ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ የአንድነት ፓርቲ ተጠባባቂ ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ

የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ ብሔራዊ ምክር ቤት ጥር 28 እና 29 ቀን 2003 ዓ.ም ያካሄደው ስብሰባ የ5 ዓመት የፓርቲውን እቅድ በማጽደቅና የስልጣን ሽግሽግ በማካሄድ መጠናቀቁን ዋና ፀሐፊው አቶ አንዱዓለም አራጌ አስታወቁ፡፡

በብሔራዊ ም/ቤቱ ስብሰባ ላይ በርካታ አጀንዳዎች ተነስተው ሰፊ ውይይት የተካሄደባቸው ሲሆን ከነዚህም መካከል ፓርቲው ለሚቀጥሉት 5 ዓመታት የሚመራበትን እቅድና ስትራቴጂ እንዲሁም የሚተገብራቸውን ዓላማዎች የያዘ ሰነድ ይገኝበታል፡፡ በም/ቤቱ የፀደቀውና ስድስት ምዕራፎች ያሉት የስትራቴጂክ እቅድ ሰነዱ ዝርዝር ይዘት ወደፊት ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም ም/ቤቱም የስልጣን ሽግሽግ ያካሄደ ሲሆን ኢ/ር ግዛቸው የምክትል ሊቀመንበርነት ስልጣናቸውን ለቀው ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ተክተዋቸዋል፡፡ የስልጣን ሽግሽጉን ተነሳሽነት የወሰዱት ኢ/ር ግዛቸውም በውጭ ጉዳይ ኃላፊነት እንዲቀጥሉ መወሰኑ ታውቋል፡፡

በተጨማሪ AbugidaInfo.com የሚከተለውን ዘግቧል

የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ጊዚያዊ የሃላፊነት ሽግሽግ እንዳደረገ ከስፍራዉ የደረሰን ዜና ያመለክታል። ከሶስት ወራት በኋላ የጠቅላላ ጉባኤ እስኪጠራና አዲስ የአመራር ምርጫ እስኪ ደረግ ድረስ፣ አምስት ወጣቶች ተግባራዊ ልምድ ይኖራቸዉ ዘንድ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ዉስጥ ገብተዉ እንዲሰሩ የተደረገ ሲሆን በቅርቡ ደግሞ ሌሎች ሶስት ይጨመራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ዉስጥ የገቡት ወጣቶች ድምጽ ከመስጠት ዉጭ በማናቸዉም የሥራ አስፈጻሚ ተግባራት የሚሰማሩ ሲሆን ሰፋ ባለ መልኩ የአመራር ብቃታቸዉን ያሳድጋሉ ተብሎ ይገመታል።
በተያያዘ ዜና የድርጅቱ ተጠባባቂ ሊቀመንበር ኢንጂነር ግዛቸዉ ከተጠባባቂ ሊቀመንበርነታቸዉ ተነስተዉ የዉጭ ጉዳይ ሃላፊ እንዲሆኑ የተደረገ ሲሆን በምትካቸዉ ዶር ነጋሶ ጊዳዳ የአንድነት ፓርቲ ተጠባባቂ ሊቀመንበር ሆነዉ ለሚቀጡሉት ሶስት ወራት አጠቃላይ ብሄራዊ ምርጫ እስኪደረግ ድረስ እንደተመረጡም የደረሰን ዜና አክሎ ይገልጻል።

በቅርቡ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያዘጋጀዉን የፓርቲዉን የሥራ እቅድና ቀጣዩን ስትራቴጂክ አካሄድ የሚተነትንና የሚያስረዳ ወደ መቶ ገጽ የሚደርስ ሰነድ የአንድነት ፓርቲ ብሄራዊ ምክር ቤት ያጸደቀዉ ሲሆን አባላትና ደጋፊዎች አስተያየት እንዲሰጡበት በቅርቡ በህገር ውስጥና በውጫገር ይሰራጫል ተብሎ ይጠበቃል።