓትርያሪኩ ወደሚገኙበት ድሬዳዋ ለመብረር ተነሥተዋል ቢባልም በርግጥም ይሂዱ አይሂዱ ለማረጋገጥ አልተቻለም፡፡ በድሬዳዋ የሚገኙ ምንጮቻችን ዘግይተው እንደጠቆሙን ወይዘሮዋ በስውሩ ጸሐፊ በተጋለጡበት ጉዳይ የአቡነ ጳውሎስ ኀዘኔታ የተቸራቸው ቢሆንም የፓትርያሪኩ የጤና ይዞታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ነው በመባሉ በአግባቡ ተቀብለው ያስተናግዷቸዋል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ብዙዎች እንደሚናገሩት የስውሩ ጸሐፊ ተግባር በፓትርያሪኩ ቤተሰቦች ዘንድ እንደ መልካም አጋጣሚ ከመታየቱም በላይ በአሁኑ ወቅት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን አስተዳደር መምሪያ በሐላፊነት በሚቆጣጠሩት ሊቀ ኅሩያን ያሬድ ከበደ ሳይቀር ቀድሞ ታውቆ በኅትመቱ እና ሥርጭቱ ረገድ ልዩ ማበረታቻ እና የገንዘብ ድጋፍ ሳይደረግለት አልቀረም፡፡ ለዚሁም ምክንያቱ በተለይም ሊቀ ኅሩያን ያሬድ ከበደ የአቡነ ጳውሎስን ‹‹ሐውልተ ስም›› መተከል በተመለከተ ከወ/ሮ እጅጋየሁ ጋራ የገቡበት እሰጥ አገባ እና የወሰዱት የተቃውሞ አቋም ነው፡፡ ሊቀ ኅሩያን ያሬድ ሐውልቱ እንዳይተከል እና በተገለጠበትም ዕለት በምረቃው ሥነ ሥርዐት ላይ እንዳይገኙ በልቅሶ ጭምር አቡነ ጳውሎስን ቢማፀኗቸውም ፓትርያሪኩ፣ ‹‹እናንተ እንዲህ የምትሉት ለእኔ ክብር ስለማትጨነቁ ነው፤›› በማለት በአቋማቸው ከመጽናታቸውም በላይ በዙርያቸው የሚገኙት ቤተ ዘመዶቻቸው የሐውልት ምረቃውን ማእከል ላደረገው ለ18ኛ ዓመት በዓለ ሢመታቸው ድምቀት በደከሙላቸው እና ‹‹ለክብሬ ይጨነቃሉ›› ባሏቸው በወ/ሮ እጅጋየሁ እና በሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒ (በዋናነት) በሚመራው የሐውልት እና የበዓል አከባበር ኮሚቴ በኩል የሚጠየቁትን እገዛ እንዲያደርጉ ኀይለ ቃል አዘል ማሳሰቢያ ሰጥተው ነበር፡፡ በዚሁ የፓትርያሪኩ አቋም መከፋታቸው የተነገረላቸው ሊቀ ኅሩያን ያሬድ በሐውልቱ ምረቃ ዕለት ዘግይተውም ቢሆን በስፍራው በመገኘት እነ ወ/ሮ እጅጋየሁ እና በጋሻው ደሳለኝ ያለከልካይ ሊፈነጩበት ያሰቡበትን ‹‹የስብከተ ወንጌል ጉባኤ›› በአጭሩ እንዲቋጭ ለመርሐ ግብሩ አስተባባሪዎች በማሳሰብ (በክርናቸው በመጎሰም ጭምር)፣ አልፎ አልፎም በብቸኝነት ሊቆጣጠሩት ያሰቡትን ድምፅ ማጉያ በመንጠቅ፣ በራት ግብዣው መርሐ ግብር ወቅትም ‹‹እግራቸውን ጎትተው›› እና በፓትርያሪኩ ሳይቀር ተለምነው በመምጣት ቅያሜያቸውን እና ቅዋሜያቸውን በግልጽ አሳይተዋል፡፡ በምሽቱ የራት ግብዣ የ‹‹ሐውልተ ስሙን›› ሥራ ሐሳብ በማመንጨት ስለ ክፉ ቀን ‹ውለታው› ከበጋሻው ደሳለኝ 40‚000 ብር እንደ ተጸበለ የተገለጠበት ስውሩ ጸሐፊ ‹ሊቀ ትጉሃን› ዘሪሁን ሙላቱም ከበዓል አሰናጅ ኮሚቴው የተዘጋጀውን የምስጋና ምስክር ወረቀት ከአቡነ ጳውሎስ እጅ ቢቀበልም ለሌላ ርምጃ እያደባ ነበር፡፡ በራሱ አገላለጽ ሰለባዎቹን ጥሩ አድርጎ ለመለጋት ‹‹በሜዳው ላይ እያመቻቻቸው›› ነበር – ‹‹እነዚህ የዘመኑ አፍኒን እና ፊንሐስ እንዲሁም የመናፍቃን ቅጥረኞች ከቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የክህነት አገልግሎትም ሆነ ሕዝባዊ አገልግሎት ተለይተው የንስሐ ዘመን ተሰጥቷቸው ስለ ኀጢአታቸው እንዲያለቅሱ እና ከምእመናንም ኅብረት እንዲለዩ ይህ ጦማረ ጽድቅ ተጦመረባቸው›› ይላል የአዲሱ ‹መጽሐፉ› መግቢያ!! የፀሐፊው ወዳጆች እንደሚሉት በመጽሐፉ የቀደመ ረቂቅ ውስጥ ስማቸው ተካትቶ ለጊዜው ከቀረላቸው ከእነ ሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒ ጋራ የሊቀ ኅሩያን ያሬድ ከበደ ‹ዶሴ›ም አንዱ የነበረ ቢሆንም ግለሰቡ አንድም ከላይ ስለተብራራው ድጋፋቸው አልያም ስውሩ ጸሐፊ ከእነ ወ/ሮ እጅጋየሁ በኩል ይከተለኛል ብሎ ከሚሰጋው ማንኛውም ጥቃት ሊያደርጉለት ከሚችሉት የተጠናከረ ጥበቃ አኳያ የሤራ ስሌቱን ሠርቶ እንዳስቀረው ይታመናል፡፡ ይህም ለስውሩ ጸሐፊ የደኅንነት ዋስትና የሰጠው ከመሆኑም በላይ ‹መጽሐፉ›ን በማሳተም እና በማሠራጨት በኩል የረዱት እና እያገዙት የሚገኙት ባልንጀሮቹ ተነጻጻሪ ነጻነት እንዲሰማቸው ሳያደርግ እንደማይቀር ይገመታል፡፡ ከእነ ወ/ሮ እጅጋየሁ በትይዩ መቆማቸው ግልጽ ሆኖ ከሚታየው የፓትርያሪኩ ዘመዶች መተባበር በመነሣት ባለፈው ሳምንት ዓርብ በሊቀ ትጉሃን ዘሪሁን ሙላቱ ላይ በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት የወጣው የ‹‹ሪፖርት አድርጉ ማሳሰቢያ›› በስውሩ ጸሐፊ ላይ ያን ያህል አሉታዊ ተጽዕኖ ሊኖረው እንደማይችል የጉዳዩ ታዛቢዎች አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡ ለዚህም አስረጅዎቻቸውን ሲጠቅሱ፣ በትላንትናው ዕለት ‹መጽሐፉን› ታሰራጫለህ›› በሚል በቁጥጥር ሥር በዋለ በደቂቃዎች ውስጥ ‹‹በስሕተት ነው›› በሚል የተለቀቀውን የቅድስት ሥላሴውን ደቀ መዝሙር ገጠመኝ ይጠቅሳሉ፡፡ ታዛቢዎቹ አክለው እንደሚያስረዱት ‹መጽሐፉ› ለኅትመት ከመዋሉ ጥቂት ቀናት በፊት የተወሰነው ረቂቅ ተልኮላቸው የነበሩት ወይዘሮ እጅጋየሁ ዘሪሁን ሙላቱን ለማስደብደብ ሁለት ጋሻ ጃግሬዎቻቸውን ይልኩበታል፡፡ ስውሩን ጸሐፊ ሲከታተሉት የቆዩት ጋሻ ጃግሬዎችም አራት ኪሎ አካባቢ ደርሰውበት ለጥቂት ደቂቃ ካሯሯጡት በኋላ ብዙም ሳይገፉበት ይመለሳሉ፡፡ የዚህ ዐይነቱ የፈራ ተባ ክትትል በወይዘሮዋ በኩል ያለውን ‹‹የኀይል ሥሡነት›› እንደሚያሳይ ይታመናል፡፡ ከድብደባው ለጥቂት ያመለጠው ስውሩ ጸሐፊም ስልክ በመደወል ወይዘሮዋን በአጸያፊ ስድብ ከሞለጫቸው በኋላ ብዙም ሳይቆይ ‹መጽሐፉ›ን በገበያ ላይ አውሎታል፡፡ እንግዲህ በዚህ መልኩ የኀይላቸውን ልክ የተረዱት ወይዘሮ እጅጋየሁ ከእነ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ እና ሌሎች ‹‹እማኞቻቸው›› ጋራ ለክስ እየተዘጋጁ ቢሆንም ብዙም እንደማይሰዳቸው በመጠራጠር ይመስላል በጽኑ ሕመም ላይ የሚገኙትን ፓትርያሪክ አጉራህ ጠናኝ ለማለት የተዘጋጁት፡፡ ሌላው የታዛቢዎቹ ተዛማጅ ማስረጃ ደግሞ፣ ሰሞኑን የሐውልት ሥራውን የሚቃወም ጽሑፍ አዘጋጅተው በመንበረ ፓትርያሪክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ዐጸድ ዙሪያ ሲለጥፉ በመገኘታቸው ብቻ ‹‹የሕዝብን ሰላም ማደፍረስ›› በሚል በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለው ከአራት ቀናት እስር በኋላ የተለቀቁትን የድጓውን ሊቅ ሊቀ መዘምራን መንግሥቱ ገብረ አብን ይመለከታል፡፡ ወዳጆቻቸው ‹‹የመንግሥቱ ማኒፌስቶ›› ያሉላቸውን የተቃውሞ መግለጫ ይዘት በትክክል ለማወቅ ባይቻልም ዐቃቤ ሕግ ድርጊቱ ‹‹የሕዝብን ሰላም ማደፍረስ ነው›› በሚል ባለፈው ዓርብ ዕለት ክስ መሥርቶባቸው እንደ ነበር ተሰምቷል፤ ይኹንና ወዲያው ከክሱ በነጻ ተሰናብተዋል፡፡ ታዛቢዎቹ ሁኔታውን እነ ሊቀ ኅሩያን ያሬድ ለሐውልት ሥራው ተቃዋሚዎች ሊኖራቸው ከሚችለው አጋርነት ጋራ ያገናኙታል፡፡ ሊቀ መዘምራን መንግሥቱ ከ1960 ዓ.ም ጀምሮ በትግራይ ሽሬ እና መቐለ ወንበር ዘርግተው ሲያስተምሩ የቆዩ አንጋፋ ምሁር የነበሩ ሲሆኑ በ1988 ዓ.ም በሲኖዶሱ ትእዛዝ ከተዘጋጀ በኋላ የትምህርተ ሃይማኖት ሕጸጽ እንዳለበት ተገልጾ የነበረውን መጽሐፍ እና በሀገረ ስብከቱ ይታይ የነበረውን አስተዳደራዊ በደል በመቃወም ምእመኑን ለሰላማዊ ሰልፍ እስከ ማስተባበር የደረሰ ተደማጭነት ነበራቸው፡፡ በመ/ፓ/ቅ/ቅ/ ማርያም ገዳም የዝማሬ መዋስዕት እና የአቋቋሙ መምህር ሆነው ሲያገልግሉ የቆዩት ሊቀ መዘምራን መንግሥቱ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት የዜማ መምህር ሆነው በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡
