እቴጌ ጣይቱ ብጡል እና እቴጌ አዜብ መስፍን


ይህንን ጽሁፍ ማንበብ ለሚፈልጉ፡- ማስጠንቀቂያ ቁጥር አንድ፤ ጽሁፉን በከፊልም ሆነ በሙሉ ለቀዳማይት እመቤቲቱ ማስነበብ አይፈቀድም፡፡ ማስገንዘቢያ ቁጥር ሁለት፤ እቴጌ አዜብን አንቺ እቴጌ ጣይቱን አንቱ እያልኩ የጻፍኩት፤ እቴጌ አዜብ ወጣት ስለሆነች (ወይም እንደወጣት ስለሚያደርጋት) ሳይሆን ከኢቲቪ በቀር አንቱ ብሎ የሚጠራት ሰው ሰምቼ ስለማላውቅ÷ እንደአርቲስት ‹አንቱ› አትባል ይሆናል ብዬ ነው፡፡

የዛሬን አያርገውና የሃገራችንን እቴጌዎች ጀብዱ መዘንጋት አይቻልም ነበር፡፡ እቴጌ ተዋበች ካሣን ‹‹እኔ ጀግና ወንድ እወዳለሁ›› እያሉ በጠላት ላይ የማያወላዳ አቋምና እርምጃ እንዲወስዱ ያደርጓቸው ነበር፡፡ እቴጌ ጣይቱ ብጡልንም የምናውቃቸውና የምናስታውሳቸው በዚሁ መሰል ጀግንነታቸው ነው፡፡ እቴጌ ጣይቱ ባይኖሩ ኖሮ የአድዋ ጦርነት ላይካሄድ፣ ኢትዮጵያም የውጫሌ ውል አንቀጽ 17ን ተቀብላ ልትቀጥል የምትችልባቸው ዕድሎች እንደነበሩ የሚገምቱ የታሪክ ባለሙያዎች አሉ፡፡ 

እቴጌ ጣይቱ ባይኖሩ ኖሮ ይሄ ዛሬ የምንመካበት ጥቁር ሕዝቦች ነጮችን ለመጀመሪያ ጊዜ ድል የነሱበት፣ ያልታጠቁ ሕዝቦች የታጠቀና የሰለጠነ ሰራዊትን መደምሰስ እንደሚችል ያሳየንበት የአድዋ ድል አይፀነስም ነበር፡፡ ከዚያም በላይ እቴጌ ጣይቱ ባይኖሩ ኖሮ የአድዋ ጦርነትን አናሸንፍም ነበር (ወይም እናሸንፋለን ለማለት ይከብድም ነበር) ምክንያቱም የጦርነቱ መደምደሚያ ከሆነው የአድዋ ጦርነት በፊት መቀሌ ላይ - ጣሊያኖቹ የሰሩት ምሽግ፣ ጫማ የሌላቸውን ኢትዮጵያውያን የማያስደርስ፣ በባለእሾህ የሽቦ አጥር የታጠረ፣ በጠርሙስ ስብርባሪ መሬቱ የተነጠፈ ነበር፡፡ ያንን ምሽግ ሰብረው መግባት የሞከሩት ኢትዮጵያውያን የሳት እራት ሆነው ቀርተዋል፡፡
በመጨረሻ ግን ጣሊያኖቹን ውሃ፣ ውሃ የሚያሰኝ መላ ለኢትዮጵያውያን አርበኞች የዘየዱት እቴጌይቱ ነበሩ፡፡ መፍትሄውም ጠላት የሚጠቀምበትንና ከምሽጉ አቅራቢያ የሚገኘውን የውሃ ምንጭ ገድቦ መክበብ ነበር፡፡ በሦስት ሜትር ካብና የእሾህ ሽቦ ታጥሮ የመሸገው የኢጣሊያ ሰራዊት በውሃ ጥም አለቀ፡፡ በመጨረሻም እጅ ለመስጠትና ለእርቅ ደረሰ፡፡ ይሄ ድል ባይገኝ ኖሮ አርበኞቻችን ቀስ በቀስ ረግፈው፣ ጣሊያኖችም ድልን ሊያጣጥሙ ይችሉ ነበር - ምስጋና ለጣይቱ!

እምዬ ምኒልክ ‹‹እምቢ›› ካፋቸው ማውጣት የሚቸግራቸው ሰው በመሆናቸው የማይጥማቸው ነገር ሲከሰት ‹‹እሺ፤ ነገ›› ማለት ያበዙ ነበር ይባላል፡፡ ነገር ግን በአገር ጉዳይ እሺታ ብቻ ሳይሆን እምቢታም ወሳኝ ስለሆነ ያንን ክፍተት በመሙላት እቴጌ ጣይቱ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ አዜብስ? ወ/ሮ አዜብ ከባለቤቷጋ ከአንድ ባሕር ነው የተቀዳችው፤ ሁለቱም እሺ አያውቁም፡፡ እሷ እንኳን እሺታ ብታውቅ የባለቤቷን ክፍተት ትሞላ ነበር፡፡ የሚገርመው ግን ከእምቢታዋም በላይ ያልተጻፈው የከልካይነት መብቷ ጉዳይ ነው፡፡

በእቴጌ ጣይቱ ዘመን የነበረው ስርዓት እንደሚፈቅደው ጣይቱ ከምኒልክ ያልተናነሰ ስልጣን ነበራቸው፡፡ ስለዚህ ያንን ስልጣናቸውን ተጠቅመው ቢሾሙ፣ ቢሽሩ አይገርምም፡፡ ወ/ሮ አዜብ ግን ወደዚያ ስርዓት ተመልሳ ይሁን ወይም በገዛ ፍቃድዋ ሳይታወቅ፣ ከዘመኑ ባፈነገጠ አሠራር የመሻርና የመሾም ባለመብት ነች እያሉ ብዙዎች ይምጰረጰሩላታል፡፡ ድንገት የሕወሃት ፖሊት ቢሮ አባል ሆና መገኘቷ፣ መጀመሪያ ሰሞን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣናቸውን ለባለቤታቸው ሊያወርሱ ነው እንዴ በሚል አስደንግጦን ነበር፡፡

አሁንም ቢሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣናቸውን እንደዛቱት ከለቀቁ፣ በወዘሮዋ አማካኝነት በእጅ አዙር የሚመሩበትን መንገድ መፍጠራቸው አይቀሬ ነው የሚል ጥርጣሬ አለኝ፡፡ አንዳንድ የዳያስፖራ መንደር መረጃዎችም ይህንኑ እየነገሩን ነው፡፡ ወይዘሮ አዜብ የሕወሃትን አመራር በባለቤቷ በኩል እያሾረችው መሆኑ ያስከፋቸው የሕወሃት ሰዎች እንዳሉ ተጽፎ አንብበናል፡፡

ይሄ ብቻም አይደለ፤ በመላው ዓለም ከተለመደው የፕሬዚደንት ሚስት ቀዳማይነት - ቀዳማይ እመቤትነቱን ከግርማ ወልደጊዮርጊስ ባለቤት የቀማችው ሴትዮይቱ የኢሕአዴግን በኢትዮጵያ ግዙፍ የኢኮኖሚ ሞኖፖሊ የመፍጠር ሕልም ታሳካለች የተባለላት ሰው ናት፡፡ ለዚያም ይመስላል የኤፈርት ሥራ አስፈፃሚዎች አንዷ ለመሆን የበቃችው፡፡ በጫት የውጭ ንግድም ቢሆን ተወዳዳሪ አልተገኘላትም፡፡ ከዚህም በላይ አሁን ደግሞ በሁሉም ቢዝነሶች ላይ እጆቿን ማስገባት እንደምትፈልግ እየተነገረ ነው፡፡ ወ/ሮ አዜብ ግን በዚህ አትስማማም፡፡ እንዲያውም ለልጆቿ የስኮላርሺፕ ለመክፈል ፍዳዋን እንዳየች ነው እሷ የምትናገረው፡፡ “ሃብት ፍለጋ ቢሆን ኖሮ” ብላለች ከECTV ጋር አድርጋ በነበረው ቃለ ምልልስ፣ “የመለስን ጭንቅላት መሸጥ ይቻል ነበር፤ ከመሪዎች ሁሉ ድሃ እኛ ነን”  ብላ ቁጭቷን ተናግራለች፡፡

ባለፈው ሰሞን ኃይሌን የሪዞርትህ ባለድርሻ አድርገኝ እያለችው ነበር ሲባል ሰምቼያለሁ (አቶ በረከት ስምኦንስ ቢሆኑ ‘ሲባል ሰምቻለሁ’ እያሉ አይደል መጽሃፋቸውን የጻፉት?)፣ ከባለፈው ሰሞን በፊት ደግሞ አሁን ከሃገር ኮብለለው ብሔራዊ የሽግግር ምክርቤት የመሰረቱት የዩኒቲ ዩንቨርስቲው ዶ/ር ፍስሐ እሸቴንም በቢዝነስ ካልተሻረኩህ እያለች ታስቸግራቸው ነበር አሉ፡፡ ምን ያልተባለ አይሸትም (Rumor has it!) ዶ/ሩ ራሳቸውምበስተመጨረሻ የሴቶች ፓንአፍሪካ ዩንቨርስቲን ሊከፍቱ የ20 አፍሪካ ዲፕሎማቶች ከፈረሙላቸው በኋላ “አዜብ ከለከለችኝ” አላሉም?

“ከእያንዳንዱ ስኬታማ ወንድ በስተጀርባ ጠንካራ ሴት አለች” ይባላል፡፡ አዎ! የአድዋ ድልን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ካበሰሩት ዳግማዊ ምኒልክ ጀርባ እቴጌ ጣይቱ ነበሩ፡፡ 21 ዓመታትን ወንበራቸው ሳይናጋ ከተቀመጡት ጠቅላይ ሚንስቴር መለስ ዜናዊ ጀርባም÷ ወ/ሮ አዜብ መስፍን አለች፡፡

------
In my defense for her, ወ/ሮ አዜብ የአፍሪካ ቀዳማይ እመቤቶች ፀረ ኤችአይቪ/ኤድስ ማሕበር ምክትል ፕሬዚደንት በመሆን ሰብአዊ ተግባር ላይ መሰማራቷ ይታወቃል፡፡

4 Comments on “እቴጌ ጣይቱ ብጡል እና እቴጌ አዜብ መስፍን”

  1. AZEB is responsible for the looting and killing going on in Ethiopia She is looting AIDS money. Who will decide the price of AIDS medicine produced by a woyane factory, distributed by a woyane company and who can kill or save Ethiopians when a woyane is a Health Minister. God knows how many are injected with AIDS or other disease carrying organisms all imprisoned for fake crime.

    Who killed Professor Asrat Woldeyes by denying medication, who knows about the health of Andualem, Eskinder and all others who are languishing under fascist woyane state torture chamber.

    http://articles2u.wordpress.com/2010/03/09/corruption-and-tplf

    http://gce-etc.tripod.com

    http://nitroethiopians.org/TPLF_Businesses.html

  2. ዉሻው መለሰን አንቱ ብለህ አዘብን አንቺ ትላታለህ.. ይህስ ከምን ይቆጠራል … እውነትም ጀግና ነህ

  3. “እቴጌ ጣይቱ ብጡል እና እቴጌ አዜብ መስፍን”፦በፍቃዱ ዘ ኃይሉ
    አቶ ፍቃዱ ዘ ኃይሉ ባለሥምንት አንቀፆችን ይዞ ኃይለ-ቃሉን በመንደርደሪያ ሃሳብዎ ለማዘናጋት በማጭበርበር ያስነበቡን ይህ ጦማር በውስጡ ብዙ ቁም-ነገሮችን ይዟል፣ሆኖም”በድቡሽት ላይ እንደተሰራ ቤት” “እቴጌ”የሚለውን ክቡር መጠሪያ እጇ በደም ለተጨማለቀ ገዳይ ወይዘሮ ያልሆነ ሥያሜ በመሰጠቱ ጦማሩ ዋጋ-ቢስ ሆኗል።በአንድ ወቅት ስለክብረ-ቢሶች እና የተከበሩ ሰዎችን ስለመግለፅ የፃፍኩትን ጦማር ያንብቡ።
    … ።መሰሪ፤ ላቫል:- ከ እንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከነበሩት ዊሊያም ሆር ጋር በ ታኅሣሥ ፲፱፻፳፰ ዓ.ም. ኢትዮጵያ ን ለ ፋሽሽት ኢጣልያ በሚያመች መልክ ለመከፋፈል የምስጢራዊ ስምምነት የፈጸሙ ናቸው።ጥቅምት ፭ ላቫል በሞት ተቀጡ።በመሰሪው የትግራይ ተወላጅ ደጃዝማች ተክሉ መሸሻ ተይዘው በጠላት እጅ ወዲያው ተረሽነው የሞቱት ራስ ደስታ ዳምጠው የካቲት ፲፭-1930 ዓ/ምህረት ነው።ከሃዲ፦***ሙሴ ቀስተኛ:- በአድዋ ጦርነት ተማርከው ወደ አዲስ አበባ የመጡት የጣልያን ወጥቶ አደሮች አብዛኞቹ በግንባታ እና የመንገድ ሥራ መስክ ተሰማርተው እንደነበር ይገልጽና ሙሴ ቀስተኛም ከነዚህ አንዱ እንደነበር ያረጋግጥልናል።በተለይም የራስ ደስታ ዳምጠውን አክስት ካገባ በኋላ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ምን ያህል አክብሮት እንዳገኘ ይነግረናል።
    የሙሴ ቀስተኛ ስም በታሪካችን ዘገባ ላይ እንደገና ብቅ የሚለው በ ግንቦት ወር ፲፱፻፴ ዓ/ም ላይ ሲሆን አሁንም እንደቀድሞው የግራዚያኒ መልእክተኛና ሰላይ በመሆን ለዕርቅ ስምምነት ከ ራስ አበበ አረጋይ ጋር ግንደበረት ላይ ተገናኝቶ ለግራዚያኒ አርበኞቹ ለመስማማት የሚፈልጉ መሆናቸውን አስታወቀ። የሠራዊቱንም ብዛት በተመለከተ የስለላ ዘገባውን ለግራዚያኒ አስታውቆ በተከተለው የፋሽሽት ጥቃት ብዙ ኢትዮጵያውያን አርበኞት አልቀዋል።ሦስተኛውና የመጨረሻው ተልዕኮው በ ጥቅምት ወር ፲፱፻፴፩ ዓ/ም ሲሆን በዳቄሮ በሚባል ሥፍራ ላይ ወደነበሩት ባላምባራስ (በኋላ ደጃዝማች) ገረሱ ዱኪ ነበር። ከሦስት ባላባቶች ጋራ የመጣው ሙሴ ቀስተኛ የሰባ አንድ ዓመት ሽማግሌ፣ ነጭ ጸጉር እና ባለሙሉ ጺማም ሲሆን አርበኞቹን ሰብስቦ በተጣራ አማርኛ፦
    “ንጉሠ ነገሥታችሁ እንኳን ትቷት የሄደውን አገር እናንተ በዚህ በልጅነት እድሜያችሁ ቅማል ወሯችሁ የማይቀርላችሁን ሞት ገደል ለገደል ከምታባርሩ ይልቅ ገብታችሁ ከኢጣልያ ጋር አገራችሁን በልማት ብታገለግሉ አይሻልም ወይ? መሣሪያችሁን አስረክባችሁ የገባችሁ እንደሆነ ኢጣልያ ትምራችኋለች፤ ሹመት እና ሽልማትም ትሰጣችኋለች” ብሎ ሲሰብካቸው ወጣት አርበኞቹም ቀደም ሲል በ፲፱፻፴ ዓ.ም ይኼው ሰላይ ወደ ራስ አበበ አረጋይ ዘንድ ሄዶ የጦሩን ኃይል ከሰለለ በኋላ ብዙ አርበኛ እንዳስፈጀ ሰምተው ስለነበር እነሱንም እንደዚሁ ለማስፈጀት እንደመጣ ተገንዝበውታል። ከሰበካው በኋላ ወደ እኩለ ቀን ሲሆን ተበተኑ።
    ሙሴ ቀስተኛም ወደሠፈረት ቦታ፣ በመጣባት በቅሎ በባሻ ኪዳኔ ወልደመድኅን ታጅቦ ሲሄዱ፣ ባሻ ኪዳኔ ቀስተኛ የለበሰው ካፖርት በደም እንዳይበላሽ በማሰብ “አባቴ ሐሩር ፀሐይ ነውና እንዳይውብቅዎት ካፖርትዎን ያውልቁት” ሲሉት “ልጄ ልትገለኝ ነው” አላቸው። ይሄኔ ባሻ ኪዳኔ ወልደ መድኅን በመውዜር ጠመንጃ ሲመቱት ‘ማማ ሚያ፤ ኢጣልያ ለዘለዓለም ትኑር ለኢጣሊያ ስል ሞትኩላት’ ብሎ ሲፎክር በሽጉጥ ራሱን መትተው ገደሉት። የለበሰውንም ሙሉ ገበርዲን ልብስና ካፖርት እንዲሁም የንግሥተ ነገሥት ዘውዲቱ ምስል ያለበትን የብር ሰዐትና በቅሎውን ከነኮርቻው ማረኩት። እሱም እንደተገደለ አብረውት መጥተው የነበሩት ባላባቶች ለጄነራል ናዚ አስታውቀው ኖሮ ሃያ ዓምስት ባታሊዮን ወታደርና ሃያ ስምንት አውሮፕላን ወደበዳቄሮ ዘምቶ ተርታውን ለሦሥት ቀን ሲከላከሉ ከቆዩ በኋላ አርበኞቹ ተሸንፈው ጠላትም የሙሴ ቀስተኛን እሬሳ አንስቶ ወሰደ። አርበኞቹም ከዚያ ሥፍራ ሸሽተው ሶዶ ላይ እንደገና ለስምንት ቀን ተዋግተው ገፉት።
    ተንኮለኞች፦እና የሥጋ ትሎች ተንኮለኛ የሰይጣን አርበኛ ፤ተንኮለኛ ተሰባብሮ ተኛ፤ ተንኮለኛ ናቸው ፣አርቃችሁ ቅበሯቸው ።ይባላል።የዘመኑ የሥጋ ትል፤ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ ኢትዮጵያን ለባዕዳን አሳልፎ የሸጠ ማነው ቢባል ከእነ መለስ ዜናዊ ይጀምራል ጣሪያው ደግሞ ሞሓመድ አልአሙዲ ነው:-የድሆችን ቤት ከሚዘርፉት ግንባር ቀደሙ ነውና።

  4. ጣይቱ ሚንሊክ ከጣሊያን ቢዋጉ::
    የኔድርሻ አለበት ሲደረመስ ደርጉ::
    ስንቱን ተጋዳላይ ያጋደልኩ እኔ ነኝ:
    ጠይቅ: መኮንንን: እኔን ካላመንከኝ::
    ስንቴ: በአጥር ዘሎ እዳላዘለለኝ:
    ሚስጥሩን: አውጥቶ: በ ኢሳት ያጋለጠኝ ::

    እኔ ሞኝ አይደለሁ ላገር የምሞተው:
    በዘሬም: የለብኝ :ነገም አላስበው::
    አያት: ቅድም አያቴ : ታሪክ ያቃቸዋል:
    ከጣሊያን ተዋጉ ሲባል ሰምታችኋል??
    ያልዘሩት: አይበቅልም: ነውና ተረቱ:
    አዜብም: አዜብ :ናት ጣይቱም ጣይቱ::
    የኔ ፍላጎቴ ላገሬ የምመኝው:
    ለሀገር: ከመሞት: ሀገርን መግደል ነው::
    ቢዝነስ: ነው: ሆቢዬ: ቢዝነስ :እወዳለሁ:
    ሀገሬን: በመሸጥ: እተባበራለ ሁ::

    በ ኤ ፈርት :ጉዳይ :ከመጣችሁብኝ:
    ህይወቴን :ለመስጠት :ሁሌም: ዝግጁ ነኝ::
    ኢኮኖሚው: በጥፍ: በያመቱ :የሚያድገው:
    የማታቁ: እወቁ : ሀገር ተሸጦ ነው::
    በእርግጥ: አደንቃለሁ :የጣይቱን ነገር:
    ጣሊያን: ወስዶት:ቢሆን :ምን: እንሆን ነበር?
    ልመና: ያልተው ነው:ከጫካ ጀምሮ
    የ ኤ ፈርት ከረጢት ተቀዳዶ ኖሮ::
    ለወባና ለኤድስ የሚላከው ሁሉ:
    እኔ ልብ: ሳልል :ተንጠባጥቧል አሉ::
    ጥሩ ቢዝነስ ናቸው:በሽታና :ችጋር:
    ያሰተዳድሩናል:እኔን :ከባሌ ጋር::

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*